የብልጽግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና የስነ-ምግባር ኮሚሽን በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጅግጅጋ ከተማ ስድስተኛ መደበኛ ስብሰባ አካሄዶ፣ ለስብሰባው የቀረቡትን አጀንዳዎች የኮሚሽኑን የ2016 በጀት ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርት በመገምገም፣ የኮሚሽኑን የተሻሻለ የአደረጃጀትና የአሰራር መመሪያ፣ የኮሚሽኑን የአቤቱታ አቀራረብና አፈታት መመሪያ እና የኮሚሽኑን የግምገማና የምዘና መመሪያዎች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግና ማሻሻያዎችን በማከል በኮሚሽኑ አባላት ሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
ከዚህም በተጨማሪ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብና የኮሚሽኑን የአሰራር መመሪያ ተገዢ ያልሆነ አንድ የኮሚሽን አባል ከኮሚሽኑ አባልነት ታግዶ ለጉባኤው እንዲቀርብ ወስኗል።
በአጠቃላይ ኮሚሽኑ በየደረጃው በሚገኘው የኮሚሽን መዋቅር የስድስት ወር አፈጻጸም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ መምጣቱ ተስፋ ሰጪ መሆኑንና በጥንካሬ የታዩትን በማጎልበት፣ የታዩ ድክመቶችን በማረም እንዲሁም በፓርቲው ለኮሚሽኑ የተሰጠውን ትኩረት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በመተዳደሪያ ደንቡ የተሰጡትን ተልዕኮ ለፓርቲው እሴት መጨመር በሚችል ሁኔታ መወጣት እንደሚገባ ገምግሟል።
በመድረኩ መጨረሻም ክብርት ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት የኮሚሽኑ ሰብሳቢ እስካሁን ባለው የኮሚሽኑ እንቅስቃሴ ተቋም ለመገንባት የተደረገው ጥረት ውጤት ማምጣት መጀመሩን ጠቅሰው፣ ኮሚሽኑ የመተዳደሪያ ደንብና የመመሪያዎች ተፈጻሚነት፣ የፓርቲውን የፓለቲካ ጥራት፣ የፓርቲውን ስነምግባር ከማስጠበቅና በፓርቲው ውስጥ የሙስና ትግል መሻሻሉን፣ የፓርቲውን አባላት መብቶችና ጥቅሞች ማስከበርና ገንዘብ፣ ንብረቶችና ሰነዶች በአግባቡ መጠበቃቸውን ቁጥጥር ከማድረግ አንጻር እንደጅምር ጥሩ የሚባሉ ስራዎች ቢኖሩም፣ ትኩረት ሰጥቶ መስራት የሚገባቸው በርካታ ስራዎች ላይ አቅጣጫ በመስጠት መደበኛ ስብሰባው ተጠናቋል።
ከነገ ጀምሮ ለሁለት ተከታይ ቀናት ለአምስተኛ ጊዜ የሚካሄደው የብልጽግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን ዋና ጽ/ቤት እና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የበላይ አመራር የጋራ የምክክር መድረክ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
“ጠንካራ ኢንስፔክሽን፤ ለጠንካራ ፓርቲ!”