“የመከላከያ ሰራዊቱን ስም በሀሰት ለማጠልሸት የሚደረገው ሙከራ አገር የማዳከም ሴራ መሆኑን በመገንዘብ
ወጣቶች ከሰራዊቱ ጎን ሊቆሙ ይገባል – የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አመራሮች
የመከላከያ ሰራዊቱን ስም በሀሰት ለማጠልሸት የሚደረገው ሙከራ አገር የማዳከም ሴራ መሆኑን በመገንዘብ
ወጣቶች ከሰራዊቱ ጎን ሊቆሙ እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አመራሮች ጥሪ አቀረቡ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ፈዲላ ቢያ እና አባንግ ኩሙዳን ÷ የመከላከያ ሰራዊቱ
የኢትዮጵያን ህልውና በጀግንነት በመጠበቅ የአገር አልኝታነቱን በተግባር ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንት ፈዲላ ቢያ÷ ሰራዊቱ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን
ብሔራዊ ኩራት ነው ብላለች፡፡
የመከላከያ ሰራዊቱ ማንነት ኢትዮጵያ መሆኗን ገልጻ÷ ሰራዊቱ አገር ለማፍረስ የተሞከሩ ጥቃቶችን
በጀግንነት ያከሸፈ የአገር አርማ ስለመሆኑም ገልጻለች፡፡
ሌላኛዋ የፓርቲው ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንት አባንግ ኩሙዳን በበኩሏ÷ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ
የሚደረግ ትንኮሳ አገር ለማፍረስ ከሚደረግ ሙከራ ተለይቶ የማይታይ መሆኑን ገልጻለች፡፡
ከዚህ አኳያ በአማራ ክልል ትጥቅ በማንገብ የሚንቀሳቀሰው ዘራፊ ቡድን መንገድ በመዝጋት ገበሬው
የመኸር የእርሻ ወቅት ተረጋግቶ እንዳያከናውን እያደረገ መሆኑን አንስታለች፡፡
ወጣቶች በሚሰሟቸው የሀሰት መረጃዎች ሊደናገሩ እንደማይገባ ገልጻ÷ ከየትኛውም አካል የሚመጣን
መረጃ በምክንያታዊነት ማጣራት እንዳለባቸውም ነው ያስረዳችው፡፡
በመሆኑም ወጣቶች ሰላም በማስጠበቅ የልማት ተጠቃሚ ለመሆን በኃላፊነት መስራት እንዳለባቸው
ጥሪ ቀርቧል፡፡