በሀገር ላይ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥም ጠንክሮ ሰርቶ በማለፍ የብልጽግና ጉዞን ማስቀጠል ይገባል-ዶ/ር አለሙ ስሜ
በፌዴራል ተቋማት ላሉ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች “አቅምን በህብረት፣ ፈተናን በስኬት” በሚል ሰነድ ላይ ለተከታታይ ሶስት ቀናት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል፡፡
በሀገር ላይ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥም ጠንክሮ ሰርቶ በማለፍ የብልጽግና ጉዞን ለማስቀጠል ርብርብ ማድረግ ይገባል ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት ፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር አለሙ ስሜ ተናገሩ፡፡
ዶ/ር አለሙ አያይዘውም አገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ፓርቲው የጀመራቸውን የሠላም፣ የዴሞክራሲ እና የልማት መንገዶችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡
ሀገሪቱ ፈተናዎችን ተቋቁማ ያገኘቻቸው ድሎች በልማት፣ በሀገራዊ ምክክር ፣በሀገረ መንግስት ግንባታና በቀጣይ መተኮር ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ማድረግ ተችሏልም ብለዋል፡፡
የለውጡ ሀይል ወደፊት ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት፣ ስኬታማ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ እና በምርጫ የህዝብን ይሁኝታ ማግኘቱን የገለጹት የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ ናቸው፡፡
አቶ ተስፋዬ አያይዘውም ብልፅግና የሚመራው መንግስት ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት እያደረገ ያለው ጥረት እጅግ የሚበረታታ እንደሆነ ጠቅሰው መሠረታዊ የፖለቲካ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደ አንድ መሰረታዊ ቁልፍ የሚወሰደውን የሀገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲሆን መስራት ይገባል ብለዋል።
በተቋማት ላይ የተሰሩ የሪፎርም ስራዎች እና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ማነቆ የሆኑ የህግ ማዕቀፎችን በማሻሽል በኩል የተሰሩ የሪፎርም ስራዎች የሀገራችንን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫ ነው ብለዋል አቶ ተስፋዬ፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በኢትዮጵያ ስር እየሰደደ የመጣው የፖለቲካ ገበያ ግንባር ቀደም ፈተና ሲሆን አክራሪነት እና ፅንፈኝነት የወለደው ግጭትና ጦርነት አገራችን ለጀመረችው የለውጥ ጉዞ ፈተና መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው ከችግሮች በመማር በሀገሪቱ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን ለማስቀጠልና ብልጽግናን ለማረጋገጥ አቅማቸውን እንዳጎለበተላቸው የተናገሩት ሰልጣኞቹ ችግሮችን በድል ለመሻገር በጋራ እንቆማለን በሚል የጋራ መግባባት የስልጠና መድረኩ ተቋጭቷል።