You are currently viewing እንደ ብልጽግና ፓርቲ እምነት…

እንደ ብልጽግና ፓርቲ እምነት…

  • Post comments:0 Comments

እንደ ብልጽግና ፓርቲ እምነት፣ በፌዴራል ስርዓት ዜጎች በማንነታቸው ኮርተውና ስለ አገራቸው በልበ ሙሉነት ተባብረው የሚሰሩበት እንጂ፤ በወዳጅና ጠላትነት ላይ ባጠነጠነ ትርክት እርስ በርሳቸው እንዲጋጩ፣ ለማንነት በእጅጉ ከፍ ያለ ግምት በመስጠት አገራዊ ማንነት ላይ የጎላ ጥላቻ እንዲፈጥሩ የማድረጊያ ስርዓት አይደለም፡፡

የፌዴራል ሥርዓት፣ ዜጎች ራሳቸውን በራሳቸው፣ የጋራ አገራቸውንም በጋራ የሚያስተዳድሩበት እንጂ፤ በእኔ አውቅልሃለው የሞግዚት ልጅነት ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ፤ በጋራ አገራቸው ውስጥ ባይተዋር ተደርገው እንዲኖሩ የሚደረግበት ሥርዓት አይደለም፡፡

የፌዴራል ሥርዓት አንዱ ስለ አገሩ የሚያውቅና የሚታመን፣ ሌላው ስለአገሩ ግድ የሌለው ተደርጎ እንደ ጠላት የሚታይበት ሳይሆን፤ ሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች ስለ አገራቸው እኩል ግድ የሚሰጣቸው፣ በአገራቸውም ተመጣጣኝ ውክልና ሊኖራቸው እና በራሳቸውም ሆነ በአገራቸው ጉዳይ በባለቤትነት ወሳኞች የሚሆኑበት ሥርዓት ነው፡፡

ብልጽግናም እውነተኛ ፌዴራሊዝምን እውን ለማድረግ ላለፉት አራት ዓመታት ተኩል የሰራው እነዚህን መሰል ህጸጾች ለማስወገድ ነው፡፡ ከዚህ መሰረታዊ እውነታ በመነሳት በለውጡ ማግስት ሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል የታቀፉበት፣ ሁሉም እኩል የሚበለጽጉበት የፌዴራል ስርዓት መገንባት የጀመረ ሲሆን፤ በዚህም የህዝብ ጥያቄዎችን መመለስ ችሏል፡፡

በፌዴራል ሥርዓቱ የክልሎች ቁጥር አስራ አንድ መድረስም የዚህ ስራው አንድ ማሳያ ሲሆን፤ ሌሎች ለመመለስ በሂደት ላይ ያሉም በርካታ የህዝብ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ይህ ደግሞ ብልጽግና ፓርቲ በዴሞክራሲ ልምምድ ውስጥ እውነተኛ ፌዴራሊዝንም ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበትና ተግባራዊ ምላሽም ያረጋገጠበት ሲሆን፤ ይሄንኑ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ይሄን መሰል ስራ ስኬታማ ለማድረግ ደግሞ የዴሞክራሲ ሥርዓትንና የተቋማት ግንባታን እውን ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ብልጽግና ፓርቲ ይሄን ተገንዝቦ የዴሞክራሲ ስርዓቱንም ሆነ ዘመን ተሻጋሪ እና ከፓርቲ ይልቅ ኢትዮጵያን የሚመስሉ ተቋማትን የመገንባት ሂደቱን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ምላሽ ይስጡ