You are currently viewing ሰላም የአሸናፊዎች ምርጫ ነው

ሰላም የአሸናፊዎች ምርጫ ነው

  • Post comments:0 Comments
ሰላም የአሸናፊዎች ምርጫ ነው፡፡ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው ፡፡ በሰላም እጦት ምክንያት ለበርካታ አስርት አመታት የኢትዮጵያ ህዝብ የተጎዳና የተጎሳቆለ ህዝብ ነው፡፡ በባለፉት የአገዛዝ ዘመናት እጆቻችን ወደ ጦርነት እንጅ ወደ ልማት ባለመዘርጋታቸው ጥንት ከነበርንበት የስልጣኔ ማማ ተንከባለን ወርደን የድህነት ቅርቃር ውስጥ መግባታችንን ልንክደው የማንችለው የገሀዱ አለም እውነታ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣውን ሰላምን ብቻ ባለመከተላችን ነው፡፡
ሰላም ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡ ጦርነት አንድም ጊዜ መፍትሄ ሆኖ አያውቅም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ የእርስበርስ ውጊያዎች ተካሂደዋል፡፡ በእነዚህ የእረስበርስ ጦርነት ውስጥ ምንም አይነት አወንታዊ ውጤት ተመዝግቦበት አያውቅም፡፡ በእርስበርስ ጦርነት የሚፈታ የፖለቲካ ችግርም የለም፡፡ የሚያኮሩን ታሪኮች ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር ብቻ ያደረግናቸው ጦርነት እንጅ እርስበርስ ያደረገናቸው ውጊያዎች አይደሉም፡፡
ሰላም ከሌለ ለዘመናት የተገነቡ የስልጣኔ አሻራዎች በሰዓታት ወይም ከዚያም ባነሰ ጊዜ ውስጥ ዶግ አመድ ሲሆኑ በአገር ልጆች አለመግባባት ሰማይ በባሩድ ጭስ ሲታጠን፣ ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች ሲጋዩ፣መሰረተ ልማት ሲወድም፣በሰላም ወጥቶ መግባት አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ዜጎች ሰላማዊ ህይወትን ፍለጋ ድንበርና ባህርን ለማቋረጥ ሲሰቃዩ ሰላም በዋጋ ሊተመን የማይችል ውድ ሀብትና ሁላችንም በጋራ ልንቆምለት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
የአገራችን የርሀብና እርዛት እንዲሁም ኋላ ቀርነት ተምሳሌት ሊፋቅ የሚችለው የሰላም አየር እየተነፈስን፤የኢትዮጵያን ከፍታ እያሰብን በጋራ በልማት ጎዳና መትመም ስንችል ነው፡፡ ሁሌም ቀውስ መለያው በሆነው የአፍሪካ ቀንድ መገኘታን በሰላማችን ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ቀላል ባይሆንም ለሰላም መደፍረስ መንስኤ የሆኑ ውስጣዊ ችግሮችን በመፍታት ላይ በትኩረት በመስራት ከአገራችን አልፎ የአፍሪካ የሰላም ዘብ መሆን እንችላለን፡፡
ዛሬ የሰፈነው ሰላም ነገም በአስተማማኝ ደረጃ ሊቀጥል የሚችለው ሁሉም ለሰላም ተግቶ ሲሰራና ሰላምን የሚያፈርሱ ነገሮችን ያለ ምህረት ሲታገል ብቻ ነው፡፡እውቁ ማህተመ ጋንዲ በአንድ ወቅት እንዳሉት ‹‹ስለ ሰላም ማውራት በቂ አይደለም፡፡ አንድ ሰው በሰላም ማመን አለበት፡፡ ማመን ብቻ ደግሞ በቂ አይደለም ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ግድ ይላል፡፡›› ሲሉ ሁላችንም ስለ ሰላም ዘብ መቆምና ተግባራዊ ማድርግን እንዳለብን መክረዋል፡፡
ትናንት በአስተማማኝ ሰላም ላይ የነበሩ ሀገሮች ዛሬ ሰላማቸው ደፍርሶ ዜጎቻቸው ሰርቶ መኖርን ይቅርና በህይወት ለመቆየት እንኳ ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡ለዚህም ሶሪያ፣ሊቢያና የመንን እንደምሳሌነት መመልከት ይቻላል፡፡
በሀገራችን ሰላምና ሰላማዊ ሁኔታ ጠብቀን ማስቀጠል ከቻልን ወቅታዊ ችግሮቻችን ብቻ ሳይሆን ተብትቦ ከያዘን ድህናትና ኋላቀርነትም ለዘለቄታው መላቀቅ እንችላለን፡፡ ሰላም ከሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሀገራችንን ራእይ እውን ማድረግ እንደምንችል መገመት አያዳግትም፡፡
ስለ ሰላም እንዘምር ስለተግባራዊነቱ ሁላችንም እንቀሳቀስ!

ምላሽ ይስጡ