ዛሬ የቆምነው ለእኛ ሲሉ የግፍ ጽዋን በተጎነጩ ጀግኖቻችን አጥንት ላይ ነው፤

ዛሬ የቆምነው ለእኛ ሲሉ የግፍ ጽዋን በተጎነጩ ጀግኖቻችን አጥንት ላይ ነው፤

  • Post comments:0 Comments

የፌዴራል መንግስቱ በህወሓት ኃይሎች ላይ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ያዘዙት በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ እንደሆነ አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር ናት፡፡ ልባም ልጆችዋ አጥር ሆነው የጋረዷት፣ ዋጋ ከፍለው ያደመቋት፣ ተቆጥሮ በማያልቅ መሥዋዕትነት ታፍራና ተከብራ የኖረች ሀገር ናት፡፡ የሩቁ ቢዘነጋን እንኳን፣ ጥቅምት 24/2013 ምሽት ላይ ግፍ የተፈጸመባቸው ጀግኖቻችን ታሪክ ፈጽሞ የሚረሳ አይደለም፡፡

እያንዳንዳችን የጀግኖቹ ዕዳ አለብን፡፡ ዛሬ የቆምነው ለእኛ ሲሉ የግፍ ጽዋን በተጎነጩ ጀግኖቻችን አጥንት ላይ ነው፡፡ እነዚያ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች “ከወገኔ በፊት እኔ ልቅደም” ብለው ደማቸውን ለአፈር፣ ሥጋቸውን ለአሞራ ባይሰጡ ኖሮ የዛሬው ቀን ዛሬን ባልመሰለ ነበር፡፡

የሰሜን ዕዝ ሠራዊት የተደራጀው ከአንድ አካባቢ አልነበረም፡፡ አማራና ኦሮሞው፣ ሲዳማና ወላይታው፣ አፋርና ጋምቤላው፣ ጉራጌና ሐድያው ከሁሉም ብሔር ተውጣጥቶ ሀገር እንዲጠብቅ የተደራጀ ሠራዊት ነበር፡፡ ሀገሬን ብሎ ለሃያ ዓመታት ከቤቱና ካሳደገው ቀዬ ተነጥሎ ዱር እያደረ ድንበር ሲጠብቅ ኖሯል፡፡

ሠራዊቱ ለትግራይ ክልልና ለሕዝቡ ከደግነት ውጭ ክፉ ሆኖ አያውቅም። ጠላት ሲመጣ የሚመክት፣ አዝመራ ሲደርስ የሚያጭድ፣ በማኅበረሰባዊ ተግባራት ላይ የሚካፈል ነበር። በደምና በላቡ ለከፈለው ደግነት በምላሹ ከሽብር ቡድኑ ሕወሐት የተቀበለው ክህደት ነው።

ኢትዮጵያን ለመውረር የመጡ ጠላቶች እንደ ሽብር ቡድኑ ዋነኛ የጦር ቤዛችንን በመደብደብ አልጀመሩም፡፡ ዋና ዋና መኮንኖችን በመግደልና ከባድ መሣሪያዎቻችንን ዘርፈው አልተነሡም። የጦርነት ቅዱስ ባይኖርም ለጭካኔም ልክ አለው። በሽብር ቡድኑ ልክ ኢትዮጵያ ላይ የጨከነ የለም፡፡

ጥቅምት 24 ሠራዊቱ ላይ የክህደት ጥቃት ሲፈጸም የሞቱት እነዚያ ጀግኖች ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ እንደመሆናቸው የተፈጸመባቸው ግፍ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመ ግፍ ነው።

የሽብር ቡድኑ በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት መሣሪያ ለመዝረፍ ብቻ የተደረገ ተራ ጥቃት አልነበረም፡፡ በተንኮል የተቀመመና በክፋት የሞላ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡ የገዛ ጓዶቹን አስኮብልሎ በተኛበት ከመግደል ባለፈ ከሬሳው ላይ ልብሱን ገፍፎ የአውሬ ቀለብ እንዲሆን እርቃኑን ሜዳ ላይ ጥሎታል። ይኼን ሲያደርግ የሽብር ቡድኑ ዓላማ ሁለት ነው፡፡

አንደኛ ሠራዊቱ በሐፍረት በትር እየተቀጣ ሞራሉ እንዲላሽቅና የአቅመ ቢስነት ስሜት እንዲሰማው፡፡ ሁለተኛ ሠራዊቱ እርስ በእርስ እንዳይተማመንና “ክፉና ደጉን አብሮ ከተካፈሉኝ ጓዶቼ እንደዚህ ዓይነት ነውር ዛሬ ከተፈጸመብኝ ነገስ?” ብሎ እንዲጠራጠር ለማድረግ ታስቦ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ሠራዊቱ እንደተጠበቀው አልሆነም፡፡

የወንድሞቹ ደም በከንቱ መፍሰስ ያንገበገበው ሠራዊት በፍጥነት ራሱን አደራጅቶ በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የሽብር ቡድኑ ያደራጀውን ኃይል ወደ በርሃ እንዲበተን ማድረግ ችሏል፡፡ የቡድኑን ቁንጮ አመራሮች አብዛኞቹን ይዞ ለሕግ አስረክቧል፡፡ የተፈጸመበትን ክህደት በበቀል ሒሳብ ሳይሆን የሕግ ማስከበር መርሕን በተከተለ መንገድ ሲያከናውን ነበር፡፡ በጦርነት ውስጥ ለመርሕ መገዛት ቀላል አይደለም፡፡

ሠራዊታችን ባለፈው ሁለት ዓመት ውስጥ ከሽብር ቡድኑ ጋር አያሌ ውጊያዎችን ሲያደርግ ብዙ ዋጋ ከፍሏል፡፡ በየጦር ውሎው በጀግንነት እየተዋጋ ለእናት ሀገሩ ተሠውቷል፡፡ ለሀገርና ለወገን ያለውን አጋርነት በንግግር ሳይሆን በተግባር አሳይቷል፡፡ ምንጊዜም ለእናት አገሩ ሲል ሰራዊቱ በዱር በገደሉ መዋደቁ አይቀሬ ነው፡፡በግፍ የተሠውት የሰሜን ዕዝ አባላትን ጨምሮ ለሀገር የተዋደቁ ጀግኖች ስማቸው በወርቅ ይጻፋል፡፡

#prosperity

Leave a Reply