ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሰው አረንጓዴ… /በሚራክል እውነቱ/

ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሰው አረንጓዴ… /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም ለቀጣይ ትውልድ መሰረት የሚሆን ትልቅ ፕሮጀክት እንደሆነ ተናግረዋል። የችግኝ ተከላው ከማንም በላይ በደን መመናመን ሳቢያ ክፉኛ እየታመመች ለምትገኘው ሀገራችን ፍቱን መድሃኒት ነው።
እንደሚታወቀው የሀገራችን የደን ሽፋን ከ40 በመቶ ወደ 3 በመቶ ዝቅ ያለበት ሁኔታ ነበር። በዶ/ር ዐብይ አህመድ አነሳሽነት ህዝቡን በማስተባበር የጭግኝ ተከላና ደን ልማት ላይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ባከናወነቻቸው ተጨባጭ ተግባሮች ይህን አሃዝ 17.2 በመቶ ከፍ ማድረግ ችላለች።
የችግኝ ተከላው ትርጉም ብዙ ነው። የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣የደን መመናመን እና የመሳሳሉት ዓለማችንን ለካርቦን ልቀት እየዳረጓት ባለበት በዚህ ዘመን ከዚህ ችግር ለመውጣት ሁነኛው መፍትሔ የችግኝ ተከላ እንደሆነ የዘርፉ ሳይንቲስቶች ይናገራሉ።
ሀገራችን ባለፉት ዓመታት በቢሊዬን የሚቆጠሩ ችግኞችን በአንድ ጀምበር በመትከል የራሷን አስተዋጾኦ ከማበርከቷም በተጨማሪ እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን ዓለምን ከካርቦን ልቀት ለመታደግ ለተያዘው ዓለም አቀፍ ጥረትም ጉልህ ፋይዳ አበርክታለች፡፡
በህብረተሰቡ ዘንድ ለዛፎች ልዩ ክብር እንደሚሰጥ ሊቃውንት ስለዛፍ ከተነገሩ ቁምነገሮች መረዳት ይቻላል፡፡ የሥነ ሕይወት ባለሙያው ፕሮፌሰር ለገሠ ነጋሽ በአንድ ወቅት ካጠናቀሩት መካከል አንደኛው እንዲህ ይላል“ሠርግ ደግስ ደስታህ ያንድ ቀን ነው፣ ተሾም ተሸለም፣ ደስታህ ያንድ ወር ነው፣ ዛፍ ትከል ደስታህ የዕድሜ ልክ ነው፡፡“ከዚህ መረዳት የሚቻለው ማህበረሰቡ ለዛፍ ያለውን በጎ አመለካከትን ነው፡፡
ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አህመድ በ2013 ዓ/ም በተካሄደው ሶስተኛው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር መጀመሩን አስመልክተው በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው እንዲህ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የኢትዮጵያውያን ሕይወት ከዛፎች እና ከጫካ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው፡፡
በ2011 የአካባቢን ብክለትና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ለመቅረፍ አስበን የአራት ዓመት ዕቅድ በማውጣት ያቀረብነው ሀገራዊ ጥሪ አንድ አካል ነው፡፡በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የምግብ ዋስትናን ያለማረጋገጥ፣ አካባቢ ተኮር ግጭቶች እና የመሳሰሉ አሉታዊ ሁኔታዎችን የመከላከያ መንገዱ በእጃችን ነው፡፡
ለመላው ኢትዮጵያውያን “ኢትዮጵያን እናልብሳት” ብዬ ጥሪ አቀርባለሁ። ጥሪው ሀገራችንን አረንጓዴ እናልብስ፣ በክልል ፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት፣ በጾታ ከመከፋፈል አልፈን፣ ለዚህ ታላቅ ሕዝብ በሚመጥን መልኩ፣ ኢትዮጵያችንን በብልጽግና እና በክብር በአንድነት የተፈጥሮ ልብሷን እናልብሳት በማለት መልዕክታቸውን ለኢትዮጵያዊያን አስተላልፈዋል።
የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ የአረንጓዴ አሻራ ብሄራዊ ጥሪ ሁሉን ገዢ ሃሳብ በመሆኑ በርካቶች ተቀባብለውታል፡፡
ከአካባቢ ፅዳትና ውበት፤ በተለይም ዓለምን እያስጨነቀ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ዛፍ የመትከል ጉዳይ የሚታለፍ አይሆንም። ኢትዮጵያም የዓለምን ችግር ለመፍታት የራሷን ድርሻ እየተወጣች መሆኗ ሊያስመሰግናት ይገባል።
ህዝቡም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ከዚህ ቀደም ባሉት ዓመታት እንዳሳዬው ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
ዛፍ መትከል የህይወት አካል መሆኑ ብዙዎችን የሚያስማማ ጉዳይ ቢሆንም ተገቢውን ትኩረት ግን አላገኘም ማለት ይቻላል።የሰው ልጅ ዛፍ ሊተክልና በዛፍ ሊጠቀም የተፈቀደለት ፍጡር እንጂ ፀረ- ዛፍ ይሆን ዘንድ በፍፁም አልተፈጠረም። ይህን ሁሉም ሰው ልብ ሊለው የሚገባ ጉዳይ ነው፤ለመጪው ለትውልድ ማሰብ ግዴታ ነው።
ለአራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ በሀገር አቀፍ ደረጃ 7.6 ቢሊየን ችግኝ በያዝነው ዓመት መጨረሻ ድረስ እንደሚተከል ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ስለሆነም ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ የተዘጋጁትን ችግኞች በህብረት መትከል ይገባዋል፡፡
ከመትከል ቀጥሎ ያለው ዋናው ነገር የተከሉትን መጠበቅና ለአቅመ ዛፍ ደረጃ እስኪደርሱ መንከባከብ አስፈላጊ መሆኑን አለመዘንጋት ነው። እስከ ዛሬም ያለው ችግር የመትከል ሳይሆን የማፅደቅና ማሳደግ ጉድለት መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡

Leave a Reply