You are currently viewing የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የብልጽግና ዕይታ  /በሚራክል እውነቱ/

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የብልጽግና ዕይታ /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments

በጠረጴዛ ዙሪያ ሰክኖ ለችግሮች ሰላማዊ መፍትሔ ማመንጨት ከዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫዎች ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ስርዓት የብዙሃንን አስተሳሰብ የሚያራምድ እንደሆነ መረዳት አዳጋች አይሆንም፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በመርህ ደረጃ የብዙሃንን አሠራር መቀበል ማለት ነውና፡፡ በብዙሃን ህግ የሚከናወን ማንኛውም አሠራርን ደግሞ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊም፤ግድም ።

ከዚህ ውጪ ከሆነ ግን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጠላት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የግለሰብ ፍላጎትና አስተሳሰብን መሰረት ያደረገ አካሄድም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት ነው፡፡ በመሆኑም በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው በሰዎችና በንብረቶቻቸው ላይ የሚደርሰው ጥቃትና እንግልት ከብዙሃን ፍላጎት ይልቅ የግለሰብ ፍላጎት ጎልቶ የታየበት ክስተት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሀሳብ ሀብት ነው፤በሀሳብ ውስጥ ሰላም፣መተሳሰብ፤መከባበር፣አንድነት፣አጋርነት እንዲሁም ብልጽግና አለ፤ይህ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡የሁሉም ነገር መነሻዎች የሰዎች ሀሳብ ነው፡፡ሰዎች ፈጣሪ በሰጣቸው አዕምሮ ተጠቅመው መልካም ነገሮችን ማፍለቅና ማምረት ሲጀምሩ ከእነሱ አልፈው ለህዝብና ለሀገር ጠቃሚ ሀሳቦችን ወደ ተግባር ይቀይራሉ፤በተቃራኒው ከፈጣሪው የተቸረውን አዕምሮ መጠቀም ያልቻለ ደግሞ ለተንኮልና ከሰውነት ዝቅ ላሉ ማንነቶችና ይዘዋቸው ለሚመጡ ድርጊቶች ይጋለጣሉ፡፡

ብልጽግና ፓርቲ በመሰረታዊነት ከሚታገልባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ መሰረታዊ የሆነው ነገር ደግሞ አንዱ የሃሳብ ልዩነቶችን በመቻቻል ማስተናገድ ነው፡፡

ብልፅግና በሀሳብ ልዕልና የሚያምን ፓርቲ ስለሆነ ብቻ አይደለም ለዲሞክራሲ ትኩረት የሚሰጠው፤ይልቁንም በሀሳብ ፍጭት ውስጥ የዳበረና ለሀገር ብልጽግና የሚጠቅም ውጤት ስለሚገኝ እንዲሁም ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለመንግሥት ቁመና የሚመጥን አስተሳሰብ ማዳበር ላይ ክፍተት መኖሩን ስለሚረዳ እንጂ፡፡

በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሃሳብ ልዩነቶች ፀጋ እንጂ እክል እንዳልሆኑ ብልጽግና ፓርቲ ከልብ ይረዳል፡፡ ለመሆኑ ምን ያህሎቻችን የሃሳብ ልዩነቶችን ባለማክበራችን የተነሳ በዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ላይ መግባባት እንዳይፈጠር እንቅፋት እንደሆነ እንረዳ ይሆን? መልሱን ለእናንተው ትቼ እኔ ግን እላለሁ ምንም እንኳ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም የሀሳብ ልዩነቶችን በሚፈለገው ደረጃ ማስተናገድ ስላለተቻለ እንደ ሀገር የሃሳብ ብዝሃነትን ማራመድ አልተቻለም፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በሀሳብ ልዕልና ወይም በዴምክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል ለማለት  ቢከብድም ሁሉም ሰው የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት፣ ልማትና ዕድገት፣ብልጽግናና አንድነቷ የጠነከረ ሀገር ይፈልጋል፤ነገር ግን የጋራ ሃሳብ ከሌለና ሁሉም በየግሉ የሚሮጥ ከሆነ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባት የሚኖረው አበርክቶ ቅንጣት ይሆናል፡፡ የጋራ መግባባት የሌለበት ማንኛውም እንቅስቃሴና ዕርምጃ ደግሞ ውጤቱ የከፋ ነው፤ አሉታዊ ጎኑ ያመዝንና አገሪቱን ሌላ ችግር ውስጥ ይከታታል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት በመንግሥት በኩል የተወሰዱ ዕርምጃዎችን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ የፖለቲካ እስረኞችን ከእስር በመፍታት፣በውጭ ይኖሩ የነበሩትንም ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ፣ሀሳብን በነጻነት የመግለጽና ሌሎችም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማጠናከር የተወሰዱ ዕርምጃዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ብልጽግና አሁን አሁን እያበበ የመጣውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በሚፈለገው ደረጃ እስኪያድግ ድረስ መከታተል የዕለት ተዕለት ስራው ሆኗል ማለት ነው፡፡

ለዴሚክራሲያዊ ሥርአት ግንባታ የሚተጋና በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመቅረጽ በሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተቀርጾ ተግባራዊ እየሆነ ያለውን የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርትና እያስከተለ ያለውን ውጤት ቆም ብሎ መመዘን የግድ ይላል፡፡

ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች፣የዘርፉ ምሁራን፣አነቃቂዎች ሌሎችም አካላት በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ለነገ የማይባል ስራ ነው፤ ይህ ካልሆነ ግን ለሁሉም እጅግ ፈተና ይሆናል። ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውጪ ሌላ ምርጫ ሊኖር እንደማይገባ ሁሉም ወገን ተገንዝቦ ስርዓቱን ወደሚፈለገው ደረጃ ማሻገር ለነገ የሚተው ሥራ አይደለም፡፡

ምላሽ ይስጡ