You are currently viewing ከስሜት ሀገርን እናስቀድም  /በሚራክል እውነቱ/

ከስሜት ሀገርን እናስቀድም /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments

የአመራር ለውጥ በዴሞክራሲያዊ አግባብ ከተደረገበት ጊዜ ወዲህ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ለውጥ ስለመፈጠሩ ጥርጥር የለውም፡፡ይሄው የለውጥ እርምጃ በሀገር ደረጃ ያሳየው የተስፋ ብርሃን በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ መነቃቃትን ከመፍጠር ባሻገር ለዓመታት ተገፋፍተው የኖሩ ወገኖች እንዲቀራረቡ ምክንያት ሆኗል፡፡

ፍቅርና ይቅርታ፣ ዕርቅና ሰላም፣ መግባባትና አንድነት የሚሉትን የለውጡ  ሐሳቦች በጉልህ ማስተጋባትና ወደ ተግባር በመቀየር ውጤት እንዲመጣ ማስቻል በለውጡ ሂደት ውስጥ ያየናቸው ደማቅ ምስሎች ናቸው፡፡ ሃገራዊ ለውጡን ወደሚፈለገው ከፍታ እንዲደርስ ደግሞ የመላው ኢትዮጵያዊያን ርብርብ እጅግ የላቀ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ለውጡ በሁሉም መስኮች የታሰበለትን ዓላማ ማሳካት እንዲችል ልዩነቶቻችንን በይደር አስቀምጠን መቅደም የሚገባቸውን ሃገራዊ አጀንዳዎች አስቀድመን፣ በጠረንጴዛ ዙሪያ በሰከነ መንፈስ፣ከግል ስሜትና ፅንፍ ከወጣ ብሔርተኝነት ወጥተን የመፍትሔ ባለቤቶች መሆናችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ የምንጠብቀው አገራዊ ለውጥ ተግዳሮቶችን ተሻግሮ እና ተሳክቶ ለማዬት እንድንችል ከጅምሩ የለውጡን ምንነት፤ ባህሪያት፤ እንዲሁም መዳረሻችን የት ነው የሚለውን ወደኋላ መለስ ብሎ በወጉ መረዳት ይገባል፡፡

ኢትዮጵያዊነትና ጽንፍ የወጣ ብሄርተኝነት በሁለት አፅናፍ ላይ ቆመው በሚጓተቱበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን የምንፈልገውን አገራዊ ለውጥ ማምጣት ያስቸግራል፡፡ከግል ስሜቶቻችን ወጥተን አገርን ማስቀደም ብልህነት ነው፡፡አገር የሁሉም ነገር መሰረት ናትና፡፡

የዛሬ አራት ዓመት አንድ ብለን የጀመርነው ለውጥ የሃገራችንን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ የላቀ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ እንድትሸጋገር ድልድይ ሆኖናል፤በመግባባት ላይ የተመሰረት የሃገራዊ አንድነት ግንባታ በመፍጠር አገራችንን ከብሄር ፅንፈኝነት አደጋ ማዳን መቻል የለውጡ ሌላው ግብ ነው፡፡

ሃገራችንን ከህገ ወጥ አሰራሮችና ተግባራት በመታደግ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ መቻል አገራችንን ከማያባራ ቀውስ በመታደግ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ በህዝባችንና አመራሩ ዘንድ የአመለካከት፤ የአስተሳሰብና የአካሄድ፤ እንዲሁም የአሰራርና መዋቅር መስተጋብር በመፍጠር አኮኖሚውን ከተፋዘዘበት ወደ መነቃቃት ማሻገር መቻል ለውጡ ይዟቸው የተነሳው ዓላማዎች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያዊያን ከለውጡ የሚጠብቋቸው ተስፋዎች በርካቶች ናቸው፤ሃገራችን ሰላሟ የተረጋገጠ፤ የበለፀገች፤ ህዝቦቿ በመግባባት የሚኖሩባት፣መተሳሰብ የጎለበተበት፣ ሃገራቸውን በላባቸው ገንብተው እና ለትውልድ ለማስረከብ የሚጥሩ ወጣቶች በዝተው የሚታዩባት እንዲሁም የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት አገር እንድትሆን ህዝቦቿ አብዝተው ይሻሉ፡፡

ዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውረው በነጻነት የሚሰሩበት፤ ሃብት የሚያፈሩበትና የተደላደለ ኑሮ የሚገነቡበት ሁኔታ እንዲፈጠር፤ በፀጥታ እጦት እና በአሻጥር ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረው ኢኮኖሚ አሁን ካለበት ደረጃ ይበልጥ እንዲሻሻል፣ ተምሮ ስራ አጥ የሆነው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት የልማቱ ተሳታፊ እና ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ለአገር ሰላምና ደህንነት ከፍተኛ ሚናውን ይወጣል፡፡

ሆኖም ግን አገራዊ ለውጡን እየፈተኑ ያሉ በርካታ ተግዳሮቶችን በጋራ መሻገር ይኖርብናል፡፡በለውጡ ምንነትና ሂደት ላይ በአመራሮች፤አባላትና ደጋፊዎች መካከል የጋራ እሴት አለመኖር በፓርቲው ውስጥ እንደ አንድ ተግዳሮት ሆኖ መገለፁ ይታወሳል፡፡

የብሔር ፖለቲካ ነጋዴነት አዝማሚያ (አክራሪ ብሄርተኝነት)  ፣የግጭት ፖለቲካን ሥልጣን ለመያዝ እንደሥልት የመጠቀም አዝማሚያ፣ ሃገራዊ አንድነትንና ብሔራዊ ማንነትን ማጠናከር ላይ ያለውን ሚዛን አለመጠበቅ፣  ዴሞክራሲያዊ አንድነት የሚያመጡ ስራዎች ላይ ያለው መዛነፍ፣ ዕለት ከዕለት እየባሱ የመጡ ብልሹ አሰራሮች፣ ሌብነት፣ መልካም አስተዳደር ችግሮች ዘረፋና የመሳሰሉት ችግሮች ለውጡ የሚፈለገውን ያህል ዕድገት እንዳያመጣ እንቅፋት ሆነውታል ማለት ይቻላል፡፡

ስለሆነም የስራ አጥነት ችግር ፤የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ እና ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ ፓርቲው ራሱን መፈተሽና እና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ሊፈጠር ይገባል ባይ ነኝ፡፡ በድርጅት እና በአመራር መካከል ሊኖር በሚገባዉ የጋራ እሴት ላይ ትርጉም ያለዉ ስራ መስራት ያስፈልጋል ፡፡

ይህን ማድረግ ሲቻል ወጣቱ ስለ አገራዊ ወቅታዊ ሁኔታው የተስተካከለ አመለካከትና ግንዛቤ እንዲጨብጥ ከተደረገ፣ በወጣቱ ዘንድ ለሚታዩ ችግሮች ራሱን ዋነኛ ችግር ፈቺ ኃይል መሆኑን ማስረዳት ከተቻለ፣ ወጣቱ በስሜታዊነት ከመነሳት በምክንያት የመደገፍና  የመቃወም ደረጃ እንዲደርስ ከተሰራ፣ በተለይም የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሙ በከፍተኛ ጥንቃቄና የኃላፊነት መንፈስ እንዲመራ ከተደረገ ተግዳሮቶቻችንን ተሻግረን የተጀመረዉን ለዉጥ በተገቢዉ ሁኔታ ለማስቀጠል ያስችለናል እላለሁ፡፡

ምላሽ ይስጡ