You are currently viewing ጥላቻን በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር ልናሸንፈው ይገባል፤  /በሚራክል እውነቱ/

ጥላቻን በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር ልናሸንፈው ይገባል፤ /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments

የኢትዮጵያ ሰላም፣ፍቅርና አንድነት በልጆቿ መዳፍ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ይህ ከሆነ ታዲያ ምን ያህሎቻችን በሰከነ አዕምሯችን ተረድተነው ይሆን? እስኪ ወደ ራሳችን ተመልሰን ከልብ እናጢነው፡፡ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ብዙዎቻችን ግን ከተራ ትርጉም በዘለለ ሀያልነታቸውን አስበነው አናውቅም፡፡የዚህ ትርጉም  በጥልቀት መረዳት የሚችሉት እንደነ ሶሪያ፣ሊቢያ፣የመንና በቅርቡ ሰላሟ እንደራቃት እንደ ጎረቤታችን ሱዳን የመሳሰሉት ሀገራት ናቸው፡፡

ሀገር በእልህ ሳይሆን በጥበብ፣በንግግር ሳይሆን በተግባር፣በዘልማድ ሳይሆን በዕውቀት፣በጥድፊያ ሳይሆን በእርጋታ ነው ልትመራ የምትችለው፡፡ነገር ግን ምርጫችን ከዚህ በተቃራኒው በመሆኑ ምክንያት ሀገሪቱ አይታው በማታውቀው ሁኔታ ብሔርንና ማንነትን መሰረት በማድረግ አንዱ አካባቢ በሌላው አካባቢ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ክብራቸውንና ማንነታቸውን በሚያጎድፍ መልኩ ዘለፋ፣ ፉከራና አጉል ጀብደኝነት በቃላትና በምስል አስደግፈው በዘመን አመጣሹ ፌስ ቡክ፣ቲዊተርና በሌሎችም የመገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት ሲለጥፉት የሚስተዋለው፡፡

ታዋቂው የጥቁሮች ሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲል መናገሩ ይታወቃል፤ “Darkness cannot drive out darkness; only light can do that. Hate cannot drive out hate; only love can do that”. ጨለማን በጨለማ ሳይሆን በብርሀን፤ ጥላቻንም በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር ልንቀይረው እንደሚገባን ያሳየናል፡፡ ታዲያ እውነታው ይህ ከሆነ እኛ እየሆን ያለነው የትኛውን ነው? ጥላቻን በጥላቻ ወይስ ጥላቻን በፍቅር? ማንም ሊረዳው የሚገባው እውነታ ግን ጥላቻ የበለጠ ሰውን ከሰው እያራራቀ ወዳልተፈለገ መንገድ ይመራል እንጂ ሰላምና አንድነትን ከቶውንም ቢሆን አምጥቶ አያውቅም፡፡

ስለዚህ በሰዎች ዘንድ የቱንም ያህል ክብራችንን የሚነካ ማንነታችንን የሚያጠለሽ ነገር እንኳ ቢፈጠር ክፉን በክፉ መመለስ ሳይሆን መጥፎውን በደግነት ቀይረን እኛነታችንን የበለጠ በመልካምነት ልናሳይ ይገባናል፡፡ ኢትዮጵያዊነት በጊዜያዊ ተግዳሮቶች ተሸንፎ ከውድድር ውጭ መሆን ሳይሆን ያጋጠሙትን እክሎች ወደ  መልካም አጋጣሚዎች  በመቀየር ድል ማድረግ ሲቻል ነው።ከዚህ ውጭ ትርጉም ሊኖረውም አይችልም፡፡

የአብሮነትና የዘመናዊነት ተምሳሌት ኢትዮጵያ፤ ዘመናትን በስልጣኔ ማማ የነገሰች ኢትዮጵያ ፣የህዝባችን የከፍታና ኩራት መሰላል፤ እጅግ ውብ ባህል እና  የዘመን አይሽሬ እሴቶቻችን ባለቤት፤ኢትዮጵያችን የታሪክ አውድማ እና የኩሩ ህዝብ ምድር መሆኗን አለም ያወቀው ፀሀይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡

ለዚህም ነው ጥላቻና ዘረኝነትን ጉድጓድ ቀብረን በሰዎች መካከል መተሳሰብ፣ፍቅር፣አንድነትና የአብሮነት ስሜት እንዲፈጠር በማድረግ የምንሳሳላትና ከማንም በላይ ቅድሚያ ለምንሰጣት ሀገራችን ያለንን ክብርና ፍቅር በተግባር ልናሳያት ይገባል የሚባለው፡፡

ምላሽ ይስጡ