ኢትዮጵያ በአሸባሪው ህወሓት የደረሰባትን በደል ለመመከት በጀመረችው የህልውና ዘመቻ መነሻነት ኢትዮጵያ ላይ የሚወርዱ ዱላዎች ብዙ ርቀት የተሄደባቸው ናቸው፡፡ ከዚህም አልፎ “ለእድገቴ ይበጀኛል፤ ከድህነት ለመውጣት ዋነኛ አማራጬ ነው” በሚል እየገነባች ያለውን የታላቁ ህዳሴ ግድብም በአሜሪካ በኩል በማናለብኝነት ለማስቆም ያልተፈነቀለ ድንጋይ የለም፡፡ እነዚህ ሁሉ ለኢትዮጵያ ከማሰብ ሳይሆን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚደረግ ሴራ አካል ነው፡፡
በዚህ መንገድ 13 ጊዜ በኢትዮጵያ ጉዳይ ሲሰበሰብ የከረመው የፀጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያ ጉዳይ ምን ያህል እረፍት እንደነሳቸው የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ አንዴ በማዕቀብ፤ ሌላ ጊዜ በማስፈራራት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡
ሰሞኑን ደግሞ አሜሪካ ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 የተሰኙ ረቂቅ ሰነዶችን በማዘጋጀት ለማፅደቅና በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማስከተል ሌላ የእጅ አዙር በትሯን እየሰነዘረች ትገኛለች፡፡
እነዚህ ሰነዶች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ዕቃዎች ላይ፣ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በሚመጣ ማንኛውም የውጭ ምንዛሪ፣ በአጋሮቿና በራሷ በኩል በምትቆጣጠራቸው ዓለም ባንክ፣ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በኩል የሚመጡ ድጋፎች ላይ ማዕቀብ በመጣል ትልቅ ተጽዕኖ ማድረግን ዓላማ ያደረገ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡
በመሆኑም በዓለም ላይ የሚገኙ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላትና መላ ኢትዮጵያውያን ይህ ማዕቀብ እንዳይፀድቅ የጀመረውን የተቃውሞ ድምጽ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡