አገራዊ ምክክሩ አገርና ህዝብን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሻግር እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል! /ዜማ ያሬድ/

አገራዊ ምክክሩ አገርና ህዝብን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሻግር እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል! /ዜማ ያሬድ/

  • Post comments:0 Comments
አገራችን አሁን ላይ ምንድን ነው የሚያስፈልጋት የሚለውን ሁሉም ዜጋ በሰከነ መንገድ ማሰብ ይጠበቅበታል፡፡ በአገራችን ለብዙሃኑ ህዝብ እምብዛም አጀንዳ ያልሆኑ ነገር ግን በሊህቃኖቻችን መካከል በሚፈጠሩ አንዳንድ አለመግባባቶች ዳፋቸው ለህዝብ እየተረፈ ያሉ ጉዳዮች ብዙ ናቸው፡፡ ይህ አንድ ቦታ መቆም ካልቻለ ደግሞ አገራዊ ኪሳረው የበዛ እንደሚሆን የመጣንበት መንገድ በማያሻማ መልኩ አሳይቶናል፡፡ የተሳሳቱ ትርክቶችንና እርስ በእርስ ያሉ አለመግባባቶችን መፍታት የሚቻለው ደግሞ አካታች በሆነ አገራዊ ምክክር ብቻ ነው፡፡ ለዛም ነው ወቅቱን የዋጀ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ተደራጅቶ ወደ ስራ የገባው፡፡
አገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ወገን ቁርጠኝነት የሚፈልግ ነው፡፡ ህዝባችን፣ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች፣ መንግስት እና መንግስትን እየመራ ያለው ገዥ ፓርቲ አገራዊ ምክክሩ ለህዝብ በሚጠቅም መንገድ እንዲጓዝና እንዲቋጭ የራሳቸውን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በሂደቱ የሚነሱ ማናቸውም ክርክሮች፣ ውይይቶች እና ድምዳሜዎች ትውልድን በሚያንጽ፤ የተወለጋገደውን በሚያርቅ መልኩ እንዲሆን በኃላፊነት መንፈስ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ምክክሩ ውጤቱ ዛሬ ላይ የምናየውን ብዙ አለመግባባቶችንና መካረሮችን አርግቦ፤ እሴቶቻችንን አጎልብቶ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ልቦና ውስጥ ያለችውን ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና እንድትወጣ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን መፍታት የሚችሉበት ብዙ ማህበረሰባዊ እሴቶች ያሏቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች በምክክር ከባድ የምንላቸውን ችግሮች አባቶች ሰብሰብ ብለው ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ዳኝተው፤ የሚበጀውን ተናግረው ችግሩን አቅልለው ሰላም ያወርዳሉ፡፡ ይህን እሴት ነው መገንባት የሚያስፈልገው፡፡ ይህ አገራዊ ምክክርም አሉ የሚባሉ እጸጾችን ሁሉ ነቅሶ በማውጣት ተማክሮ ለአገር የሚበጀው እንዲያሸንፍ በማስተዋል የሚከወን ሊሆን ይገባል፡፡
አገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ አባቶች በምክር፤ መንግስትም ሆነ ገዥው ፓርቲ ብልጽግና እንዲሁም በዚህ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ባለድርሻ አካላት ሁሉ ትውልዱን በማሰብ በሰከነ ሁኔታ ሂደቱን በመከታተል እንዲሳካ የበኩላቸውን እና የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንደሚገባቸው እሙን ነው፡፡
ከዚህ አንጻር ብልጽግና ፓርቲ አገራዊ ምክክሩ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ እና አገራችን ዘላቂ ሰላሟ ተረጋግጦ የተሳካ የብልጽግና ጉዞና በተሳለጠ መንገድ እንድታስቀጥል በቁርጠኝት የሚሰራ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ አባላቱም አመራሩም ፍጹም ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ እያንዳንዱ ስራችን የአገራችንን ቀጣይ እጣ ፋንታ ያማረ በሚያደረግ መልኩ እንዲሆን መትጋት ይገባል፡፡

Leave a Reply