You are currently viewing የትውልዱ ታሪካዊ አደራውን የመወጣትና አገርን የመገንባት ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ /በሚራክል እውነቱ/

የትውልዱ ታሪካዊ አደራውን የመወጣትና አገርን የመገንባት ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments
ለእኛ ኢትዮጵያውያን መነቃቃትን የፈጠረው እና በገሀድ እየታዬ ያለው ሀገራዊ ለውጥ ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው ዓለም ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ኩራት ሁኗቸው በየሚኖሩበት ሀገር በብሔርና በሀይማኖት ስንክሳር ውስጥ ታጥረው ከወንድማማችነት ይልቅ የጠላትነት ስሜት በውስጣቸው ሲብላላ ቢቆይም እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ በተግባር የታየው ሀገራዊ ለውጥ ግን ጥቁሩ መጋረጃ ተወግዶ ኢትዮጵያዊነት በልጆቿ በመላው ዓለም ከፍ ብሎ እንዲታይ አስችሏል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት የጠንካራ አንድነት ጉልህ ፋይዳ ማሣያ ነውና።
ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት መጨመር ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት፣ለማህበራዊና አካባቢያዊ እንቅስቃሴዎች መስፋፋት ወጣቱ ትውልድ ትልቅ ሚና እንዳለው የማይታበይ ሀቅ ነው። ኢትዮጵያ እንደ ጀርመን ካሉ ሀገራት ጋር ስትነፃፀር ብዙ ወጣት ትውልድ ያላት ሀገር ናት።
በኢትዮጵያ 30 በመቶ ያህሉ በወጣትነት የዕድሜ ደረጃ ላይ ያለ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል። እነዚህ ወጣቶች ለሀገሪቱ ቀጣይ እድገት ጠንካራ መሰረት በመሆናቸው ለወጣቱ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ አስቀድሞ መስራት የግድ ነው።
በተለይ ደግሞ በትምህርት ዘርፎች፣ በስነ ምግባር፣ስራ ወዳድነት/ስራ ፈጠራ/እንዲሁም ለወጣቱ አስተማማኝ የሆነ የስራ እድል መፍጠርም ለነገ የማይባል የቤት ስራ ሊሆን ይገባዋል።
ደቡብ ኮሪያዊያን “እኛ የተወለድነው ለታሪካዊ ራዕይና ሀገራችንን ለመገንባት ነው” የሚል ዘመን ተሻጋሪና ከህሊና ሊጠፋ የማይችል ሀገረኛ አባባል አላቸው። በርግጥስ እነሱ እንደሚሉት ያለምክንያት የተፈጠረ ትውልድ አለ ብላችሁ ታስባላችሁ?
ደቡብ ኮሪያዊያን ለ35 ዓመታት በጃፓን ቀኝ ግዛት ተገዝተዋል።
ሰው ሆነው እንደሰው ያልታዩ፣ሰዋዊ ክብራቸው ተገፎ፣ሴቶችና ልጃ ገረዶች በጃፓን ወታደሮች ሲደፈሩ ማየት፣ህፃናት ከአቅማቸው በላይ እንዲሰሩ በማድረግ የጉልበት ብዝበዛ ማድረስ፣ አዛውንቶችን በአደባባይ መግረፍና ማሰቃየት፣የሚወዷት ሀገራቸው በቀኝ ገዢዎች ምስቅልቅሏ ሲወጣ እየተመለከቱ ማልቀስ የዕለት ተዕለት ስራቸው ሆኖ ለዘመናት ልባቸው ተሰብሮ ቆይቷል። ይህ ግን ለደቡብ ኮሪያዊያን የበለጠ ጉልበት ሆኗቸው ስለ ውድ ሀገራቸው ዕድገትና ነፃነት እንዲያስቡና እንዲያሰላስሉ አቅም ሆናቸው።
ያ ሁሉ ግፍና መከራ አልፎ ዛሬ ደቡብ ኮሪያ ነፃነቷን ካወጀችበት ጊዜ ጀምሮ ሌት ተቀን በመስራት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ፣በመኪና ምርትና ሽያጭ/ በየ 10 ሰከንዱ አንድ መኪና ማምረት የሚትችል ሀገር ሁናለች/፣በግዙፍ መርከቦች ምርት፣በስማርት ስልኮች… በሌሎችም ዘርፎች ከዓለም በመሪዎች ደረጃ ላይ የምትገኝ ሀገር ስትሆን የዜጎቿ የነፍስ ወከፍ ገቢም 30,000 ዶላር ማድረስ ችላለች።
ይህ ተዓምር ሊሆን ይችላል። ግን ደግሞ እጃችንን እስኪሻክርና ወገባችን እስኪጎብጥ ለምንወዳት ሀገራችንና ለተተኪው ትውልድ የምናስብ ከሆነ ዛሬ ላይ ለጉልበታችን ሳንሳሳ ልንደክም፣ልንሰራ ይገባናል።
ደቡብ ኮሪያ ትናንት ዜጎቿ በምግብ እጥረት ሲታመሱ፣ሀገሪቱ ወደለየለት ርሃብ ወርዳ ሲመለከቷት የነበሩ ሀገራት ይህች ሀገር ከዚህ በኋላ መቼውንም ልታድግም ሆነ ልትለወጥ አትችልም እንደውም ስም ሁሉ አውጥተውላት “ጥንቸል ናት” እያሉ ሲሳለቁባት የነበሩ ሁሉ ዛሬ ላይ በዜጎቿ እልፍ አስጨራሽ ትግል የተለወጠችውን ደቡብ ኮሪያ ሲለመከቱ ጥንቸሏ እያሉ ሲያላግጡባት የነበረችውን ሀገር “የኤስያዋ ነበር” በማለት መስክረውላታል።
እኛ ኢትዮጵያዊያንስ ከደቡብ ኮሪያዊያን ምን እንማራለን? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። ዛሬ በሀገራችን በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ገንብተን አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ አስቀምጠን የጋራ ሀገራችንን በመገንባት ሂደት ውስጥ እንገኛለን።
የሰላም መስፈን ጥቅሙ የጋራችን ነው፤ሰላም ማጣታችንም ጉዳቱ ለሁላችንም ነው። የህግ የበላይነት መከበርና የዴሞክራሲ መጎልበት ለኛ ለዜጎች የሚኖራቸው ጠቀሜታ ቀላል አይደለም፤ በመሆኑም ሰላማችን እንዳይደፈርስ፣ ብዝሃነትን ያከበረ ዴሞክራሲያዊ አብሮነታችን እንዲጎለብት ስንል አንድነታችን የሚፈታተኑ ሃይሎች የሚፈፀሙትን እኩይ ተግባራት መመከት፣ ማጋለጥና ማክሸፍ ብሎም እንደ ሀገር የጀመርነውን ሀገራዊ ለውጥ አጠናክረን በመቀጠል የሰላም ዘብ መሆናችን በተግባር ልናሳይ ይገባ።
የአሁኑ ትውልድ ቀደምት አባቶቻችን የጣሉበትን ታሪካዊ አደራና አገርን እንደ አገር የማስቀጠል ታላቅ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ሙሉ በሙሉ ፊቱን ወደ ልማት ማዞርና አደራውን ለመወጣት ሌት ተቀን ሊተጋ ይገባዋል።
ስለሆነም ከኤስያዋ ነበር ደቡብ ኮሪያ ትምህርት ወስደን ዛሬ ላይ ከፊት ለፊታችን ያለውን ዳገትና ኮረብታ በጋራ ሀይላችን ንደን የበለፀገችና ለመጪው ትውልድ ያማረች ሀገር ለማውረስ ያስችለን ዘንድ ነገን በማሰብ ከሴረኞችና ከጥፋት ሀይሎች እሳቤ ተላቀን ለምንወዳት ሀገራችን ሌት ተቀን በመስራት ሀላፊነታችንን እንድንወጣ መስራት ይኖርብናል።

ምላሽ ይስጡ