ብዝሃነታችን ጌጣችን፤ ኢትዮጵያዊነት መገለጫችን ነው! (በዘላለም በላይ)

ብዝሃነታችን ጌጣችን፤ ኢትዮጵያዊነት መገለጫችን ነው! (በዘላለም በላይ)

  • Post comments:0 Comments
ብዝሃነታችን ጌጣችን፤ ኢትዮጵያዊነት መገለጫችን ነው!
(በዘላለም በላይ)
የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የየራሳቸውን ባህልና እሴት ከመጠበቅና ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን የጋራቸው የሆኑ ባህሎችንና እሴቶችን እያዳበሩ በመቻቻልና በመተሳሰብ ኖረዋል፡፡ የብዙ ቋንቋዎች ተናጋሪ መሆናቸው ከመግባባት አላገዳቸውም፡፡ የተለያዩ ሃይማኖቶችንና እምነቶችን ቢከተሉም በፍቅርና በመተሳሰብ ከመኖር አልገደባቸውም፡፡
የተለያዩ የፓለቲካ አስተሳሰብ ቢኖሯቸውም በፖለቲካ ቅራኔዎቻቸው ሳቢያ ሀገራቸውን አላፈረሱም፡፡
የአንዱ ማኅበረሰብ ባህልና እሴት ለሌላው መኩሪያና መድመቂያ ሲሆን ተስተውሏል፡፡ የአንዱ እምነት ለሌላው ድጋፍ ሆኖት ኖሯል፡፡
ፖለቲካዊ ግንኙነቶች በቅራኔ በተሞሉበት ጊዜም ቢሆን ሀገር አደጋ ውስጥ ስትወድቅ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ሲተምሙና ጠላትን ሲያሳፍሩ ኖረዋል፡፡ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ብዝሃነታችን የምንደምቅበትና ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን አጉልተን የምናሳይበት ጌጣችን ነው፡፡
የሃይማኖት ይሁን የፖለቲካ፤ የብሄር ይሁን የመደብ ብዝሃነታችን ጌጥ ከመሆኑም በላይ የጥንካሬያችን ምንጭ ነው፡፡ ስንተባበርና አንድ ስንሆን ለአገራችን ብልጽግና ጽኑ መሠረት እንደምንሆን፤ ለጠላት ግን እንደ እሳት ነበልባል የምናቃጥል መሆናችንን የቅርብ አመታት ትውስታችን በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያዳበሯቸው የጋራ ባህልና እሴቶች የሀገራችንን ሉዓላዊነት አስጠብቀው ቆይተዋል፡፡ በአድዋ፣ በካራማራ፣ በማይጨው፣ ወዘተ… በጋራ ያስመዘገብናቸው ድሎች ብዝሃነታችን የጥንካሬያችን ምንጭና የኢትየጵያዊ ማንነታችን መገለጫ መሆኑን ማሳያ ናቸው፡፡
በዚህ ትውልድም በሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በዘመቻ ህብረ ብሄራዊ አንድነት፣ በበቃን የዲጂታል ዘመቻ ያሳየነው መተባበርና ያስመዘገብነው ድል ኢትዮጵያዊነታችንን ደግመን ያፀናንበት ነው፡፡

Leave a Reply