You are currently viewing ‹‹በኢትዮጵያ የሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤ የአፍሪካውያንን አንድነትና ወንድማማችነት ያረጋገጠ ነው›› -ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር

‹‹በኢትዮጵያ የሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤ የአፍሪካውያንን አንድነትና ወንድማማችነት ያረጋገጠ ነው›› -ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር

  • Post comments:0 Comments
35ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ በኢትዮጵያ መዲና መካሄድ የአፍሪካውያንን አንድነትና ወንድማማችነት ያረጋገጠ ነው ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ። የአፍሪካውያን አንድነት ለአገራዊና አህጉራዊ ጠላቶች ትልቅ መልዕክት አስተላልፏል።
ዶክተር ቢቂላ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በኢትዮጵያ መዲና መካሄድ የአፍሪካውያን አንድነትና ወንድማማችነት የሚያጠናከርና ለውጭ ኃይሎች ትልቅ መልዕክት ያስተላለፈ ነው።
አገር በማዳን ዘመቻ መንግሥት ጦርነት ውስጥ በገባበት ጊዜ የኢትዮጵያ ጠላቶች ከውስጥና ከውጪ ተደራጅተው በሚዲያ፣ በኢኮኖሚና በዲፕሎማስ መስክ ኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ አካሂደዋል።
ሚዲያቸውን በመጠቀም ከሁለት ሦስት ወር በፊት ኢትዮጵያ ልትበተን ነው የውጭ አገር ዜጎች አፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ እምነት እንዳይኖራቸው ለማድረግ መጠነ ሰፊ የተዛባመረጃ አሰራጭተዋል ብለዋል። ተቋማት በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸውን የልማትና የዲፕሎማሲ ሥራዎቻቸውን አቋርጠው እንዲወጡም ጥረት ተደርጎ እንደነበር አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በአንድነት በመቆም በከፈሉት መስዋዕትነት አገራዊና አህጉራዊ ጦርነቱን በሚገባ መቀልበስ ተችሏል ያሉት ዶክተር ቢቂላ፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት ያጣችውን ንብረት ወደ መገንባት እየተጓዘች ትገኛለች ብለዋል።
ድሉ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ መዲና እንዲካሄድ በማስቻሉ እንደ አገርም ሆነ እንደ አህጉር ለውስጥና ለውጭ ጠላት ትልቅ መልዕክት አስተላልፏል ብለዋል። የአፍሪካውያን አንድነትና ወንድማማችነትም የጥንካሬ ማሳያ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
እንደ ዶክተር ቢቂላ ገለጻ፤ ይህ ሁሉ ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ በተከፈተበት ወቅት አብዛኛው የአፍሪካ አገራት በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ድምፃቸውን በማሰማት ከኢትዮጵያ ጎን ቆመው አሳይተዋል። ኢትዮጵያ የገጠማትን የውስጥ ችግር በራሷ አቅም መፍታት እንዳለባት ያሰሙት ድምፅም በተዘዋዋሪ አፍሪካውያን የራስን ጉዳይ ያለማንም የውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነት መፍታት እንደሚችሉ ትልቅ ትርጉም ያለው መልዕክት አስተላልፈዋል ብለዋል።
አፍሪካውያንና ኢትዮጵያውያን በከፈሉት መስዋዕትነት የኢትዮጵያ እውነታ ለዓለም ማኅበረሰብ ተገልጧል። በኢትዮጵያ የሠላምና የጸጥታ ችግር አለመኖሩ በአፍሪካ ኅብረት ተቀባይነት አገኝቶ 35ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ መወሰኑ ለዚህ ትልቁ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል። ድሉ የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካውያን ድል ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ጥንካሬውን ለማስቀጠል የውጭ ጣልቃገብነትን በመቃወም የአፍሪካውያንን አንድነት ለማጠናክር የጀመረውን ፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ ለማጠናከር ይሠራል ያሉት ዶክተር ቢቂላ፤ ለወደፊት አፍሪካዊ አንድነትን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ትስስሮች ለማጠናከር እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ምላሽ ይስጡ