You are currently viewing ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት እስከ ህብረት  /በሚራክል እውነቱ/

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት እስከ ህብረት /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments

ቀደም ሲል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ያሁኑ የአፍሪካ ህብረት የተመሰረተው በኢትዮጵያ ሲሆን የተቋሙ መቀመጫም የሆነው በመዲናችን አዲስ አበባ ነው፡፡የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመጀመሪያው መሪ የሆኑት ቀዳማዊ ሃይለስላሴ መሆናቸውን በታሪክ ሰፍሮ እናገኘዋለን።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል እንደመሆኗም በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለአፍሪካ ነጻነት ድምጽ በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስታደርግ መቆየቷ በበርካታ አፍሪካዊያን ምሁራኖች አንደበት ሲገለጽ ቆይቷል፤ወደፊትም ይህ እውነታ ለትውልድ የሚተላለፍ ይሆናል፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ሕብረት ከተሸጋገረም በኋላ በአፍሪካ ውስጥ ለሚነሱ ግጭቶች በሠላም ማስከበር እና በሌሎች ልዩ ልዩ ተልዕኮዎች ስትሳተፍ ቆይታለች፤ እየተሳተፈችም ትገኛለች። ኢትዮጵያ እንደ መስራች አገር የመሪነት ሚናዋን በፍጹም ቁርጠኝነት ኃላፊነቷን እየተወጣች ትገኛለች።

ምዕራባውያን ኢትዮጵያን ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረጉ ባሉበት ወቅት አፍሪካውያን 35ኛው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰናቸው ለኢትዮጵያ ያላቸውን ክብርና ታላቅነት ያሳያል፡፡ አፍሪካውያን፣ የአፍሪካ ምሁራን እና መንግሥታት ለኢትዮጵያ የሚሰጡት ክብር ከፍ ያለ መሆኑን አንዱ ማሳያ አፍሪካውያን 35ኛው የሕብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰን መቻላቸው ነው፡፡

እኛ አፍሪካዊያን ከድህነት የመውጣትና የማደግ ተስፋችን እር በእርስ የተጋመደና የተሳሰረ ነው፡፡ አንዳችን ያለአንዳችን ከድህነት መውጣት በእጅጉ ይከብደናል፤ስለሆነም አፍሪካችንን ወደ ብልጽግና ከፍታ ለማሸጋገር ያስችለን ዘንድ አህጉራዊ ግንኙነታችንን ይበልጥ ማጠናከር ይገባናል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካዊያን ሁለተኛ አገራቸው ናት ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ አዲስ አበባ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ህንጻ ደግሞ አፍሪካዊያን በልዩ ልዩ ጉዳዮቻቸው ዙሪያ ከየአገራቸው ወደ መዲናችን መጠው የሚመክሩበት የጋራ መጠለያቸው ነው፡፡

አፍሪካውያን ወንድሞቻችን አገራችንን እንደ እኛ ይወዳሉ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በዓለ ሲመት ወቅት ከተገኙት ጎረቤት አገራት መካከል የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት እናት›› በማለት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

እንደ አገር ብቻችንን ከድህነት አረንቋ መውጣት ከባድ ነው፤ሊታሰብም አይችልም፡፡የወደፊት ራዕያችንና እጣ ፈንታችን ከአፍሪካዊያን ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2063 የአፍሪካ አገራትን እርስ በእርስ በልማት የማስተሳሰር ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ከተገባ ዋል አደር ብሏል።ይህን ዕቅድ ከግብ ማድረስ ስንችል አብሮ የመልማትና የማደግ የጋራ ዕቅዳችን ይሳካል ሲሉ ገልጸዋል ማለት ነው፡፡

የ35ኛው የህብረቱ አባል አገራት ተሳታፊ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ልክ አገራቸው እንዳሉ እንዲሰማቸው ማድረግ የእያንዳንዳችን ግዴታና ሃላፊነት መሆኑን ተረድተን በዚህ ልክ መዘጋጀት ይገባናል። ከአፍሪካውያን ይልቅ ለነጮች ያለን ከበሬታ በእጅጉ የተለዬ በመሆኑ ይህንን የተዛባ አተያይ በፍጥነት መቀልበስና ለአፍሪካዊያን ያለን ምልከታ ማሰተካከል ይኖርብናል፡፡

የአፍሪካ ወንድሞቻችን ከእኛ ጋር መሰለፋቸው አንዱ ማሳያ አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባዊያን አገራት ከአሸባሪው ህወኃት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ እያሳደሩት በነበረው ጫና ላይ የይበቃል (No More) እንቅስቃሴ በመቀላቀል ከፍ ያለ አጋርነታቸውን ማሳየታቸው ነው፡፡

ስለሆነም ለአፍሪካዊያን ያለን ምልከታ ያደገና ወቅቱን ያገናዘበ መሆን እንደሚገባው መረዳት አለብን፡፡በጉባኤው ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ በሚመጡበት ጊዜ ኢትዮጵያን እንደሚያስቧት የአፍሪካውያን መሆኗን በአክብሮትና የእንግዳ ተቀባይነት ባህላችንን ማሳየት በእርግጥም ለአፍሪካዊያን ያለንን ወዳጅነት ከፍታ ማሳያ ይሆናል።

ምላሽ ይስጡ