አካታች ብሔራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ ትንሳኤ መሰረት ነው፤ /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments

ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ያላቸው ፍቅርና ስሜት ቃላት ከሚገልጹት በላይ ነው፡፡ዓለም ኢትዮጵያውያንን በአንድ ነገር ያውቋቸዋል፤ ይህም ስማችን በበጎ ከሚነሳባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ለሃገራችን በአንድነት የመቆማችን ሚስጥር ነው። ይህንን ታሪካችን ደግሞ ኢትዮጵያን ለመቀራመት ፍላጎት የነበራቸው ምዕራባውያን ቅኝ ገዢዎች ፍላጎታቸውን ለማሳካት በተነሱበት ወቅት እምቢ ለሃገሬ ብለን በተግባር መልሰን አሳይተናቸዋል።

የጣሊያን ቅኝ ገዢ ወራሪ ፋሽስት ሃይሎች የአድዋ ጦርነት በተካሄደበት ወቅት ስለኢትዮጵያ የነበራቸው ግምት በእጅጉ የተሳሳተ ነበር።በአንድ በኩል ኢትዮጵያዊያን ድሆችና ያልሰለጠኑ ናቸው፤በሌላ በኩል ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የላቸውም፤ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው የተዳከመና ጉልበት የሌላው ነው፤ኢትዮጵያውን ስለአገራቸው ጉዳይ ከአፍሪካውያን የተለዬ አቋም የላቸውም በመሆኑም በቀላሉ ወረራ አካሂደን ዓላማችንን ማሳካት እንችላለን ሲሉ አስበው ነበር።

ይሁን እንጂ በአድዋ ጦርነት ወቅት የመሳሪያ ብዛትና ክምችት እንዲሁም ግዙፍ የጦር ሰራዊት ብቻውን ለድል እንደማያበቃ ከኢትዮጵያ ትልቅ ትምህርት የወሰዱበት ወቅት ሆኖ ሊያልፍ ችሏል። ይህ ሊሆን የቻለው ታዲያ ኢትዮጵያውያን በጋራ ጉዳያቸው ላይ ያለምንም ጉትጎታ ከፊት የሚሰለፉ ህዝቦች በመሆናቸው ነው።

ይህንን አኩሪ ገድል የሰሩት ኢትዮጵያዊያንን ስነ ልቦና በውል ያልተረዳውና ከታሪክ ሊማርም ሆነ ሊገባው ያልቻለው የአሸባሪው ሕወኃት ኃይሎችም ዛሬም በተመሳሳይ ይህንን የኢትዮጵያውያንን ማንነት ዘንግተው ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያለ የሌለ ሃይላቸውን ተጠቅመው ቢንቀሳቀሱም በጀግና ኢትዮጵያዊያን አንድነት አፍረው ተመልሰዋል።ጠላት መጨረሻም ውድቀት ነው፤በመካከላቸው አለመግባባቶች እያየለ የመጣው አሸባሪው የህወኃት ቡድን ከዚህ በኋላ ምንም መፍጠር አቅምም ሆነ ተሰሚነት እንደሌለው እርግጥ ሆኗል፡፡

በሽብር ቡድኑ የተነሳ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ሰላማቸውን አጠው ኖረዋል፡፡ከዚህ በኋላ ግን ኢትዮጵያዊያን ሊያግቧቧቸው ያልቻሉ ነጥቦችን ነቅሰው በማውጣትና ለችግሮቹ በጠረንጴዛ ዙሪያ ሁሉን አቀፍ ምክክር በማድረግ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የሰላም አየር ከጫፍ ጫፍ ይነፍስ ዘንድ ፍላጎታቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል አካታች ብሔራዊ የውይይት መድረክ ለማካሄድ ያለውን ፍላጎት ይህንኑ ሊመራ የሚችል ኮሚሽን ከማቋቋም ጀምሮ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችን እስከ መፍታት ድረስ አሳይቷል፡፡

መንግስት አካታች ብሔራዊ የውይይት መድረክ ለመፍጠር እያሳለፋቸው ያሉት ውሳኔዎች ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ያሳያል በሚል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝና የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር የሆኑት ሙሳ ፋቂ ምስክርነታቸውንና አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአንድ አገር ውስጥ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ኖሮም አያውቅም፤ሊኖርም አይችልም፡፡ ስለሆነም በሁሉም ነገር መግባባት ከቶም አይቻልም፤ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው የራሱ ምልከታና ግምት አለውና፡፡ ሆኖም ግን ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን በማድረግ እንደ አገር ለድርድር በማይቀርቡ ወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መክረን ለአገር ቀጣይ ሰላም፣ልማትና ብልጽግና ደጀንነታችንን ልናሳይ ይገባል፡፡

በመስቀል አደባባይ የአዲስ መንግሥት ምስረታና በዓለ ሲመት ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር፤ በአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል መግባባትን ለመፍጠር ሁሉን አካታች ውይይት ይካሄዳል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ “የፖለቲካ ሥርዓቱ የአሸናፊ ሳይሆን የመግባባት እንዲሆን አብረን እንሠራለን። በንግግር እና በምክክር ለአንገብጋቢ ችግሮች መፍትሔ እናገኛለን። አካታች ብሔራዊ የውይይት መድረክ እናካሂዳለን። ችግሮቻችንን በጠረጴዛ ዙርያ የምንፈታበት ይሆናል” ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “በመጪው ዘመን ብዝኃነታችንን በጌጥነት ተቀብለን መታረቅ የሚችል ሐሳባችንን አስታርቀን መከበር የሚገባው ልዩነቶቻችችን አክብረን ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን አጠንክረን ወደ ከፍታ የምንተምበት ጊዜ ይሆናል። ይኸም እንዲሳካ የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን ለማጥበብ አካታች ብሔራዊ የውይይት መድረክ እናካሂዳለን” ሲሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ ቃል ገብተዋል፡፡

ይህ አካታች የምክክር ሒደት ችግሮቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ ይፈታሉ ብለው የሚያምኑትን የሚያካትት፤ በፖለቲካ ልሒቃን መካከል ብቻ የሚደረግ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ያገናዘበ አጠቃላይ ሒደቱ አካታች እና አሳታፊ እንዲሁም በኢትዮጵያውያን እየተመራ ሀገር በቀል መፍትሔዎች ለማፍለቅ ታልሞ የሚከናወን ስለመሆኑ የብልጽግና ፓርቲም ሆነ መንግስት በተደጋጋሚ እየገለጸ ይገኛል፡፡

ስለሆነም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ለዚህ አካታች ብሔራዊ የምክክር መድረክ ስኬታማነት የየበኩላችንን አስተዋጾኦ በመወጣት የታሪክ ተካፋይ ልንሆን ይገባል፡፡ሰላም!

Leave a Reply