You are currently viewing የዲያስፖራው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ለአገር ግንባታና ለብልጽግና መሰረት ነው፤ በሚራክል እውነቱ

የዲያስፖራው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ለአገር ግንባታና ለብልጽግና መሰረት ነው፤ በሚራክል እውነቱ

  • Post comments:0 Comments
ዶ/ር አብይ አህመድ የጠቅላይ ሚኒስተርነቱን ቦታ ከያዙ ጀምሮ እያስመዘገቡ ያሉት ፈጣን ፖለቲካዊ ለውጥ ያላስደሰታቸው ካሉ ጥቂት ለሆዳቸው ያደሩ፣ የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ ያልተረዱ ስለመሆናቸው ጥርጥር የለውም፡፡
 
አሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች በአገራችን ላይ እያሳደሩት ያለውን ጫናና ጣልቃ ገብነት ለመቃወም ሰሞኑን በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች ሲደረጉ የነበሩ መሬት አርድ ሰላማዊ ሰልፎች በእርግጥም ለአገራቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅርና ከበሬታ ያሳየ ነበር፡፡
 
በውጭ የሚኖረው የዲያስፖራው ማህበረሰብ እንቅስቃሴ በእጅጉ አበረታችና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ሲሆን ይህ ወገናዊነት ከሰላማዊ ሰልፍ አልፎ ወደ ኢኮኖሚያዊ ትብብር እና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡ በተለይ ደግሞ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች ያደረሰውን ውድመትና የሃብት ምዝበራ ለመተካት ያስችል ዘንድ ጠንካራ ኢኮኖሚ መፍጠር የግድ የሚለን ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡
 
በሌላ በኩል እንደ አገር የገጠመንን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች ገደብ የለሽ እንቅስቃሴ ተጠባቂ ነው፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ገንዘብ በባንክ በኩል ብቻ እንዲልኩ በማድረግ ሃገራችን ከገጠማት ኢኮኖሚያዊ አጣብቂኝ ውስጥ ማውጣት ይገባቸዋል፡፡ ይህን ማድረግ እንደሚችሉም እያሳዩት ያሉት ሰሞናዊ ተግባራቸው መስካሪ ነው፡፡
 
ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገራቸው እየገቡ ይገኛሉ፡፡ ሰሞኑንም በአሸባሪው ህወኃት የወደሙ ንብረቶችንና ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ለመጎብኘት ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የዲያስፖራው ማህበረሰብ ከጉብኝቱ ባሻገር ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ማካካስ በሚችሉ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ለአገራቸው የሚጠቅም ስራ ይሰራሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡
 
አሸባሪው ህወኃት ስልጣን ላይ ባሳለፋቸው እነዚያ የመከራና የጨለማ 27 አመታት ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች ሲደርስባቸው የነበረውን ግፍና የኢኮኖሚ አሻጥር መቼም አይዘነጉትም፡፡ ከአገራዊ ኢኮኖሚው ይልቅ ከአሸባሪው ህወኃት ጋር የጥቅም ትስስር ለነበራቸው የንግድ ድርጅቶች እና ባለሃብቶች ቅድሚያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የሚያስችል የውጭ ምንዛሬ አደላደል እና አጠቃቀም በርካታ ባለሃብቶች ከሚወዷት አገራቸው ተገፍተው ገንዘባቸውንና ሃብታቸውን በውጭ እንዲያፈሱ ያስገደደ አድሏዊ አሰራር ነበር፡፡
 
አሁን የአገራችንን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ዲያስፖራው ወደ ሃገር ቤት የሚልከው ገንዘብ ከጥቁር ገበያ የጸዳና ህጋዊነቱን የተከተለ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህን ማድረግ ሲቻል ኢኮኖሚያዊ አቅማችን ከማደጉም በላይ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቀነስ ያስችላል፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር በነበራቸው መድረክ ላይ እያንዳንዳችን ለማኪያቶ በቀን የምናወጣውን “አንድ ዶላር” መሰብሰብና ወደ አገር ቤት መላክ ብንችል ክፍተቶቻችንን ለመሙላት ያግዘናል ማለታቸው ይታወሳል፡፡
 
በዚህ መነሻ ሃሳብ ሊሰበሰብ የታቀደው የውጭ ምንዛሬ ገንዘብ በተበጣጠሰ፣ ባልታቀደ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት በጎደለው መልኩ እንዳይካሄድና የመሳካት እድሉን አነስተኛ ወይም ዝቅተኛ እንዳያደርገው ህጋዊ መስመሩን የተከተለና ገንዘብ ለሚልከው የዲያስፖራ ማህበረሰብ ግልፀኝነት የተሞላበት መሆን ይኖርበታል።
 
ምንም እንኳን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መሪነት የተጀመረው የለውጥ ሂደት በሃገር ወስጥ እና በዲያስፖራ ያለውን ህዝብ ቀልብ የሳበ እና ትልቅ ተስፋን ያሳደረ ክስተት ቢሆንም፤ ይህን የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ የሚሹ ከውስጥም ከውጭም እጃቸው የረዘሙ ሃይሎችን ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ጋር ሆነን በጋራ ልንታገላቸው ይገባል፡፡
 
ከዲያስፖራው ጋር የምናደርገው ይህ አይነቱ የጋራ እንቅስቃሴያችን ጣልቃ ሊገቡ ያሰቡ ሃይሎችን አስቀድሞ አፋቸውንም ሆነ እጃቸውን እንዲሰበስቡ ከማድረጉም ባሻገር በዲያስፖራው እና በመንግስት መካከል ያለው ግንኙነት እና ትብብር ስር የያዘ እና ዘለቄታዊነት ያለው እንዲሆን ያደርጋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ዲያስፖራው የትውልድ ሃገሩን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ለመርዳት እና ለማሳደግ ሰፊ በር የሚከፍት እና አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጥ ነው።
 
በመጨረሻም ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች በሃገር ቤት የሚያደርጓቸው የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት፣ የእውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የበጎ አድራጎት እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች የብልሹ አሰራር ሰለባ እንዳይሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በመፈተሽ በተቻለ መጠን ቀልጣፋ እንዲሆኑ እና ከሙስና እንዲጸዱ ማድረግ ለነገ የማይባል ተግባር ሊሆን ይገባዋል።

ምላሽ ይስጡ