አዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁላችንም በምናበረክተው ጠጠር ልክ ትሰራለች! /በዜማ ያሬድ/

አዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁላችንም በምናበረክተው ጠጠር ልክ ትሰራለች! /በዜማ ያሬድ/

  • Post comments:0 Comments
ኢትዮጵያውያን ልባቸውም እግራቸውም ወደአገር ቤት እየተመመ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ በብዙ እያተረፈች ነው፡፡ ሃብትና ዝና ከአገር በታች መሆኑን በዚህ ተገደን በገባንበት የህልውና ዘመቻ ማየት ተችሏል፡፡ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአለም ጫፍ ቢሆኑ ለአገራቸው ያላቸው ክብርና ፍቅር የማይሸረሸር፤ አገር ካካበቱት ሃብት፣ ካላቸው ዝናም በላይ መሆኑን በማሳየት ብዙ ሆነው ግን እንደ አንድ በመቆም አለምን ማስደመም ችለዋል፡፡ በእርግጥም እኛ ኢትዮጵያውያን ትናንትም ዛሬም ወደፊትም የአገራችንን ህልውና ማስጠበቅ የምንችለው በራሳችን ጥረት ብቻ መሆኑን ከደረስንበት የትግል ምዕራፍ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ናት፡፡ ብዙ ስለአገር የሚዋደቁ፤ ስለአገር ኖረው የሚያልፉ ልጆች አሏት፡፡ በዓለም አደባባይ አገሬን አትንኩ ሲሉ ወደአደባባይ በመውጣት ስለአገራቸው ግንባራቸውን የሰጡ ልጆች ያሏት አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ አሁን በብዙ እያተረፈች ነው፡፡ ሰለአገር የተዋደቁ፤ ስለአገር መስዋዕትነት የከፈሉ ዜጎቿ በክብር የሚወደሱበት፤ የተዋደቁለት አላማም ግቡን የሚመታበት የአንድነት እና የብልጽግና ዘመን ከፊታችን አለ፡፡
በዘር፣ በሃይማኖት ከፋፍለው ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ግን ተራርቀው፤ ሆድና ጀርባ ሆነው እንዲኖሩ የፈረዱባት የአገር ነቀርሳዎችን መንግሎ በመጣል የማትናወጥ አገር ለመፍጠር ሁሉም አሻራውን እያሳረፈ ነው፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በልጆቿ መስዋዕትነት አትርፋለች የምንለው፡፡
ኢትዮጵያውያን ለአገር ህመም የሆነን ማንኛውንም አካል የሚሸከሙበት ጫንቃ እንደሌላቸው በተጨባጭ አሳይተዋል፡፡ አሁንም እዚህም እዚያም ተወትፎ ስር ለስር የአገር አንድነትን የሚሸረሽር አካል መጨረሻው መቃብር መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን ዳግም አንድነትን የሚያላላ፤ ለአገር ብልጽግናም ሳንካ የሆነን ማናቸውንም አካል መታገስ አይገባቸውም፡፡ አሁን ዜማውም ቅኔውም አንድ ነው፡፡ አንድነት፣ መተጋገዝ፣ መተሳሰብ እና ብልጽግና ብቻ፡፡
ኢትዮጵያን ልቀቁ እየተባለ የጥፋት ከበሮ ሲጎሰም ሞቴንም ደስታዬንም በአገሬ ብላችሁ ወደአገራችሁ የተመማችሁ የአገሬ ልጆች ኢትዮጵያ በእናንተ አትርፋለች፡፡ በአገር ተስፋ እንደማይቆረጥ እናንተ ሆናችሁ አሳይታችኋልና ክብር ይገባችኋል፡፡ ወደፊትም እያንዳንዷ ርምጃችሁ አገርና ህዝብ በሚያተርፍበት፤ አንድነታችን በሚጎለብትበትና ብልጽግናችን በሚረጋገጥበት ጉዳይ ላይ ብቻ እንዲሆን መትጋት ይገባችኋል፡፡
አገሬ ነገዋ ብሩህ ነው፡፡ ይህ ለጠላቶቻችን ህመም ነው፤ ነገም የለመዱትን ሴራቸውን ከመሸረብ ወደኋላ አይሉምና ዙሪያ ገባችንን ነቅቶ መጠበቅ ግድ ይላል፡፡ አንድነታችንን ጠብቀን እርስ በእርስ መደጋገፋችንን አጎልብተን ለኢትዮጵያ ብልጽግና ወደፊት ማለት ያስፈልጋል፡፡
የህወሃት የሽብር ቡድን በአማራ እና አፋር ክልል ፍጹም ኢትዮጵያዊ ያለሆነ እኩይ ተግባር በመፈጸም ባህላችንን፤ እሴታችንን ለማቆሸሽ ብዙ ጥረት አድርጓል፡፡ ይህ ቡድን አላማው ኢትዮጵያን ማፍረስ፤ ቅርሶቿን ማውደም፤ እሴታችንን፣ መገለጫችን በማጥፋት ኢትዮጵያውያን ዘላለም አጎንብሰው እንዲኖሩ ማድረግ ነበር፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያውያን ከፍ ያለ ስነልቦና ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን አልተረዱትም፡፡
ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው የፈረሰውን መገንባት እንደሚችሉም አላስተዋሉትም፡፡ ኢትዮጵያ ትፈተናለች እንጂ መቼም አትወድቅም፡፡በአማራ እና አፋር ክልል የደረሰውን ውድመት ኢትዮጵያውያን ተባብረው በመጠገን፣ የሰማዕታቱን ቤተሰቦችም በቋሚነት በማገዝ ጉዳታቸውን መካፈል ያስፈልጋል፡፡
የተሰበሩ ልቦችን ኢትዮጵያውያን በወጋቸው በባህላቸው ሊጠግኑ ይገባል፡፡ ይሄን ጊዜ አልፈን ኢትዮጵያ ብልጽግናዋ እውን ሆኖ የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ አገራችን በልጆቿ ብዙ ታተርፋለች እና አገር እንደእናት ስትጣራ አለሁ ብላችሁ ለመጣችሁ፤ በጦርነቱ ተጎዱ ወገኖቻችሁንም በአቅማችሁ ለማገዝ እየተረባረባችሁ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ክብር ለእናንተ ይሁን፡፡ ነጋችን በምንጽፈው ታሪክ፤ በምንወረውራት እያንዳንዷ ጠጠር ትሰራለች፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች፡፡

Leave a Reply