You are currently viewing ኢትዮጵያ ለዘመናት ብሔራዊ…

ኢትዮጵያ ለዘመናት ብሔራዊ…

  • Post comments:0 Comments
ኢትዮጵያ ለዘመናት ብሔራዊ ክብሯን ሉዓላዊነቷን ሳታስደፍር የኖረችው በየዘመኑ በኖሩ አገር ወዳድ አባቶቻችን፣እናቶቻችን በከፈሉት ከፍ ያለ መስዋዕትነት መሆኑ የሚታወቅና ሁሌም ሲዘከር የሚኖር ጀብድ ነው።
 
አገር ሊወር ከሩቅ የመጣ ጠላት ጊዜው ያፈራውን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስካፍንጫው ታጥቆና ውቅያኖስ አቋርጦ፤ በማንአለብኝነት ድንበር ጥሰው አንገታችንን ሊያስደፉን፣ኢትዮጵያዊ ክብራችንን ሊነጥቁን፣ሉዓላዊነታችንን ሊደፍሩ አስበውና አቅደው የመጡ ጠላቶቻችንን ኢትዮጵያ በኋላ ቀር መሳሪያ መክታና ድል አድርጋ የመለሰቻቸው በልጆቿ የተባበረ ክንድ ነው።
 
ኢትዮጵያዊያን በአዲስ ተስፋና በፈተና ውስጥ ናቸው። የያዝነው ተስፋ በግልጽ የሚታይ ነው፤ላለፉት ሃያ ሰባት የጨለማ ዓመታት በልዩነትና በጥላቻ አጥር ውስጥ ታጥረው የነበሩ ህዝቦቿ ህብረ ብሄራዊ አንድነታቸውን ጠብቀው እንዲጓዙ የሚያስችል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ መገኘታችን ነው።
 
በጠመንጃ መዋጋት የምንችለውን ጠላት ተዋግተን ኢትዮጵያ ዛሬም በልጆቿ ፀንታ እንድትቆም ማድረግ ችለናል፡፡ዳሩ ይህ ብቻ ያሰብነውን አገራዊ ብልጽግና ማምጣት አይችልም፤በአፈሙዝ ተዋግተን ማሸነፍ የማንችለው ብቸኛው የጋራ ጠላታችን ድህነት ነው፤ስለሆነም በጠላት ላይ ያሳየነውን የበላይነት ዳግም በድህነት ላይ ልንረባረብበት ይገባል፡፡
 
የውጭ ጠላቶቻችን ተደጋጋሚ ጫናዎችንና ማዕቀቦችን መጣላቸው አንደኛው ምክንያት ኢኮኖሚያዊ አቅማችን የጎለበተ ባለመሆኑና ዛሬም ድረስ ተረጂ በመሆናችን የተነሳ ነው፡፡
 
ሰጪ ጉልበት አለው፣ያሻውን መወሰንም ሆነ ማድረግ ይችላል፤ከዚህ ሁሉ ጫና ተላቆ ራስን የበለጠ ለማስከበር ደግሞ ሌት ተቀን ሳንል እጃችን እስኪሻክር ድረስ መስራትና ከድህነት ጋር ፊት ለፊት ታግለን ማሸነፍ ስንችል ብቻ ነው፡፡ሁላችንም ትኩረታችንን ወደ ልማታዊ ስራዎቻችን እናድርግ፡፡

ምላሽ ይስጡ