ብድር እና እርዳታ- አፍሪካን የጠፈነገው ችንካር
በማራኪ አያሌው
ምዕራባውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛት ቀጥታ ሲበዘብዟት ከኖሩ በኋላ አሁን ደግሞ አህጉሪቷን ከማትወጣበት አዙሪት ውስጥ በመክተት የብዝበዛ ስልቱን በአዲስ እሳቤ ቀየሩት፤ በብድር እና እርዳታ፡፡ ይህ ስልታቸው ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ለሚሆን ግዜ አፍሪካን ከማይነጥፍ የተፈጥሮ ሃብቷ እንድትገብርላቸው አድርጓታል፡፡
ለአፍሪካ የሚሰጥ እርዳታ ወደ እድገት የሚያስፈነጥር ሳይሆን አፍሪካ እነሱ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ እንድትኳትን የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በተለይም በአለም አቀፉ ገንዘብ ድርጅት (IMF) እና አለም ባንክ (WB0 በኩል የሚሰጠው ብድር የረባ ነገር ላይ ሳይውል፤ ወለድ እና ብድሩን አፍሪካ ትከፍላለች፡፡
የመጣው ገንዘብ ከፊሉ ከራሳቸው ከምዕራባውያኑ ለሚሸመተው የጦር መሳሪያ ግዥ፤ ከፊሉ ደግሞ ለሙስና ሲሳይ ይሆናል፡፡ በዚህም በዓመት ውስጥ ከአፍሪካ ካዝና ወደ ውጭ የሚወጣው ገንዝብ በብድር እና እርዳታ ከሚመጣው የሚበልጥ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
በኢትዮጵያ ህወሓት ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ከሀገር ውስጥ ምርት ከግማሽ በላይ የሚሆነው ያክል የውጪ ብድር ዕዳ እንድትሸከም ተገድዳለች፡፡ ፎርብስ በ2017 ባወጣው ጽሑፍ በ27 ዓመታት ውስጥ በብድር እና እርዳታ መልክ ወደ ኢትዮጵያ የገባውን ጨምሮ 30 ቢሊየን ዶላር ከኢትዮጵያ መውጣቱን ያነሳል፡፡ ይህ ማለት በዓመት ከ1ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ተዘርፏል ማለት ነው፡፡ ለሀገርቱ ዜጎች የተረፈው ዕዳው እና ወለዱ ብቻ ነው፡፡ ሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት የዚህ መሰል ዝርፊያ ሰለባ ናቸው፡፡
ከሁሉ በላይ ደግሞ የሚሰጡትን ብድር እና እርዳታ የሚሰጡት በቅድመ ሁኔታዎች አስረው በመሆኑ ገንዘቡን የሚቀበሉት አፍሪካውያን ከየሀገራቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይስማማ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ ገበያዎቻቸውን እና የተፈጥሮ ሃብታቸውን በብዝበዛ ለተካኑት የምዕራባውያኑ ኩባንያዎች ክፍት ማድረግ ነው፡፡ ብድሩን ተከትሎ ኩባንያዎቹ ያለ ከልካይ ምዝበራቸውን ያጧጡፋሉ፡፡
ወዲያ በአፍሪካ የተፈጥሮ ሃብት ሌሎች የብልጽግናና የቅንጦት ኑሮ ሲመሩ ወዲህ ደግሞ ብድር እና እርዳታ በተባለ ችንካር አፍሪካ እና አፍሪካውያን ባሉበት እየረገጡ ይኖራሉ፡፡ የአፍሪካ ሃብት ለአፍሪካውያን ብልጽግና ይውል ዘንድ አህጉሪቷን የጠፈነጋት ችንካር ሊነቀል ግድ ስለሚል ነው ኢትዮጵያ (#NoMore) #በቃ ማለት የጀመረችው፡፡
የገጠምነው ትግል ከደለቡ ሴረኞች እና ጥቅምን በእጅጉ ከሚያሳድዱ ጋር እንደመሆኑ ችንካሩን ለመንቀል እልህ አስጨራሽ ትግል ይጠይቃል፡፡ እናም ቅኝ ግዛትን ለማክተም የጥንት አባቶቻችን እንዳደረጉት ሁሉ ከአፍሪካውያን እህት-ወንድሞቻችንን ጋር ተሰልፈን በመራራ ትግል ጣፋጩን ድል ልናጣጥም ግድ ነው፡፡