You are currently viewing ሁለገቡ የኢትዮጵያ ኩራት  *በሚራክል እውነቱ*

ሁለገቡ የኢትዮጵያ ኩራት *በሚራክል እውነቱ*

  • Post comments:0 Comments

ሰራዊታችን ችግር የማይበግረው፤ ከራስ በፊት ለህዝብ ኖሮ ለአገር የሚሞት፣የፈተናዎች መደራረብ ከኢትዮጵያዊነቱ መሰረቱ የማይነቃነቅ፣የአገር ሰላም የሚያሳስበው፣ተርቦና ተጠምቶ እንኳ አገርን ከፊት የሚያስቀድም፣በስነ ምግባር የተቀረጸ፣ከአገር አልፎ ለአፍሪካዊያን ኩራት ምንጭ የሆነ ሰራዊት ነው-የአገር መከላከጣ ሰራዊት፡፡

ጠላት ሀገርን ሊወር ከሩቅ ሲመጣ ከህዝብ ቀድሞ ግንባሩን ለጥይት የሚሰጥ፣ ለሀገር ኖሮ፣ ለህይወቱ ሳይሳሳ ግንባር ተሰልፎ፣ ለሀገር ተዋግቶ፣ ለሀገር ቆስሎ ለሀገር የሚሞት የኢትዮጵያዊነት መሰረት ነው፤ የአገር መከላከያ ሰራዊት፡፡

በሰላሙም ጊዜ ህዝብን መስሎ የሚኖር፣ ህዝብ ሲቸገር ቆሞ ማየት የማይችል እንስፍስፍ ልብ ያለው፣ ዜጎች በደም እጦት ምክንያት ህይወታቸው እንዳያልፍ ዳር ድንበሩን እየጠበቀ ደሙን ሳይሰስት የሚሰጥ የህዝባዊነት ምልክት ነው፡፡

ሰራዊታችን በአሸባሪው የህወኃት ቡድንም ሆነ በተፈጥሮ ምክንያት የፈረሱና አገልግሎት መስጠት ያልቻሉ ድልድዮችንና መንገዶችን ጉልበቱን፣ ገንዘቡንና ዕውቀቱን አጣምሮ ለህዝብ ጥቅም የሚያውል ከራሱ በላይ ለህዝብ የሚኖር የመልካም ስብዕና ባለቤት ነው፡፡

የሽብር ቡድኑ ህወኃት በሰራዊታችን የሚቃጣበትን ጥቃት መቋቋም ሲሳነው በህዝብ ሀብት የተሰሩ ትምህርት ቤቶችን፣የጤና ተቋማትን፣ግዙፍ ፋብሪካዎችን፣ድልድዮችን፣ተሸከርካሪዎችን፣መንገዶችንና አየር መንገዶችን ከጥቅም ውጭ ሲያደርግ ተመልክተናል፡፡ ይሁን እንጂ ሁለገብ የሆነው ሰራዊታችን ከዚህ ቀደም በተለያዩ የግዳጅ ግንባሮች እንደሚያደርገው ሁሉ ጠላት የሆነውን ህወኃት እየተዋጋ ጎን ለጎን በጥፋት ቡድን ጥቃት የተፈጸመባቸው መሰረተ ልማቶችን እየጠገነ ለአገልግሎት እንዲበቁ ማድረጉ በታሪክ ተመዝግቦ የሚቀመጥ እውነታ ነው፡፡

ሰራዊታችን አርሶ አደር ነው፤ ከአርሶ አደሩ ጋር አርሞ፣ አጭዶ ጎተራ የሚያስገባ ገበሬ፤ አርብቶ አደርም ነው፡፡ መሐንዲስም ነው፡፡ መልካዓ ምድራዊ አቀማመጣቸው በእጅጉ ፈታኝ የሆኑ አካባቢዎችን ሀላፊነት ወስዶ ጋራ ሸንተረሩና ሸለቆው ሳይበግረው መንገድና ድልድይ ስርቶ ማስረከብ የሚችል የታታሪነት ተምሳሌት፡፡

ሰራዊታችን በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩና በቂ የህክምና አገልግሎት ማግኘት ላልቻሉ ነዋሪዎች ከተማ ድረስ ሄደው ህክምና እንዲያገኙ በርካታ አምፑላንሶችን ገዝቶ ለወለደው ህዝብ እንካችሁ የሚል ከህዝብ ወጥቶ ለህዝብ እየኖረ ያለ ርሁሩህ ሰራዊት ነው፡፡

ሰራዊታችን ሁሉንም መሆን የቻለና የሚችል የብሔር ብሔረሰቦች ስብስብ ነው፡፡ ለዛም ነው ሰራዊታችን ዛሬም ህዝባዊነቱን ጠብቆ የንጹሃንን እልቂት በመቀነስ አጥፊ ቡድኑን ነጥሎ ለማስወገድ ራሱን መስዋዕት እያደረገ በጥበብ እየተንቀሳቀሰ ያለው፡፡

ሰራዊታችን በዘራፊውና አምባገነኑ ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን ህግን የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ላይ እጅግ በረቀቀ መንገድ፣ ብስለት በተሞላበት አካሄድ በተመረጠና በተጠና ሁኔታ ጠላትን ለይቶ በማጥቃት አላስፈላጊ ጉዳት እንዳይደርስ በማሰብ ተልዕኮውን በጥንቃቄ እየፈጸመ ይገኛል የጀግንነት ጥግ ማሳያ ነው፡፡ ዛሬም ነገም ወደፊትም የድልና የኢትዮጵያዊነት ምልክት ሆኖ ይቀጥላል፡፡

ምላሽ ይስጡ