You are currently viewing ኢትዮጵያን አሸናፊ በማድረግ የነጻነት ቀንዲልነቷን ዳግም ለአለም እናበስራለን  !

ኢትዮጵያን አሸናፊ በማድረግ የነጻነት ቀንዲልነቷን ዳግም ለአለም እናበስራለን  !

  • Post comments:0 Comments

ኢትዮጵያን አሸናፊ በማድረግ የነጻነት ቀንዲልነቷን ዳግም ለአለም እናበስራለን  !

የአንድ አገር ሉአላዊነት የሚረጋገጠው ከአለም አቀፍ ህግጋት በላይ የዚያች አገር ሉአላዊ ክብር ሳይጣስና ሳይገሰስ መከበር እስከቻለ ድረስ ብቻ ነው፡፡ አገራት የተለያዩ አለም አቀፍ ስምምነቶች ውሰጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ በአለም አቀፍ ስምምነት ሽፋን የአገራቸው ሉአላዊነት እንዲጣስ አይፈቅዱም፡፡ አለም አቀፍ ስምምነቶችም ቢሆኑ የህግ ቅርጽ ይዘው ተፈጻሚ ሊሆኑ የሚችሉት እንደየአገሮች የህግ ስርአት በየአገሮቹ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ተቀባይነት ሲኖራቸውና ስምምነት ላይ ሲደረሱ ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የህግ ስርአት ማንኛውም አለም አቀፍ ስምምነት ተቀባይነት የሚኖረው በኢፌዴሪ ህገመንግስት መሰረት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እስከጸደቀ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም አካሄድ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡

ኢትዮጵያ በራሷ የውስጥ ጉዳይ ላይ ሙሉ ነጻነት ያላት ሉአላዊት አገር ናት፡፡ ይሁን እንጂ እኛ እናውቅልሻለን በሚል ፍላጎት የሚሞግቷት ተገዳዳሪ አቅም አልገጠማትም ወይም አይገጥማትም ማለት አይደለም፡፡ ይኸ አይነት ችግር በየታሪክ ምዕራፉ አጋጥሟታል፡፡ ዛሬም እንደጅብራ ከፊት ለፊቷ ተገትረው  የሚገዳደሯት ኃይሎች ቀላል አይደሉም፡፡ በተለይም ከሰብአዊ መብት አያያዝና ከአለም አቀፍ የሰው ልጆች ደህንነት ጋር በማያያዝ በእጅ አዙር ሊገዙንና ከቻሉም ሊጨፈልቁን የሚሽቱ በርካታ አገሮች አሉ፡፡ የሁሉም ፍላጎት ግን አንድና ተመሳሳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በኢትዮጵያውያን ሰብአዊ ጥቅም መከበር ሰበብ መጣስና ለኢትዮጵያ ታሪክ የማይመጥን ተንበርካኪ አውድ መፍጠር ነው፡፡

የኢትዮጵያ መሪዎች እንደወትሮው ሁሉ አፍሪካዊ ቃልኪዳናቸውን ጠብቀው በጽናት ቆመዋል፡፡ በኢትዮጵያ ክብርና ነጻነት አትምጡብን ማለታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ይኸ የመሪዎች አቋም በቀደሙ ዘመናት ሁሉ የተለመደ ኢትዮጵያዊ ቀለም ያለው የማይለወጥ ባህርይ ነው፡፡ ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ ለምን ወደጦር ግንባር ወረዱ በሚል የማይመሳሰሉ ነገሮችን በማያያዝ ሊተቿቸው የሚፈልጉ አለም አቀፍ ሚዲያዎች ፍላጎታቸው አንድን ነገር መከላከል ነው፡፡ ኢትዮጵያን በማንበርከክ ራሷን የቻለች አፍሪካ እንዳትፈጠር ማድረግ፡፡ እንደዶክተር አብይ አህመድ አይነት መሪዎች በአፍሪካ ምድር እንዲፈጠሩ ፈጽሞ አይፈለግም፡፡ ምክንያቱም አፍሪካ በባነነች ቁጥር የአውሮፓውያን ቅንጦትና ድሎት እየተመናመነ እንደሚመጣ ያውቁታል፡፡ ስለሆነም ተሟጋችና ጠያቂ መሪ በአፍሪካ ምድር እንዳይኖር ስውር ክልከላ ይደረጋል፡፡ ድንገት ብቅ የሚሉ ተራማጅ መሪዎች ከተገኙም የምዕራባውያን ሚዲያና የአለም አቀፍ ተቋማት ማዕቀብ ሰለባ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ ለዚህም የአውሮፓና የአሜሪካ የስለላ ተቋማት ከአንድ አንድ ተላላኪ የአፍሪካ አገራት የስለላ መዋቅሮች ጋር ተቀናጅተው ይሰራሉ፡፡ ዛሬም በአገራችን ኢትዮጵያና በመሪዎችዋ ላይ እየሆነ ያለው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡

ስለሰብአዊ መብትና ስለሰው ልጆች እኩልነት የሚያደነቁሩን ምዕራባውያን ለአፍሪካ ያላቸውን ንቀትና ዝቅተኛ ስሜት በተግባር ያውቁታል፡፡ አፍሪካ በየትኛውም የአለም መድረክ ያላት ስፍራ በእጅጉ ዝቅተኛ ነው፡፡ የእኩልነት መርህ ለአፍሪካ የቅንጦት ጥያቄ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ስለሆነም አፍሪካ መነቃቃት የለባትም፡፡ በአለም ከሚኖረው 7.5 ቢሊየን ህዝብ መካከል አፍሪካ ከኤዥያ አህጉር ቀጥሎ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ አህጉር ሲሆን 1.3 ቢሊዮን ህዝብ ይይዛል፡፡ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ድርሻ 114 ሚሊየን ይደርሳል፡፡ ይኸ ማለት ኢትዮጵያ በህዝብ ብዛት በአፍሪካ ከናይጀርያ ቀጥሎ 2ኛ በአለም ደግሞ 12ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ጉዳዩ የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጉዳይ ቢሆን ኖሮ አፍሪካም ሆነች ኢትዮጵያ በአለም አደባባይ የሚገባቸውን ክብርና ትኩረት ባገኙ ነበረ፡፡ ነገር ግን ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ እንደሚባለው የምዕራባውያኑ ቀልድ ያው የተለመደ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን በአጠቃላይ የአለም ጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ቀንዲል ናት፡፡ በአልበገርም ባይነት የምትታወቅ የአፍሪካውያን የነጻነት ተምሳሌትም ናት፡፡ ይኸንን የኢትዮጵያን ማንነት ጠብቆና አስጠብቆ መሄድ የመላ ኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ግዴታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከተንበረከከች በእርግጥም አፍሪካ ጨለማ አህጉር ይሆናል፡፡ የተስፋ ፍንጣቂ የማይታይበት በጭቆናና በድህነት የሚማቅቅ እድለ ቢስ አህጉር፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገሮች በውጭ ጣልቃ ገብነት ተበዝብዘዋል፡፡ ሆን ተብሎ ፖለቲካዊ መረጋጋት እንዳይኖራቸው ተደርጓል፡፡ በቅርቡ የተገደሉትን የሊቢያውን መሪ  ሙአመር ጋዳፊን ጨምሮ በርካታ መሪዎች በሴራ የተገደሉበት አህጉር ነው፡፡ በአፍሪካ ፈጽሞ መነቃቃት እንዲፈጠር የማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች ድንገት ቀና ብሎ የሚያገኙት አገር ካለ አንገቱን ለማስደፋት ምክንያት ይፈልጉለታል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ አንድና ተመሳሳይ ነው፡፡ የተለመደ የዴሞክራሲ ድብብቆሽና እንቆቅልሽ፡፡

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2011 ዓ.ም በርካታ የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት በጸደይ አብዮት  ሲመቱ ምክንያቱ የዜጎች ስራ አጥነትና የመንግስታት አምባገነንነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንጻራዊ መረጋጋትና ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ያሳዩ አገሮች የምዕራባውያንን ኩርኩም ቀምሰው ኩምሽሽ እንዲሉ ተደርገዋል፡፡ ወደእርስ በእርስ ጦርነት እንዲገቡና ያልተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ እንዲያስተናግዱ ግልጽ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል፡፡ ሊቢያ፣ ግብጽ፣ ሶርያንና የመንን ማስታወስ ከበቂ በላይ ነው፡፡ እነዚህ አገሮች ከ2011 በፊት የነበራቸውን አንጻራዊ መረጋጋትና ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ዛሬ ላይ ማግኘት አልቻሉም፡፡ ራሳቸውን ችለው መቆም የሚችሉ አገሮች አይደሉም፡፡ እርስ በእርስ መጠራጠር፣ መገፋፋትና መገዳደል የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡ አንድ አንዶቹም በምዕራባውያን የሚዘወሩ አሽከሮችና ተላላኪዎች ሆነዋል፡፡ የዜጎቻቸው ሰቆቃ በቃላት  የሚገለጽ አይደለም፡፡ ያፈረሱትን አንድነት መልሰው ለማግኘት በርካታ አስርተ አመታት ያስልጋቸዋል፡፡ ያወደሙትን ሀብት በማስላት ከመቆጨት ባሻገር በእድሚያቸው የሚመልሱት አይደለም፡፡ ከምዕራባውያን ሴራና ጣልቃ ገብነት ያተረፉት ነገር ቢኖር ዘላለማዊ ጸጸት ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያውያን መተው ከዘላለማዊ ጸጸት የሚገላግል ፍቱን መድሀኒት ነው፡፡ ፖለቲካዊ ችግራችንንም ሆነ በመካከላችን ያጋጠመንን ስንጥቅ በራሳችን አቅም እንፈታዋለን፡፡ ለጊዜው በመካከላችን የበቀሉትን አረሞች እኛው በራሳችን ጥረት ነቃቅለን እናስወግዳቸዋለን፡፡ ይህንን ለማድረግ በአረሞቹም ላይ ሆነ በሚወገዱበት ብልሀት ላይ የጋራ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያን በማዋረድ መላ አፍሪካውያንንና የአለም ግፉአንን ተስፋ ማስቆረጥ የለብንም፡፡ እንደጥንቱ ሁሉ የብርሀን ቀንዲልነታችንን ለአለም ህዝብ ማሳየት አለብን፡፡ ከመካከላችን እያፈነገጡ ለሉአላዊነታችን እንቅፋት የሚሆን ደባ የሚፈጽሙብንን ተላላኪ ባንዳዎች በአንድ ልብ ሆነን ልናወግዛቸው ይገባል፡፡ የውስጥ ችግራችንን በራሳችን አቅም መፍታት እደምንችል ለአለም ህዝብ ማሳየት አለብን፡፡ ተገደን የገባንበትን ጦርነት በድል አጠናቀን ድህረ ጦርነት የተናበበ የመልሶ ግንባታ ስራ መስራት ይኖርብናል፡፡

ከሽብር ቡድኑ የሽብር እንቅስቃሴ አንጻራዊ ነጻነቱን ጠብቆ በከፍተኛ ፍርሀትና ስጋት ውስጥ የኖረውና በከፋ ጭቆና ውስጥ ተደፍቆና ተጨፍልቆ የቆየውን ጭቁኑን የትግራይ ህዝብና በሽብር ቡድኑ ወረራ ስር ከልክ በላይ ሲማቅቅ የባጀውን መላውን ህዝባችንን ቁስል በማከም ከሁለንተናዊ ህመሙ እንዲያገግም ማድረግና የኢትዮጵያን አንድነትና ትንሳዔ ማረጋገጥ አለብን፡፡ ለአፍታም ቢሆን ተሳስተን ሊቢያ የመንና ሶርያ በቆሙበት ስፍራ ለመቆም መሞከር የለብንም፡፡ ኢትዮጵያን አሸናፊ በማድረግ የነጻነት ቀንዲልነቷን ዳግም ለአለም እናበስራለን ስንል አሸናፊነታችንን የምናረጋግጠው የሽብር ቡድኑን በመደምሰስና ዳግም የኢትዮጵያ አንድነት ጸር የማይሆንበት ደረጃ ላይ በማድረስ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ አሸናፊነት የሚረጋገጠው የህዝቦቿን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ነው፡፡ ስለሆነም ድህረ ጦርነት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የዜጎቿን ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት በጽኑ አለት ላይ እንመሰርታለን፡፡ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ የመሆናችንን ቃልኪዳን ዳግም እናድሳለን፡፡

 

 

Leave a Reply