“በብሔር ስም እየነገዱ ኢትዮጵያን ማሸበር ፈጽሞ አይቻልም” ከንቲባ አዳነች አቤቤ
**********************************************************************
“ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ በመንዛትና በብሔር ስም በመነገድ ኢትዮጵያን ማሸበር ፈጽሞ አይቻልም” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአሸባሪ ቡድኖችን የሽብር ተልዕኮ ማክሸፍ የኢትዮጵያዊያን የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አበቤ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከኢትዮጵያ ባለፈ የአፍሪካ ርዕሰ መዲናና ፤የዓለም ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባ በፕሮፓጋንዳ ለማሸበር የሚደረጉ ጥረቶች የሕልውና ዘመቻው ከመጀመሩ በፊት የነበሩ ናቸው ብለዋል።
ከሳምንታት በፊት የውስጥና የውጭ ሃይሎች አዲስ አበባ ስለመከበቧ ፕሮፓጋንዳ ሲነዙ ቢቆዩም፣ አዲስ አበባ ዛሬም ያለምንም ኮሽታ ዕለታዊ ክዋኔዋን መቀጠሏን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ የተከበበችው ሰርጎ ገቦችን ለመቆጣጠር በተጠንቀቅ በቆሙ የመንግስት የጸጥታ ሃይላት መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ወደ ከተማዋ የሚገቡና የሚወጡ ነገሮችን በሚገባ ማወቅ አስችሎናል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ህዝብ ከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት ያለው በመሆኑ ለአገሩ ህልውና አስቀድሞ ተነስቷል ያሉት ከንቲባዋ፤ መረጃ በመስጠት፣ አካባቢውን በመጠበቅ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በተቀናጀ አግባብ በመስራት በኩል ውጤታማ መሆኑንም ተናግረዋል።
ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን 6 ቢሊየን ብር ድጋፍ መደረጉን የጠቆሙት ከንቲባዋ ህዝቡ ተደራጅቶ አካባቢውን በንቃት እየጠበቀ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ምንም አይነት የፀጥታ ችግር ባይከሰትም አሸባሪ ቡድኑ በስልጣን ላይ እያለ ዛሬን ታሳቢ ያደረገ የክፋት ዕቅድ እንደነበረው ገልጸው፤ በከተማዋ ያቀዳቸው የክፋት ዕቅዶችና ማስፈጸሚያ ስልቶቹ ጭምር እየተጋለጡና እየከሸፉ መሆኑን አንስተዋል።
ለአብነትም በሺዎች የሚቆጠሩ በጦር ሜዳ ብቻ የሚያገለግሉ የነፍስ ወከፍ እና የቡድን ጦር መሳሪያዎች እንዲሁም ለሽብር ተዕልኮ የሚውል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መያዙን አንስተዋል።
“አሸባሪው ቡድን አዲስ አበባን ቢመኛትም፤ ተመልሶ ዳግም አይረግጣትም፤ ቅዠት ነው” ብለዋል።
አዲስ አበባን ለማሸበር ያቀዱትን ሴራ የማክሸፍ ስራውንም ህብረተሰቡና መንግስት በቅንጅት እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የአሜሪካ ኤምባሲን ጨምሮ አንዳንድ የዲፕሎማሲ ተቋማት ዜጎቻቸውን እና ባለሀብቶችን ከአዲስ አበባ እንዲወጡ ቤት ለቤት ሳይቀር እየዞሩ ቅስቀሳ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አንስተዋል።
በሌላ በኩል ከዕውነት ጋር የቆሙ የኢትዮጵያ ወዳጅ አገራትም በኤምባሲዎቻቸው በኩል አዲስ አባበ ሰላም መሆኗን መስክረዋል ነው ያሉት።
ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ክፍላተ ዓለማት የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ አባላት ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸውንና በኢትዮጵያም በነጻነት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን መናገራቸውን አንስተዋል።
ማንነትን መሰረት ያደረገ ማዋከብ እንዳለ በማስመሰል ከዕውነት የራቀ መረጃ የሚያሰራጩ አካለት መኖራቸውን የጠቀሱት ከንቲባዋ አንድም ሰው በብሔሩ ምክንያት አለመያዙን ገልጸዋል።
አሸባሪው የሕወሃት ቡድን በብሔር ሲነግድና ሲያስነግድ መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁን ግን ”በብሔር መነገድ ይበቃል፤ ሸብርተኛንም አንታገስም” ብለዋል።
በፕሮፓጋንዳና በሀሰተኛ መረጃዎች የሕግ ማስከበር ስራውን ማስቆምም ሆነ ኢትዮጵያን ማሸበር አይቻለም ብለዋል ከንቲባዋ።
አሸባሪ ቡድኑን በገንዘብና በሞራል መደገፍ በራሱ ወንጀል መሆኑን ጠቅሰው፤ በቁጥጥር ስር የዋሉትም የሽብር ቡድኑን ተልዕኮ ለማሳካት በገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ ተብለው የተጠረጠሩ እና የጦር መሳሪያ የተገኘባቸው አካላት እንደሆኑ ተናግረዋል።
ጉዳዩ አገር የማዳን የሕልውና ጉዳይ ነውና ማንም በፕሮፓጋንዳ እንደማይሸማቀቅ ይልቁኑም የሽብር ተልዕኮውን የማክሸፍ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጠል አረጋግጠዋል።
የሽብር ተዕልኮውን ለማክሸፍ የተሰሩ ስራዎችን ለማራከስ ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ መንዛት እና የመሪዎችን ንግግር ከዓውድ ውጭ በመተርጎም ችግር ለመፍጠር የሚደረገው እንቅስቀሴ ፍጹም ተቀባይነት እንደሌለውም ገልጸዋል።
ለአብነትም ከንቲባዋ ራሳቸው ከሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የተናገሩትን ከአውድ ውጭ በመተርጎም የተካሄደውን የተሳሳተ አካሄድ አንስተዋል።
ፈቃድ ወስደው የሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎችም ሆነ የማህበራዊ ሚዲያ ተዋናዮች ሀሰተኛ መረጃን ማስተጋባት ከሕግ ተጠያቂነት ባለፈ አገርንና ትውልድን የሚጎዳ በመሆኑ በሃላፊነት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የመሪዎችን ንግግር ከዐውድ ውጭ በማዛባት ማቅረብ የሽብር ቡድኖች የተካኑበት ልማዳቸው መሆኑን ጠቅሰው ያልተደረገን ተደረገ በማለትና የሰዎችን ንግግር ሆን ብለው በማዛባት የሚያሰራጩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ቀደም ሲል ከደጀን እስከ ግንባር ከነበረው ተሳትፎ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ጦር ግንባር ካመሩበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ መነቃቃት መፈጠሩን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባም ሆነ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለህልውና ዘመቻው እየሰጠ ያለው ምላሽ ታሪካዊ ነው ብለዋል።
ጦርነቱ በግንባር ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ እና በሚዲያ ግንባሮች የሚደረግ በመሆኑ መሳሪያ ይዞ ግንባር ላይ መሰለፍ ብቻ ሳይሆን ሁሉም እንደ መክሊቱ በሚችለው መስክ በመሳተፍ አገር የማዳን ትግሉን እንዲቀላቀል ጠይቀዋል።(ኢዜአ)
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!