ኢትዮጵያውያን አሁን…

ኢትዮጵያውያን አሁን…

  • Post comments:0 Comments
ኢትዮጵያውያን አሁን አንድ ሆነው ተነስተዋል።ትህነግ አንድ እንዳይሆን ሴራ ሲሸርብበት የነበረው ህዝብ ዛሬ አንድ ሆኖ ጠላትን ድባቅ እየመታ ነው።የፈራው አንድነት በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ጎልቶ መታየት ጀምሯል።
 
ከጥንት ጀምሮ በሀገራቸው ጉዳይ የማይደራደሩት ኢትዮጵያውያን አገር ሊያፈርሱ የመጡ ጠላቶቻቸው ወኔና ብርታት ሆኗቸው ስለአገራቸው አንድ ላይ ቆመዋል። ዛሬ ላይ ከዳር እስከ ዳር እየጠነከረ ያለውን ኢትዮጵያዊነት ለተመለከተ የአሸባሪው ትህነግ ዕድሜ እያጠረ መምጣቱን ያሳያል፤ የጠላት ሃይል የንጹሃን ደም አስክሮት መቀበሪያ ጉድጓዱን እያፋጠነ ነው።
 
ከጠላት ጋር የጀመርነው የህልውና ትግል በስኬት እንዲጠናቀቅ መላው ኢትዮጵያዊያን በግንባርም ሆነ ለሰራዊታችን የሚሆን ልዩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ እያሳየነው ያለነውን ህዝባዊ ደጀንነት አጠናክረው መቀጠልና ለሀገራችን ያለንን ከፍ ያለ ፍቅርና በምንም የማይለወጥ ታማኝነት በተግባር ማሳየት ይጠበቅብናል።
 
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ራሷን ለእጅ አዙር ቀኝ ግዛት ላለመገዛት እየተዋጋች ያለችው ከአሸባሪው ትህነግ ጋር ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ደካማና ተላላኪ መንግስት ተመስርቶ ያሻቸውን ለማድረግ ፍላጎት ካላቸው የውጭ ሀገር መንግስታትና ሀይሎች ጋር ጭምር ነው።
 
አንድ ሆነን ጠላቶቻችንን የምንመክትበት ጊዜ አሁን ነው። የሀገራችንን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ የመኖር ዋስትናችንን ማረጋገጥ ይገባናል። ህዝባችንን ሊበታትኑ፤ ሀገራችንን ሊያፈርሱ ጋብቻ መስርተው ቃል ኪዳን የተሳሰሩትን ሃይሎች ማስቆም የምንችለው አንድ ሆነን እንደ ህዝብ መታገል ስንችል ነው። የውጭም የውስጥም ጠላቶቻችን ያሰቡትን እንዳያሳኩ የምናርጋቸው አንድ ሆነን ስንታይ ነው።

Leave a Reply