You are currently viewing ” ኢትዮጵያ እንደለመደችው በአጭር ጊዜ አሸንፋ በጠላቶቿ መቃብር ላይ የክቡር ሰንደቋን ትሰቅላለች” – አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር

” ኢትዮጵያ እንደለመደችው በአጭር ጊዜ አሸንፋ በጠላቶቿ መቃብር ላይ የክቡር ሰንደቋን ትሰቅላለች” – አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር

  • Post comments:0 Comments
” ኢትዮጵያ እንደለመደችው በአጭር ጊዜ አሸንፋ በጠላቶቿ መቃብር ላይ የክቡር ሰንደቋን ትሰቅላለች”
– አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር
***********************************************************************
ኢትዮጵያ እንደለመደችው በአጭር ጊዜ አሸንፋ በጠላቶቿ መቃብር ላይ የክቡር ሰንደቋን ትሰቅላለች ሲሉ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በሁሉም መስክ የተግባር ሰዉ በመሆን፣ በጀግንነት በመቆምና መስዋዕትነት በመክፈል ዉዷ ሀገራችን ኢትዮጵያን እናጸናለን ብለዋል ባስተላለፉት መልዕክት።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያስተላለፉት መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል።
የኦሮሞ ህዝብ ትላንት እንደ ህዝብ የተወጋውን ውግ፣ የወጋውን ጠላትም ሆነ የተወጋበትን ጦር ይረሳ ዘንድ በፍጹም አይችልም፡፡ የተፈጸመብንን ግፍ፣ የተጎነጨነውን መራራ የመከራ ጽዋ፣ ተጭነው የገፉንን የግፍ እጆች፣ አንገታችንን ቆልምመው በሀፍረት ያስጎነበሱንን የወራሪዉ እና የአሸባሪዉን ትህነግ የባርነት መዳፎች፣ ከሰውነት ተርታ አውርደው ትቢያ ላይ የረገጡንን ጨካኝ እግሮቹን መቼም አንረሳቸውም፡፡
ገዳዮቻችን መግደላቸውን ቢዘነጉ ወይም ቢያዘናጉ እንኳ እኛ ግን ሞት እና አንባው- ዋይታው – ሰቀቀን እና እሪታው- ሀዘን እና መጎሳቆሉ መናቅ እና መበደሉ ከልባችን አለና አንዘነጋውም፡፡ ረስተን ሳይሆን ትተን፣ ለበቀል ሳይሆን ለይቅርታ ጀግነን ህዝብ እና ሀገርን ብለን የተውነው ጠላታችን ለሌላ ሞት፣ ለሌላ እንግልት፣ ለሌላ ስደት፣ ለሌላ ባርነት ሊያጨን ደም እና እውነት አላስቀምጥ ብለውት ከህጻን እስከ ሽማግሌ በማዝመት ለሁለተኛ ዙር ባርነት ቀንበር ሊጭንብን መደንፋት ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡
በመሆኑም ውጭ ካሉ ጌቶቹ እና እኛው ውስጥ ከተሰገሰጉ አሽከሮቹ ጋር ሀገር የማፍረስ ሰፊ ሴራ አሲረው በሰው ልጆች – ያውም በገዛ ወገን ላይ ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰብ ዘግናኝ ጭፍጨፋ እና እልቂት በንጹሀን ላይ እያደረሱ ለዳግም መከራ ሊያጩን መፍጨርጨራቸዉን ቀጥለዋል፡፡
ይህንኑ አደገኛ አካሄዳቸውን ተከትሎም ሰው በላውን ጁንታም ሆነ አሽከሩ ሸኔን አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት እና ከኢትዮጵያ ህዝብ ትከሻ ላይ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ነቅሎ ግብአተ መሬቱን ለማጠናቀቅ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትራችን ራሳቸው ግንባር በመዝመት ጦሩን ለመምራት እና በአጭር ጊዜ ውስጥ የታላቋን ኢትዮጵያ ታላቅ ድል ለመላ ኢትዮጵያውያን ለማብሰር የወሰኑትን ቆራጥ ውሳኔ እና ያስተላለፉትን ታሪካዊ ሀገራዊ ጥሪ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና መላው የኦሮሞ ህዝብ በፍጹም አድናቆት፣ ፍቅር፣ ክብር እና ተነሳሽነት ተቀብለውታል፡፡
የኦሮሚያ ክልል አመራሮችም የመሪያችንን ወቅታዊ እና ሀገራዊ ጥሪ በፍጹም ልበ ሙሉነት ተቀብለን፤ እኛም እንደ አባቶቻችን ሁሉ በክብር በደም እና በአጥንታችን መስዋዕትነት ከፍለን የተከበረች ሀገር ለልጆቻችን ለማቆየት እንዲሁም በልማት እና በአስተዳደር ስራ መስክም የላቀ ዉጤት በማስመዝገብ ሀገራችንን ከተጋረጠባት ፈተና ለመታደግ ዝግጁ መሆናችንን በቆራጥነት እናረጋግጣለን፡፡
የክልላችን ህዝብም የልጁን- የመሪውን እና ሀገር እና ህዝቡን ለመታደግ ጦር ሜዳ የወረደውን የዶክተር አቢይ አህመድ አሊን ጥሪ ተቀብሎ ሁሉም ከያለበት ነቅሎ በመውጣት የጠላቶቻችንን፤ የሸኔን እና የአሸባሪዉ የትህነግን ቀብር በመፈጸም ሀገራዊ ነቀርሳነታቸዉ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያከትም እንዲያደርግ ጥሪዬን በአክብሮት አስተላልፋለሁ፡፡
ትላንት ባዶ እጃቸውን ታንክ፣ መድፍ እና መትረየስ ፊት ቆመው ወያኔን ወደወጣበት ዋሻ የመለሱት ቄሮ እና ቀሬዎቻችን ዛሬም እንደገና ላስገብራቹ- እንደገና ልግዛቹ- እንደገና ልዝረፋቹ ብሎ የመጣውን ይህንን እብሪተኛ ሀይል ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የጠቅላይ ሚንስትራችንን ጥሪ ተቀብለው ነቅለዉ በመዉጣት ጀግናዉ የመከላከያ ሰራዊታችንን በመቀላቀል እና በጦር ሜዳ ጀብዱ የነ አብዲሳ አጋ፣ ባልቻ ሰፎ፣ ገረሱ ዱኪ፣ የጃጋማ ኬሎ ልጆች እንደሆኑ ዳግም እንዲያስመሰክሩ ታሪካዊ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ የመመከቱ ታሪካዊ ሀላፊነት እንዳለ ሆኖ በገባንበት ጦርነት ሳቢያ ሀገራችን ወደማንቆጣጠረው የከፋ የኢኮኖሚ ችግር እንዳትገባ ደጀን ህዝባችን ከሌላዉ ጊዜ በተለየ መልኩ በልማት ስራና በየተሰማራበት መስክ ሁሉ ውጤታማ ስራዎችን በመስራት፣ የአከባቢዉን ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ የዚህ ታሪካዊ ምእራፍ አሻራ ባለቤት እንዲሆን አደራ እላለሁ፡፡
በመጨረሻም ሁሉም ህዝብ በየእምነቱ እና አምልኮቱ ጥላ ስር ሆኖ በዱኣ እና በጸሎት ሀገሩን እንዲያግዝ ጥሪዬን አቀርባለሁ! ምንም ጥርጥር የለውም እግዚአብሄር ይረዳናል፡፡ ኢትዮጵያ እንደለመደችው በአጭር ጊዜ አሸንፋ በጠላቶቿ መቃብር ላይ ክቡር ሰንደቋን ትሰቅላለች፡፡ኢ.ፕ.ድ
አካባቢህን ጠብቅ‼
ወደ ግንባር ዝመት‼
ሠራዊቱን ደግፍ‼

ምላሽ ይስጡ