የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ህዝብ ሁሌም ያሸንፋል!
በአብዲ ኬ
አሁን ለገጠመን ፈተና ምላሽ የአገሬው ህዝብ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ እያሳየ ያለው ጀግንነትና ትብብር በእውነቱ የሚያኮራ ነው፡፡
እውቁ የአገራችን ፖለቲከኛ ሃይሌ ፊዳ፤ ከላይ በርዕሱ ላይ የጠቀስኳትን ሀረግ በተደጋጋሚ ይጠቀሙ ነበር ይባላል፡፡ “የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ህዝብ ያሸንፋል” የምትል አባባል ሁሌም ከአፋቸው አትጠፋም ይባላል፡፡ አሁን የገጠመን ህልውናችንን የሚፈታትን አደጋ ደግሞ በዚህ አባባል የተቃኘ ምላሽ ይፈልጋል፡፡
አንድ ህዝብ የተጋረጠበትን አደጋ፤ የሚደርስበትን ጭቆና፤ ወይም እኛን እንደገጠመን አይነት በውስጥና በውጭ ጠላት አገር ላይ የተደቀነን አደጋ መቀልበስ የሚቻለው በምልዓተ ህዝቡ የጋራ ትግል ነው፡፡
አንድ ህዝብ ደግሞ እንደ ህዝብ በጋራ የመጣበትን ህልውናውን የሚፈታተን አደጋ መመከት የሚቻለው ደግሞ፤ በጉዳዩ ላይ የጋራ ግንዛቤ ሲኖረው፤ አደጋውን መመከት በሚያስችለው ልክ ሲደራጅ እንዲሁም አደጋውን ለመመከት የሚያስችለውን ትጥቅ ሲታጠቅ ብቻ ነው፡፡ አሁን እንደ አገር የገጠመንን ጦርነት እና የተደቀነው የህልውና አደጋ ሊቀልበስ የሚችለው በዚሁ መንገድ ነው፡፡
መጀመሪያ የገጠመን ፈተና አገርን እንደ አገር፤ ህዝቡ የጋራ እሴት ኖሮት በአብሮነት እንደ አንድ ህዝብ የመቀጠልና ያለመቀጠል ህልውናችንን የሚፈትን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ይህ ፈተና የሆነ የአገራችን ክፍል ላይ እንደተከሰተ ቀለል ያለ ችግር አድርጎ ማየት ሳይሆን፤ የሁላችንም ህይወት ላይ የተደቀነ፤ ቤታችንና ቤተሰባችንን ሊያፈርስ እንደመጣ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህን መመከት የሚቻለው ደግሞ በተባበረ ክንዳችን ብቻና ብቻ መሆኑንም እንዲሁ፡፡
ይህ አደጋ የደቀነብን ጠላቶች ደግሞ እነማን እንደሆኑ፤ አላማቸው ምን እንደሆነ ብሎም ክፋታቸው ምንድረስ ሊዘልቅ እንደሚችል ጠንቅቆ ማወቅና የጋራ አቋም መያዝ ያስፈልገል፡፡
በመቀጠል ደግሞ፤ ወጥቶአደር፤ አርሶና አርብቶ አደር፤ ነጋዴ፣ የመንግስት ሰራተኛና የመሳሰሉ ሳይባል ሁሉም እንደሚመለከተው አውቆ፤ አደጋውን መመከት በሚያስችለው መንገድ መደራጀት ያስፈልጋል፡፡
በመጨረሻም አስፈላጊውን የቁስና የስነ ልቦና ትጥቅ መታጠቅ ግድ ይላል፡፡ ይህ ሲሆን ነው ሁሉም አቅሙን አሟጦ ከቤተሰቡ ጀምሮ ወገኑንና አገሩን ከአደጋ ለመታደግ የሚያስችለውን ማበርከት የሚችለው፡፡ ካልሆነ ሁሉም ማበርከት የሚችለውን እንኳን ማድረግ እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡
በዚህ ረገድ አሁን አሸባሪው ቡድን የደቀነውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በሁሉም ረገድ ያለው ህዝባዊ ተሳትፎ እጅግ የሚያኮረ ቢሆንም፤ አሁንም አሁን የመጣውን ጠላት ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለሚከጅለን ሁሉ ምንም አይነት ክፍተት ማግኘት እንደማይችል መልዕክት በሚያስተላልፍ መልኩ መንቃት፤ መደራጀትና አስፈላጊውን ትጥቅ መታጠቅ ይገባል፡፡