You are currently viewing ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነታችንና የነጻነታችን ምልክት  /በሚራክል እውነቱ/

ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነታችንና የነጻነታችን ምልክት /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments

ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነታችንና የነጻነታችን ምልክት

በሚራክል እውነቱ

ቀደም ባለው የአባቶቻችን ዘመን ማንም ሰው ጥፋት ሰርቶ ሲሄድ “ወድቃ በተነሳችው ሰንደቅ ዓላማ” ከተባለ ከአለበት አይንቀሳቀስም ነበር ይባላል፡፡ ይህ ለሰንደቅ ዓላማ የተሰጠውን ክብርና ምልክት ያሳያል፡፡በአሁኑ ወቅት ክቡር የሆነችው ሰንደቅ ዓላማ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለ ቦታዋና ያለ ሰዓቷ ተሰቅላ እናያታለን፤አያት ቅድመ አያቶቻችን ህይወታቸውን ሰውተው አጥንትና ደማቸውን ገብረው ያቆይዋትን ሰንደቅ ዓላማ የአሁኑ ትውልድም ሊያከብራት እና ሊጠብቃት ይገባል፡፡

ሰንደቅ ዓላማውን ያላከበረ ግለሰብም ሆነ ቡድን ለሰንደቅ ዓላማ የተከፈለውን መስዋዕትነት በውል ካለመረዳታቸው ባሻገር ውድ አገራቸውን ጠንቅቀው አላወቁም ማለት ነው፡፡አንዳንድ አካላት በተለይም ደግሞ በቡድን የተደራጁ ግለሰቦች ከራሳቸው ጥቅም በመነሳት እና የሚያነሷቸው ልዩ ልዩ ጥያቄዎች አልተፈቱም በማለት የማይታወቅ ሰንደቅ ዓላማን ከማውለብለብ ጀምሮ በሰንደቅ ዓላማ ላይ የሚያደርጉት ነገር ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ሊቆም ይገባዋል፡፡ መንግሥትም ለሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ያስፈልጋል፤ ሰንደቅ ዓላማ ተገቢው ክብር ሊኖረው ይገባል፡፡

ሰንደቅ ዓላማን በተመለከተ ሥርዓቱን ለማስከበር እንቅስቃሴ በሚደረግ ጊዜ መሰረታዊ የግንዛቤ ችግር እንዳለ ይታወቃል፡፡ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ የተቀደደ ሰንደቅ ዓላማ፣አሮጌ፣እንዲሁም ብሔራዊ በዓላት ከተከበሩ በኋላ መሬት ላይ መጣል እና ሰንደቅ ዓላማ መውጣትና መውረድ የሚገባው ሰዓትን አክብሮ አለመንቀሳቀስ ይስተዋላል፡፡

በመሆኑም ይህንን የተሳሳተ ግንዛቤ ለመለወጥ በዓመት አንድ ጊዜ በሰንደቅ ዓላማ በዓል ሰሞን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ወቅቶች በመገናኛ ብዙኃን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በተከታታይ ሊሰሩ ይገባል። ይህም ህብረተሰቡ በራሱ ሰንደቅ ዓላማን አክብሮና ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲጠቀምበት የህግ አስከባሪዎች ሥራም እንዲቃለል የሚያግዝ ይሆናል።

አንዳንድ የታሪክ ምሁራን እንደሚገልጹት ኢትዮጵያ በዓለም ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የሚያሰልፋት በአፍሪካ ደግሞ በቀዳሚነት የሚያስቀምጣት ከ3ሺ 500 ዓመት በላይ ያስቆጠረ የሰንደቅ ዓላማ ታሪኳ ነው የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ። ሰንደቅ ዓላማ ህዝቦች ማንነታቸውን የሚያንጸባርቁበት፣ አንድነታቸውን የሚያሳዩበት፣ የሉዓላዊነታቸውና የነፃነታቸው መገለጫ ምልክት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

የቀድሞ አባቶች የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው አድዋ ላይ የውጭ ወረራን ድል አድርገው ከራሳቸው አልፈው የጥቁር ህዝቦች ክብርና መንፈስ ከፍ እንዲል አድርገዋል፡፡ ይህ ትውልድም የውጭ ወራሪን ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ነፃነትንና እኩልነትን ለማስፈንና የአገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ ሊጠቀምበት ይገባል፡፡

በተለያዩ በዓላት፣ በህዝባዊ ሰልፎች፣ በስፖርታዊ ውድድሮች፣ በትምህርት ተቋማት፣ በንግድ ማዕከሎች ወዘተ ተሰቅለው የማያቸውን ብዙዎቹን ሰንደቅ ዓላማዎች ከሰንደቅ ዓላማ አዋጁ ድንጋጌዎች አንፃር ስናያቸው አዋጁና አተገባበሩ ለየቅል ሆኖ እናገኘዋለን።

«በአዋጅ 654/2001 ዓ.ም መሰረት የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ የራሱ ሥርዓት ያለው በመሆኑ ማንኛውም ዜጋ ህጉን መሰረት አድርጎ የሚገባውን ክብር መስጠትና መተግበር፤ ከህግ ውጪ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ አስፈላጊው እርምትና ቅጣት ሊወሰድ ይገባል። ለተግባራዊነቱም ሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ቢኖርበትም ፖሊስና ሌሎች የህግ አካላት በግንባር ቀደምትነት መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ግን ልብ ማለት ይገባል፡፡

 

ምላሽ ይስጡ