You are currently viewing የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ የያዘው አቋም በእውነታ ላይ የተመሰረተ አይደለም – ላውረንስ ፍሪማን

የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ የያዘው አቋም በእውነታ ላይ የተመሰረተ አይደለም – ላውረንስ ፍሪማን

  • Post comments:0 Comments
የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ የያዘው አቋም በእውነታ ላይ የተመሰረተ አይደለም – ላውረንስ ፍሪማን
የአፍሪካ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ተንታኝ የሆኑት ፕሮፌሰር ላውረንስ ፍሪማን ከከ ኦቢ ኤን እንግሊዝኛ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ላይ ማእቀብ ለመጣል ስለያዙት አቋም በስፋት አብራርተዋል።
ፍሪማን እንደገለጹት፤ ፕሬዚዳንት ባይደን በኢትዮጵያ ላይ ማእቀብ ለመጣል የሚያስችለውን የማስፈጸሚያ ትዕዛዝ የፈረሙት በዙሪያቸው ካሉት አማካሪዎች በሚያገኙት የተዛቡ መረጃዎች መሰረት ነው።
በእውነተኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ የሚደረግ ውሳኔ ባለመሆኑ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ብሎም ለመላው አፍሪካ አህጉር የሚተርፍ ችግር ይዞ እንደሚመጣም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ጉዳዩ ከአሜሪካ ብሄራዊ የጸጥታ ጥቅሞች ጋር የሚጋጭ በመሆኑ አደጋው ለአሜሪካም እንደሚተርፍ አስጠንቅቀዋል።
ይህ አይነቱ ውሳኔ 120 ሚሊዮን ህዝብ ላላት ኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካና ለሚመጡት የአፍሪካ ትውልዶችም አደጋ በመሆኑ የተሳሳተው የአሜሪካ ፖሊሲ እንዲስተካከል ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ፕሮፌሰር ላውረንስ ፍሪማን አመላክተዋል።
በማሊ፣ በናይጄሪያ፣ በቡርኪናፋሶ እየታዩ ያሉ ሰቆቃዎች በኢትዮጵያ መደገም እንደሌለባቸው የሚያነሱት ፕሮፌሰሩ፤ እነ ሱዛን ራይስ፣ አንቶኒዮ ብሊንከን፣ ሳማንታ ፓወርን ያካተተው የኦባማ አስተዳዳር በሊቢያ ሞዓመር ጋዳፊን ከስልጣን አስወግዶ ሀገሪቱን ቀውስ ውስጥ፤ ዜጎቿን የከፋ ችግር ውስጥ መክተቱን አስታውሰዋል።
የሰብአዊ ድጋፍ ጉዳዮችን ማንሳቱ ከሰው የሚጠበቅ መሆኑን ያስረዱት ፕሮፌሰሩ፤ “አስፈላጊውን ድጋፍ ለተጎጂዎቹ ማቅረብ መልካም ሆኖ እያለ የመቶ ሚሊዮኖችን ሃገር በማፍረስ ሙሉውን ምስራቅ አፍሪካ ችግር ውስጥ ማስገባት ግን የባይደን አስተዳደር ፖሊሲ ላይ ጥያቄ ያስነሳል” ብለዋል።
የባይደን አስተዳዳር አፍሪካን በሚመለከት ያላቸው ግንዛቤ እጅግ አነስተኛ መሆኑን በመጠቆም አሜሪካ በሌሎች ሃገራት ላይ የምትወስዳቸው ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጣልቃ ገብነቶች ሃገራቱን ከማረጋጋት ይልቅ እንዳይነሱ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።
አስተዳደሩ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚፈልገው ቻይናን ከአፍሪካ ለማራቅ ሲባል ብቻ መሆኑን የሚገልጹት ላውረንስ ፍሪማን፤ ጣልቃ ገብነቱ የየሃገራቱን ትውልዶች ከፍ ያለ ዋጋ እያስከፈሉ መሆኑን አፍጋኒስታን፣ ኢራቅና ሊቢያን ለማሳያነት አንስተዋል።
አሜሪካ እከተለዋለሁ የምትለውን ሊበራል ዴሞክራሲ በሌሎች ሃገራት ላይ ለመጫን የምታደርገው ጥረት ጭልጥ ያለ አምባገነን ስርአትን እንደሚፈጥር ያብራሩት ፕሮፌሰሩ፤ “ይሄን አይነቱ ስርአት ደግሞ አፍሪካ በሃገራቸው እሳቤ መሰረተ የሚመሩ ባለራእይ መሪዎች እንዳይኖራትና ሁልጊዜም እርዳታ ጠባቂ እንድትሆን ያደርጋል” ብለዋል።
የባይደን አስተዳደር ሃገራት በሚያደርጓቸው የመልማት ጥረቶች ላይ እንቅፋት በማስቀመጥ እንዳይሳኩ እየተደረገ መሆኑን ፕሮፌሰሩ አብራርተዋል።
አሸባሪው ህወሃት ለኢትዮጵያ ካወጣው ህገመንግስት ጋር ተላትሞ ማእከላዊ መንግስቱን ለማስወገድ በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘሩ ምክንያት የተጀመረው ጦርነት ይሄንን ችግር የፈጠረ መሆኑን ያስታወሱት ፕሮፌሰሩ፤ “ከ40 ሚሊዮን ህዝብ በላይ የመረጠው የኢትዮጵያ መንግስት ችላ ተብሎ ለአሜሪካ ግልጋሎት ሲሰጥ የነበረው ህወሃት ብቻ ሊደመጥ አይገባውም” ብለዋል።
አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ለትግራይ ክልል ንጹሃንና ህጻናት ሰላምና መረጋጋት ሲባል በትግራይ ያለውን ግጭት በክልሉ ካሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተነጋግሮ መፍትሄ ያበጅለታል የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተዋል።

ምላሽ ይስጡ