ዓለም ጆሮ የነፈጋቸው ድምጾች    /በሚራክል እውነቱ/

ዓለም ጆሮ የነፈጋቸው ድምጾች /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments
ዓለም ጆሮ የነፈጋቸው ድምጾች
/በሚራክል እውነቱ/
 
አሸባሪው የህወኃት ቡድን የሠራዊቱን ሃገራዊ ፍቅሩንና ብሄራዊ ክብሩን በማዋረድ ሠራዊቱን በዘርና ኃይማኖት በመከፋፈል የእኩይ ዓላማው ማስፈጸሚያ ለማድረግ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም፡፡ ይህ እኩይ ዓላማው አልሳካለት ቢል ጥንት አባቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት ያላስደፈሯትን አገር እንደ ሶሪያ፣ የመን፣ ሊቢያ ዶግ አመድ የማድረግ ቅዠት ውስጥ ገብቷል፡፡
 
ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ከውጭ ወራሪ ሃይል ሲጠብቀው የነበረውን የመከላከያ ሰራዊታችንን ከጀርባ ሆኖ ከመውጋት ባለፈ ንጹሃንን በግፍ ገድሏል፤ ለእንስሳትም የማይራራ የአውሬ ቡድን መሆኑን በተግባር አሳይቷል፡፡
አሸባሪው የህወኃት ቡድን በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ ጡዘት ሰማይ እንዲነካ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በክልሎች መካከል ቁርሾ በመፍጠር እርስ በእርስ መተማመን እንዲጠፋ፤ አገራዊ አንድነት እንዲሸረሸር አለፍ ሲልም ህዝቡ እንዲተላለቅ ሴራ ሲሸርብ ቆይቷል፡፡ አገሪቱን የወንበዴዎች መናኸሪያ ለማድረግ ምንም አይነት ህገ መንግስታዊ መሰረት የሌለውን አሰራር በመዘርጋት የአንድ አገር ህዝቦችን እርስ በእርስ ውጥረት ውስጥ እንዲገቡ ሲያደርግ ነበር፡፡
ይህ በጥቅም የተሳሰረው አሸባሪው የህወኃት ቡድን ወንድማማቾችን በጦርነት የማፋጀት የፖለቲካ ሴራ ከድርጅቱ ምስረታ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ዓላማ አድርጎ ይዞታል፡፡ ይሄው አሸባሪው ቡድን የኢትዮጵያን ዕድገትና መለወጥ ከማይፈልጉ ሃይሎች ጋር በመስራት ጸረ-ኢትዮጵያዊነቱን በገሃድ ቢያሳይም በአጭር ጊዜ ውስጥ በጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን፣ ልዩ ሀይላችንና ሚሊሻችን እንዲሁም በመላው ህዝባችን ድጋፍ የዚህ የሽብር ቡድን እቅድ ቅዥት ሆኖ እንዲቀር ማድረግ ተችሏል፡፡
 
ኢትዮጵያ የምትፈልገው በትብብር መስራት እና ብልጽግናዋን ማረጋገጥ እንጂ በየትኛውም ሁኔታ ልማቷን ሊያስተጓጉል የሚችል ጎታች አካሄዶችን እና ጸረ-ልማት እንቅስቃሴዎችን ዛሬም ሆነ ነገም ፈጽሞ አትቀበልም፡፡
 
የትኛውም ሃይል በጉልበትም ሆነ በተለያዬ መንገድ በኢትዮጵያችን ጥቅም እና ክብር የሚመጣ ከሆነ ኢትዮጵያዊያን ከፊት ቀድመው ለመሰለፍ እና ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ማንም አይቀድማቸውም፡፡ጀግንነትና አገር ወዳድነት ከደማቸው ነውና፡፡
 
ግራና ቀኝ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ከማይፈልጉ ሃይሎች ጋር እየሰራ የሚገኘው እና ግማሽ አካሉ መቃብር ውስጥ የሚገኘው አሸባሪው የህወኃት ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች በሚገኙ የሐይማኖት ተቋማት፣ የመንግስትና የግለሰብ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት አድርሷል፡፡ ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ህጻናትን አስገድዶ ደፍሯል፤ በአሰቃቂ ሁኔታ በጅምላ ገድሏቸዋል፡፡
 
ጧሪና ቀባሪ የሌላቸው አቅመ ደካሞችንና የሐይማኖት አባቶችን ስቃይና እንግልት ከማድረሱም በላይ በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል አፈር ሳያለብስ በአንድ ጉድጓድ ውስጥ በመጣል የጅብ እራት እንዲሆኑ ፈርዶባቸዋል፡፡ ነፍሰ ጡር ሴቶችን ያለ ርህራሄ በመድፈር እና በመግደል ህወኃት አሸባሪነቱን በተግባር ቢያሳይም አገራት ግን ደፍረው ከእኩይ ተግባሩ እንዲታቀብ እንኳ ድምጻቸውን ማሰማት አልቻሉም፡፡
 
መሽቶ መንጋቱ እንደማይቀር ሁሉ እየገጠሙን ያሉ ፈተናዎችን በጥረታችን ተሻግረን ለብልጽግና መብቃታችን እሙን ነው፡፡ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ዳግም ወደ ከፍታ ያመራሉ፡፡ የውስጥ ተላላኪዎቻችንን ጫና ተቋቁመን አንገታችንን ቀና የምናደርግበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፤ ያኔ የውስጥም የውጭም ጠላቶቻችን በተራቸው ያፍራሉ፤ ይሸማቀቃሉ፤ አንገታቸውን ይደፋሉ፡፡

Leave a Reply