You are currently viewing የተጋረጡብንን ፈተናዎች አልፈን ህልማችንን ዕውን እናደርጋለን! /በሚራክል እውነቱ/

የተጋረጡብንን ፈተናዎች አልፈን ህልማችንን ዕውን እናደርጋለን! /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments
የተጋረጡብንን ፈተናዎች አልፈን ህልማችንን ዕውን እናደርጋለን!
/በሚራክል እውነቱ/
 
እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት የለውጥ ዓመታት በዓይን የሚታይ፣ በእጅ የሚዳሰስ ለውጦችን በሁሉም መስኮች ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊውንና ፈጣኑን የለውጥ ሃዲድ መነሻ አድርጋ የብልፅግና ማማ ላይ ለመድረስ የሚያስችላትን እሳቤ እና ትልም ይዛ በምትንቀሳቀስበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ከውስጥም ከውጭም ጠላቶቿ ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ከገባች ውላ አድራለች፡፡
 
በዚህ የለውጥ ጉዟችን አይናቸው ደም የለበሱ ሀይሎችና ቡድኖች በተለያየ መንገድ ከለውጡ ሀዲድ እንድንወጣና ዛሬም እንደትናንቱ አብሮነታችን ላይ ጥላ ሊያጠሉ፤ አንድነታችንን ሊበትኑ እንቅልፍ አጥተው በግራና በቀኝ ትንኮሳቸውን ቀጥለዋል፡፡
 
የስልጣን ጥማት እንቅልፍ ቢነሳቸው፣ አላስቀምጥ አላስቆም ቢላቸው ዕድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሱ የነገ አገር ተረካቢ ታዳጊዎችን ጦርነት ውስጥ በመማገድ ያለዕድሜያቸው ለእነሱ ፍላጎት እንዲሰዉ፣ አካል ጉዳተኛ እንዲሆኑ እና የስነ ልቦና ጉዳት እንዲደርስባቸው ከማድረጉም በተጨማሪ ዓመታትን ደክመው ያሳደጓቸውን ወላጆች ያለ ጧሪ ቀባሪ እንዲቀሩ አሸባሪው የህወኃት ቡድን ፈርዶባቸዋል፡፡
 
አገር ከምንም ከማንም በላይ ናት፤ ጥላ ከለላ ናት፤ ለሃያ ሰባት ዓመታት በማን አለብኝነት የአገሪቱን ሃብት ንብረት ሲዘርፍ የኖረው አሸባሪው የህወኃት ቡድን ጥጋብ ደረቱን ቢነፋው እና ከማዕከላዊ መንግስት መነሳቱ እንደ እግር እሳት ቢያቃጥለው ዛሬም ድረስ ትልቁን የኢትዮጵያዊነት ምስል ለማደብዘዝ ሲኳትን ይታያል፡፡
የህዝብን ሰላም በማሳጣት የአገር አንድነትን ለመበጣጠስ በገሃድ ተንቀሳቅሷል፡፡ ዓለም ወደ አንድ መንደር እየተሰበሰበች ባለችበት በዚህ ዘመን አሸባሪው የህወኃት ቡድን የብተና ፖለቲካ ሲያራምድ የኖረ ዛሬም ከዚህ ባህሪው ሳይላቀቅ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን በማቀንቀን ህዝብን ለግጭት ሲዳርግ ዓለም በግልጽ ተመልክቷል፡፡
 
አቋሙ በምንም ሁኔታ የማይለዋወጥ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት ለመገንባት ሌት ተቀን የሚጥረው ብልፅግና ትክክለኛና እውነተኛ ፌደራሊዝም እንዲተገበር አበክሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
 
እጅግ ተለዋዋጭና ፈታኝ ችግሮች ቢደራረቡም፣ አይን ያወጣ መድሎና ወደ አንድ ወገን ያጋደሉ አለም አቀፍ ውሳኔዎች ቢሰጡም ህዝቡ ብልፅግና ፓርቲ ከሚመራው መንግስት ጎን በመሆን የሕግ የበላይነት እንዲከበርና ሕገ ወጦች አደብ እንዲገዙ፣ የውስጥ ተላላኪዎች ከውጭ ሃይሎች ጋር ተዳምረው የሚፈጥሩትን ጫና ለመቀነስ ከምንጊዜውም በላይ አንድነታችንን ልናጠነክር ይገባል፡፡
ዘመን ተሻጋሪ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ውጤት ለማምጣት ርብርብ እያደረገ የሚገኘውና የህዝብ የሆነው ብልጽግና ፓርቲ እጅግ ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እያለ እንኳ መሰረታዊና ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገቡን ቀጥሎበታል፤ ዳሩ ከሰራቸው ስራዎችና ካመጣቸው ለውጦች ይልቅ ገና ወገብ የሚያጎብጡ አያሌ የቤት ስራዎች ቢኖሩበትም፡፡
 
ኢትዮጵያዊያን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ለህግ የበላይነት በሁሉም ቦታ መከበር፣ ወንድማማችነትን በማጎልበት ፈተና የማያላላው አንድነታቸውን ይበልጥ እንዲያጠነክሩ፣ እንደ አገር ለሚገጥሙን ፈተናዎች በጋራ መመከት እንድንችል በተደራጀና ለውጭ ሃይሎች ክፍተት በማይፈጥር መልኩ መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡
 
ሀገራዊ ጉዳዮች ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው አጀንዳ መሆኑን በአግባቡ ተረድተን ትኩረት መስጠት ከቻልን እና ለጋራ ብልፅግና በጋራ መነሳት ከቻልን በሩቅ ያየነውን ብልጽግና እዚሁ በኢትዮጵያችን ላይ ዕውን ሆኖ እናየዋለን፡፡
 
በሠለጠነና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሕዝብን አደራጅቶ በፅናት ከመታገል ይልቅ በጉርሻ በመደለል አገር ለማፍረስ መንቀሳቀስ፣ በህዝቦች መካከል ልዩነቶችን ለመፍጠር መሞከርና ሁከትና ብጥብጥ ማስነሳት የአሸባሪው የህወኃት ቡድን እና የአንዳንድ ባንዳዎች መለያ ቢሆንም ይህ እኩይ ዓላማ በኢትዮጵያውያን የጋራ ትብብር ዕውን እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡
 
ወቅቱ ኢትዮጵያችን በበርካታ ውስብስብና ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ የተከበበች መሆኑን በውል ተረድተን አንድነታችንን ይበልጥ ማጠናከርና ከመንግስታችን ጎን ሆነን ድምጻችንን ማሰማት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነው፡፡
 
በጣረ ሞት ላይ የሚገኘው አሸባሪውን የህወኃት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አፈር ልሶ እንዳይነሳ እስከወዲያኛው በመሸኘት በመላ አገሪቱ የሰላም አየር እንዲነፍስ ዛሬውኑ ከሰራዊታችን ጎን ልንሆን ይገባል፤ ይህን ማድረግ ስንችል ለሁሉም ዜጎቿ እኩል የሆነችና የምትመች ፣ ብልጽግናዋ የተረጋገጠ፣ ህዝቦቿ በፍቅርና በመተሳሰብ የሚኖሩባት ዴሞክራሲያዊት አገር መፍጠር እንችላለን፡፡

ምላሽ ይስጡ