ሁላችንም ወታደሮች ነን!
በጦር ግምባር ተሰልፎ አገርና ህዝብን ከወራሪ መታደግ ትልቅ ክብር የሚያሰጠው ተግባር መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ብዙዎች ከአሁን የግል ፍላጎትና ምኞታቸው ይልቅ አገርን አስቀድመው በዚህ መንገድ ለሌሎች ብርሃን ሆነው አልፈዋል፡፡ ዛሬም በርካቶች በዱር በገደሉ ስለአገራቸው እየተዋደቁ ይገኛሉ::
ትውልድ ሲዘክረው በሚኖር የውትድርና ህይወት አካል መሆን ያልቻለ ማንኛው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ዛሬ አገራችን የገባችበትን ተደራራቢ ችግር ለመሻገር በተሰማራበት መስክ ወታደር ሆኖ አገርን ማገልገል ይጠበቅበታል፡፡
አገራችን ጦርነት ላይ ናት፡፡ ጦርነቱ ከውስጥም ከውጭም ነው፡፡ የተጋረጠብን ችግር ማለፊያ መንገድ ሃቀኛ የወታደራዊ ስነልቦና መላበስ ነው፡፡ ነጋዴው አገራችን ያለችበትን ሁኔታ በአግባቡ ተረድቶ እያንዳንዱ እንቅስቃሴው አገር ከማዳን፤ ከመጠበቅ አንፃር እንጂ በዚህ ወቅት አላግባብ ትርፍ ለማጋበስ በመባዘን መሆን አይገባውም፡፡
በመንግስትም ሆነ በግል ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ ለአገሩ ወታደር በመሆን፤ ህዝቡን በቅንነት በማገልገል፤ ለሚሰጠው አገልግሎትም ታማኝ በመሆንና በጊዜ የለኝም ስሜት እንዲሁም በበለጠ የስራ ተነሳሽነት መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ዲያስፖራውም በተመሳሳይ አገራችን የተጋረጠባትን የውጭ አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት አገሩን ማገዝና መደገፍ የዜግንነት ግዴታ አለበት፡፡
በጥቅሉ ሁላችንም በየተሰማራንበት የስራ መስክ በታማኝነት ለአገር ቆመን በመስራት የአገር አንድነትና ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ የህይወት መስዋዕትነት ከሚከፍሉት እኩል ወታደሮች መሆን ይጠበቅብናል፡፡ ሁላችንም ለአገራችን ወታደሮች ነን፡፡ መከፋታችን፣ ደስታችን ሁሉም በአገር ላይ ነው ጣእም ያለው፡፡ ከአገር በላይ ምንም የለምና አገራችንን ወታደሮች ሆነን በመጠበቅ የገባንበትን ሁለንተናዊ ችግር በጋራ መሻገር ይገባናል፡፡