You are currently viewing ከቀደምት አባቶቻችን የተረከብናትን አገር ሉዓላዊነት ለማስቀጠል እንታገላለን

ከቀደምት አባቶቻችን የተረከብናትን አገር ሉዓላዊነት ለማስቀጠል እንታገላለን

  • Post comments:0 Comments
ከቀደምት አባቶቻችን የተረከብናትን አገር ሉዓላዊነት ለማስቀጠል እንታገላለን
ከቀደምት አባቶቻችን የተረከብናትን አገር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር እንታገላለን ሲሉ በጦላይ ማሰልጠኛ ማዕከል መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና ላይ የሚገኙ ምልምል እንስት የሠራዊት አባላት ገለጹ።
ለኢዜአ ሃሳባቸውን ያጋሩት እንስቶቹ ምልምል የሠራዊት አባላት የአገር መከላከያ ሠራዊት ፍጹም ኢትዮጵያዊነት የሚንጸባረቅበት ተቋም ነው ይላሉ።
ይህም “ከራስ በፊት ለሕዝብ” የሚለውን መርህ በመላበስ ለአገር ሉዓላዊነትና ለሕዝብ ሠላም መጠበቅ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
ምልምል ወታደር ብዙ አለማየሁ ኢትዮጵያ ለዘመናት ሉዓላዊነቷ ተከብሮ የቆየች፤ ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች አገር ባለቤት ነች ስትል ገልጻለች።
የአሁኑ ትውልድም የአባቶቹን የቃልኪዳን አደራ በመረከብ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ማስረከብ ይጠበቅበታል ብላለች።
የኢንጂነሪንግ ተማሪ እንደነበረች የገለጸችው ምልምል ወታደሯ ለአገር ሉዓላዊነት መጠበቅ የበኩሏን ለመወጣት መስዋዕትንነት ለመክፈል መዘጋጀቷን አረጋግጣለች።
ምልምል ወታደር ኢማን ዋሱ በበኩሏ ኢትዮጵያ ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን ነፃ እንድትወጣ በመሻት የአገር መከላከያ ሠራዊቱን መቀላቀሏን ገልጻለች።
ለሀገሬ አለሁላት የምትለው ኢማን ቀደምት አባቶች ያስረከቧትን ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች አገር ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን ተናግራለች።
ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ለአገር ሉዓላዊነት መከበር የመከላከያ ሠራዊቱን በመቀላቀል ለአገራቸው ዳር ድንበር መከበር እንዲተጉም ጥሪዋን አቅርባለች።
ለአገር ሉዓላዊነት መከበር ለሚከፈል ዋጋ አንዳች ቁጭት የለም ያለችው ደግሞ ምልምል ወታደር መቅደስ ታምሬ ነች።

ምላሽ ይስጡ