You are currently viewing ክቡር አቶ አብርሐም አለኸኝ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽቤት ኃላፊ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት

ክቡር አቶ አብርሐም አለኸኝ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽቤት ኃላፊ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት

  • Post comments:0 Comments
ክቡር አቶ አብርሐም አለኸኝ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽቤት ኃላፊ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል እንትታነቡት ተጋብዛችኋል፡፡
**************************************************************************************
 አንድ የታጠቀ ሚሊሻ ለአገሩና ለህዝቡ ሲል፣የአገሩንና የህዝቡን ውርደት መቋቋም አልችል ሲል፤ጠላትን እያርበደበደ፣እያንቀጠቀጠ ብቻውን 20ና 30፤እየገደለ የሚሰዋበት የትግል መድረክ ነው፡፡የኮኪት አርሶ አደርና ሚሊሻ፣ ይህን ጀብድ ፈጽሟል፡፡የቆቦ አርሶ አደር እና ሚሊሻው ይህን ጀብድ ፈጽመዋል፡፡የሐራ አርሶ አደርና ሚሊሻው፣የግዳን አርሶ አደርና ሚሊሻው ይህንን ጀብድ ፈጽመዋል፡፡
 ሰሜን ጎንደርና ምዕራብ ጎንደር እነዚህ ድሎች እየታዩበት ያለ የጀግንነት መድረክ፤ጀብደኝነት የሚተረክበት፣በተግባር የሚኖርበት መድረክ ሆኗል፡፡
 የምስራቅ ጎጃም አርሶ አደሮች ብሬናንና ዲሽቃ የሚማርኩበት፣የደቡብ ጎንደር አርሶ አደሮች ብሬንና ዲሽቃ ከያዘ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው ጠላት የሚገሉበት፣የሰሜን ሸዋ አርሶ አደሮች፣የኦሮሞ ብሔረሰብ አርሶ አደሮች ጀብድ የሚፈጽሙበት፣የአዊ ብሔረሰብ አርሶ አደሮች፣የሰቆጣ ወጣቶች፣ሚሊሻዎች ከጠላት ጋር ፊት ለፊት የሚተናነቁበት የታሪክ መድረክ ነው፡፡እነዚህን ታሪክ ያነሳቸዋል፡፡
 የወልዲያ ወጣቶች፣የመርሳ ወጣቶች፣የደብረ ታቦር ወጣቶች፣የንፋስ መውጫ ወጣቶች ታሪክ ሊዘነጋችሁ አይችልም፡፡
 ጋሸና ላይ ያሉ ታጣቂዎች የሰሩት ጀብዱ ቀላል አይደለም፤የሰሜን ወሎን የራያን ጢነኛ የሰራው ፣የደሴን የባህር ዳርን፣የጎንደርን የምዕራብ ጎጃምን አርሶ አደር ሚሊሻ ጀግንነት ገልጾ መጨረሽ አይቻልም፡፡
 የሰሜን ጎንደር፣የደቡብ ጎንደር፣የምዕራብ ጎጃም፣የጎንደር ፋኖ የሰራውን ጀግንነት በቀላሉ ማብራራት አይቻልም፡፡
 የደቡብ ወሎ ሚሊሻዎች ከጫፍ እስከ ጫፍ ተነስተው ከመከላከያ ሰራዊታችን ጋር ተቀላቅለው፣ከልዩ ሃይላችን ጋር ተቀላቅለው ታሪካዊ ጀብዱ እየፈጸሙ የምንገኝበት መድረክ ላይ ነው ያለነው፡፡
 የወርቄ አርሶ አደር ተናግረህ ተናግረህ የማትጨርሰው የጦርነት ጀብዱ እየፈጸመ ያለ አርሶ አደር ነው፡፡እስካሁኗ ሰዓት ድረስ ቀየውን ያላስደፈረ አርሶ አደር ነው፤ታንክ ቢመጣ፣ መድፍ ቢመጣ እማይበገር አርሶ አደር፤እስካሁኗ ሰዓት ድረስ ከጠላት ጋር የሚተናነቅ አርሶ አደር፣እንዲህ አይነት አርሶ አደሮች፣እንዲህ አይነት ጀግኖች የሞሉበት አገር፣የሞሉበት ምድር ላይ ነው ያለነው፡፡
 ያ የአፋር ጀግና የሰራውን ጀብድ ሁላችንም እናውቃለን፤ጥይቱን ጨርሶ ራሱን ለመሰዋት ወስኖ ታንክ ላይ በመውጣት ታንክ እስከመማረክ የደረሰ ጀግና ነው፡፡ዛሬ የአማራ ክልል መሬት፣የአፋር ክልል መሬት የኢንዚህ ጀግኖች ውሎ እየተረከ ነው የሚገኘው፡፡
 ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት፣የአማራና የአፋር ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻ፣ወጣቶች በሚያደርጉት የህለውና ትግል ውስጥ ህይወታቸውን ሳይሰስቱ በመገበር ጠላትን በሁሉም አካባቢ አከርካሪውን እየመቱ ይገኛሉ፡፡
 የኢትዮጵያን ህልውና ለመታደግ፣የግዛት አንድነታችንን ለመጠበቅ መስዋዕትነት የሚከፍሉ ጀግኖች ብዙ ናቸው፡፡የሶማሌ ልዩ ሃይል፣የኦሮሚያ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ፣የአፋር ልዩ ሃይልና ሚሊሻ፣የሐረሪና የድሬዳዋ ልዩ ሃይል፣የሲዳማና የደቡብ ልዩ ሃይል እየከፈለ ያለ መስዋዕትነት ቀላለወ አይደለም፡፡
 በዚህ ሁሉ የጦር ውሎ በርካታ ጀግንነት ተመዝግቧል፤ጋምቤላ በርካታ ጀግኖችን አሰማርቷል፤እነዚህ ጀግኖች ትልልቅ ጀብዱ እየፈጸሙ ነው፡፡የቤንሻንጉል ጉሙዝ ጀግኖች በየአውደ ግንባሩ መስዋዕትነት እየከፈሉ አገርን ከመፈራረስ እየጠበቁ ነው፡፡
 ይሔ ጦርነት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት በመጠበቅና በማስጠበቅ ላይ ብቻ የተመሰረተ ሳይሆን የኢትዮጵያዊያንን አንድነትም ያበሰረ ነው፡፡
 ወያኔ ጦርነቱን ለሆነ ቡድን ቆርሶ ለመስጠት ፈልጎ ነበር፤ ወያኔ ጦርነቱን በሆነ ህዝብ መካከል ለማድረግ ፈልጎ ነበር በለመደው የሴራ ትንታኔ፣በለመደው የሴራ ፖለቲካ ፣ትናንት እንደከፋፈለን ዛሬም ሊከፋፍለን ታች ላይ ብሎ ነበር አልተሳካለትም፡፡
 በዚህ ጦርነት መላው ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንን በተግባር አረጋግጠናል፡፡አንድነታችንን በደማችን በመስዋዕትነታችን አረጋግጠናል፡፡ደማችንን አንድ ላይ አፍሰናል፤አጥንታችንን አንድ ላይ ከስክሰናል፣የጀብደኝነት ስራችንንም አንድ ላይ አረጋግጠናል፡፡
 ጀግንነታቸውን፣ኢትዮጵያዊነታቸውን አገር አይፈርስም ህዝብ አይጎሳቆልም ብለው ታሪካቸውን በሁሉም የጦር አውድ ጽፈዋል፡፡አብረን እንደኖርን ሁሉ አብረን እየሞትን፣አብረን እየተቀበርን የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ የቃል ኪዳን ውላችን አስረናል፡፡ይሄ ጦርነት በርካታ ልምድ የተገኘበት ጦርነት ነው፣ይህ ትልቅ የታሪክ አውድ ነው፡፡
 እነዚህ ጀግኖች አገራቸውን ከመፈራረስ ለማዳን ፣ህዝባቸውን ከመጎሳቆል ለማዳን ያልከፈሉት መስዋዕትነት የለም፡፡በአጠቃላይ ስማቸውን ዘርዝረን የማንጨርሳቸው ጠላት በገባበት ምድር ሁሉ እረፍት ሳይሰጡ በተሰበሰበበት በቦንብ በማቃጠል ጠላትን አሳዶ በመግደል ከጠላት ጋር ፊት ለፊት በመታገል ህዝብና አገር የሰጣቸውን ተልዕኮ በጀግንነት የሚፈጽሙ የልዩ ሃይል አባላት፣የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ሚሊሻ አባላት የተቆረቆሩ ወጣቶች ቀላል አይደሉም፡፡
 ወጣቶች እየዋሉ እያደሩ አምቢ ለአገሬ እምቢ ለህዝቤ አይኔ እያዬ ጠላት የበላይነት ሊያገኝ አይገባም ብለው ታሪካዊ መስዋዕትነት እየፈጸሙ ነው የሚገኙት፡፡እነዚህ ወጣቶች፣እነዚህን ሚሊሻዎች፣እነዚህ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላትና የልዩ ሃይል አባላት፣አርሶ አደሮችን ሴቶችን በምን ሚዛን ነው አመስግነን የምንጨርሰው፤እጅግ በጣም ከባድ ነው፣ታሪክ ግን ሁሌም ያመሰግናቸዋል፡፡በወርቅ ቀለም የተጻፈ ጀብዱ ፈጽመዋልና ትውልድ ያስታውሳቸዋል፡፡
 የክልላችን መንግስት አሁንም ጠላትን ለሚመቱ ወጣቶች፣ጠላትን ለሚያብረከርኩ የአገራችን አርሶ አደሮች የማረኩትን ሰለባ እንዲወስዱ ፈቅዶላቸዋል፡፡ይሄ ሰለባ ክላሽም ይሁን መትረጌስ ታሪካዊ ቅርስ ነው፡፡ተራ ንብረት አይደለም፣የአርበኝነት ውሎ ውጤት ነው፡፡ስለሆነም ክላሽ ለማግኘት ወይም ሌላ የጦር መሳሪያ ለማግኘት የምናደርገው ትንቅንቅ አይደለም፣የአገር አንድነት ለመጠበቅ የአማራን ህዝብ ከጉስቁልና ለማውጣት ህልውናችንን ለመታደግ ባደረግነው ታሪካዊ ትግል የተገኘ ታሪካዊ አሻራ ነው፡፡ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ ነው፤ዛሬ እንድንወስደው የተፈቀደልን የጦር መሳሪያ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በቅርስነት ተመዝግቦ ለኢትዮጵያዊያን የጀግንነት ምልክት ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡
 ከዚህ በኋላ ዒትዮጵያን ፣ከዚህ በኋላ የአማራ ክልልን ጠላት እንዳይደፍር የምናደርግበት በርቱ መልዕከት ነው፡፡ስለሆነም የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት፣የልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት፣የአገራችን ወጣቶች ለዚህ ትግል ለምታደርጉት አስተዋጾኦ በእጅጉ ኮርተንባችኋል፡፡ትውልድ ለዘለዓለም ሲኮራባችሁ ይኖራል፡፡አባት አርበኞቻችንን የምናነሳቸው እንደእናንተ ሁሉ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት በቻሉት ሁሉ ታግለው መስዋዕትነት ከፍለው አገራቸውንና ህዝባቸውን ነጻ ስላወጡ ነው፡፡በዚህ ጦርነት ውስጥ የአማራ ክልል ህዝብን ጀግንነት ከቦታ ቦታ ማዬት ማረጋገጥ ችለናል፡፡አሁንም የአማራ፣የአፋር ክልል ህዝብ አይጠረጠርም፡፡
 አንዲት የአፋር እንስት ያለችውን መጥቀስ እፈልጋለሁ፣ወያኔ አትጠራጠር የአፋር አንዲት ሴት እንኳ በህይወት መኖር ከቻለች ኢትዮጵያን ማፍረስ አትችልም ነው ያለችው፡፡ይሄ ታሪካዊ ጀግንነት ነው፡፡ሁላችንም በህይወት እያለን ወያኔ ከግብረ አበሮቹ ጋር በጋራ ሆኖ ኢትዮጵያን በፍጹም አያፈርስም፣እናንተ እያላችሁ ኢትዮጵያ አትፈርስም፡፡እናንተ ጀግኖች እያላችሁ የአማራ ክልል ህዝብ አንገቱን አይደፋም፣እናንተ እያላችሁ የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት በፍጹም አይሸረሸርም፣በዚህ ፍጹም እምነት አለን፡፡ስለሆነም ይህ ጀግንነት ማስቀጠል አለብን፡፡ለጀግንነታችሁ እኔ ብቻዬን አመስግኜ የምወጣው የታሪክ ዕዳ ስላልሆነ ለትውልድ እተወዋለሁ፡፡
 ይሄ መድረክ የስጋት መድረክ ብቻ አይደለም፤በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ያሉ የአማራ ማህበረሰብ አባላት እየፈጸሙት ያለው ተጋድሎ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ሰልፍ በማድረግ፣ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ እየሰሩት ያለው ስራ የሚደነቅ ነው፡፡ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማህበረሰብ በመሰብሰብ ይሄንን ችግር ክልሉ እንዴት እንዲያልፈው እናድርግ የሚለው ስራ በሰፊው እየተስፋፋ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ይሄ ብቻ አይደለም ያጋጠመንን ችግር በውል ተረድተው በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ያሉ በርካታ አክቲቪስቶች ያሊ ሳይቀሩ አንድነት ሃይል ነው በሚል ስሜት በመነሳት ከህዝባችን ከመንግስታችን ጋር ሆነው ይሄንን ጠላት በሳይበሩም ሳይቀር እየተፋለሙት ይገኛሉ፡፡እነሱን አለማመስገን ንፉግነት ነው፡፡
 በመጨረሻ ሁላችንም አካባቢያችንን ለማዳን ህዝባችንን ለማዳን፣ኢትዮጵያን ለማዳን በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተች የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ለማረጋገጥ ሁላችንም ወታደሮች ነን፤ሁላችንም አርበኞች ነን፣ሁላችንም የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ልዩ ሃይል እንሁን፣ሁላችንም ለአገራችን መዳን ዘብ እንቁም፣ያለምንም ጥርጥር ይሄ ጊዜ ያልፋል፣በሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ እሾህ አንትከል አንድ እንሁን፣አንድ ከሆን ጠላት ይበተናል፣አቅም የለውም፡፡በገባንበት ሁሉ የጠላትን አቅም አይተነዋል ፈትሸነዋል፣ከእኛ የተሻለ አንዳችም አቅም የለውም፡፡ስለሆነም እንደ ህዝብ ቆፎው እንደተነካበት ንብ ሆነን ጠላት በጋራ እንፋለም፤እንግጠመው፡፡የወረረን ጠላት የከበበንን ጠላት ከአገረ መንግስቱ ጋር ሆነን በአገረ መንግስቱ እየተመራን ግብዓተ መሬቱን ማረጋገጥ አለብን፡፡
 አማራ ክልል የገባ ጠላት ከአማራ ክልል እንዳይወጣ ማድረግ አለብን፡፡በዚህ መማማል አለብን፤ቃል መገባባት አለብን፤አባቶቻችን አርበኞች ተማምለው ነው ጠላትን ማሸነፍ የቻሉት፤ቃል ኪዳን አስረው ነው ጠላትን ማሸነፍ የቻሉት፤ቃል ሳንገባ እርስ በእርስ ሳንተማመን በውስጣችን ያሉ ሰንኮፎችን በውል ለይተን እያራን ሳንሄድ ተጃምለን ጠላትን ልናሸንፈው አንችልም፡፡ስለዚህ የሁሉም አማራ ተልዕኮ፣የሁሉም ኢትዮጵያ ተልዕኮ እንደ ወታደር ኢትዮጵያን ማዳን ነው፤አማራ ክልልን ማዳን ነው፡፡ይሄንን ስናደርግ ታሪክ እንጽፋለን፣አንድ እንሁን ፤አንድነታችን የጠላትን ግብዓተ መሬት ያረጋግጣል፡፡
 
ትግላችን ለህልውናችን!!
ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ መቼም የትም በምንም!
አመሰግናለሁ!
 
ክቡር አቶ አብርሐም አለኸኝ
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽቤት ኃላፊ

ምላሽ ይስጡ