አሸባሪው ህወሓት ከ“አልቃይዳ እና አይኤስ” የበለጠ የሽብር ድርጊትን ፈጽሟል፡- አቶ ግዛቸው ሙሉነህ
በኢትዮጵያ የሽብር ድርጊትን በመፈጸም አሸባሪው ህወሓት ከአልቃይዳ እና አይኤስ የበለጠ አሰቃቂ እና አስነዋሪ ድርጊቶችን የፈጸመ መሆኑን የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ያልተፈጸመ በደል የለም የሚሉት ዳይሬክተሩ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ማንነታችን የሰረቀ፣ ታሪካችንን ያበላሸ፣ ብሔርን ከብሄር የሚያጋጭ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ሲያጋጭ የኖረ፣ በአጠቃላይ ሃይማኖታዊ ትውፊቶችን ሳይቀር እንዲሸረሸሩ ያደረገና ስነ ምግባራችን ጭምር እንዲዛባ ይሰራ የነበረ ቡድን ነው” ብለዋል፡፡
ይህ አሸባሪ ድርጅት በአረመኔያዊ ድርጊቱ በርካቶችን በጅምላ እየገደለ ሲቀብር የኖረ፣ በፖለቲካ አሻጥር የሚታወቅ፣ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ የሚያዛባ እና አገር እንዲበጠበጥ፣ እንዲፈርስና እንዲበተን ከውጭ ጠላቶች ጋር ጭምር እየሰራ ያለ ድርጅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሓት ቀድሞ በሰራው የአሻጥር ፖለቲካ ምክንያት እውነትን ሊሰሙ ፈቃደኛ አለመሆናቸው እየታየ መሆኑን ነው አቶ ግዛቸው የገለጹት፡፡
“እውነት ያለው እኛ ጋር ሆኖ ሳለ ውሸት እውነት ሆኖ እየተነገረ ያለበት ወቅት ነው” የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ባላስፈላጊ መንገድ የሱዳን ኮሪደር ይከፈት እያሉ ያሉትም የዚህ የፖለቲካ አሻጥር ውጤት ነው ብለዋል፡፡
መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ እያለ በአማራ ክልል በፈፀመው ትንኮሳ ከ200 ሺህ የሚልቁ የክልሉ ነዋሪዎችን ከቀያቸው አፈናቅሎ እርዳታ ጠባቂ ማድረጉን በመግለፅ ይህን አሸባሪ ቡድን እስኪጠፋ መታገል የሁሉንም ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡