የምርጫው ስኬታማ መሆን በኢትዮጵያ ላይ ትችት የሚያቀርቡ አከላት የተሳሳቱ መሆናቸውን ያረጋግጣል-ላውረንስ ፍሪማን

የምርጫው ስኬታማ መሆን በኢትዮጵያ ላይ ትችት የሚያቀርቡ አከላት የተሳሳቱ መሆናቸውን ያረጋግጣል-ላውረንስ ፍሪማን

  • Post comments:0 Comments
ኢትዮጵያ ያካሄደችው ስድስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ መሆን በኢትዮጵያ ላይ ትችት የሚያቀርቡ አከላት የተሳሳቱ መሆናቸውን ያረጋግጣል ሲሉ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኙ ላውረንስ ፍሪማን ገለጹ።
ከ30 ዓመታት በላይ በአፍሪካ የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲዎች ላይ ተሳትፎ ያላቸው ላውረንስ ፈሪማን÷ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት ባዘጋጁት ትንታኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በነቂስ ወጥቶ የሚመራውን መምረጡ በተላያየ ጫናዎች ውስጥ የምትገኘውን ሀገር ወደ ዴሞክራሲ ለማሻገር መሠረት የጣለ ነው ብለዋል።
የምርጫው ስኬታማ መሆን በምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃንና መንግስታት ሲሰጡ የነበሩ የአመጽና የብጥብጥ መላምቶችን ያፈረሰ መሆኑን ጠቁመው÷ የትኛውም የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ የምርጫውን ስኬት አላደናቀፈውም በማለት ገልጸዋል።
ምንም እንኳ ስኬታማነቱን የምዕራባውያን የመገናኛ ብዙኃን ለመዘገብ ፊታቸውን ቢያዞሩም ኢትዮጵያውያን ግን ወደ አንድነት፣ ሰላምና ልማት የሚመራቸውን ለመምረጥ ለረጅም ሰዓታት ታግሰው ምርጫቸውን አካሂደዋል ሲሉ አመልክተዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዘቢዎችና የምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ቡድንም ከአንዳንድ የጸጥታና የአቅርቦት ችግር በቀር ምርጫው በታመነ ሁኔታ፣ በሰላማዊ መንገድና ያለምንም ችግር ተካሂዷል ማለታቸው የዚህ ማሳያ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
ሆኖም የተዛባ እይታ ያለቻው የምዕራባውያን መንግስታት ግን ምርጫው ላይ ታዛቢ ለመላክ ካለመፈለግም በላይ የምርጫውን በስኬት መጠናቀቅ ተከትሎ የእንኳን ደስ አላችሁና የአድናቆት መልእክት አለማስተላለፋቸው “ኢትዮጵያ ያካሄደችው ስድስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ መሆን በኢትዮጵያ ላይ ትችት የሚያቀርቡ አካላት የተሳሳቱ መሆናቸውን ያረጋግጣል” ሲሉ ላውረንስ ፍሪማን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና አመራሮቹ ገለልተኛ መሆን ምርጫውን ለመታዘብ የመጡትን እንዲሁም ባለድርሻ አካለትን በመርጫው ላይ እምነት እንዲኖራቸው ማስቻሉንም ጠቁመዋል።
በብዙ ፈተናዎች መካከል የተካሄደ ምርጫ መሆኑን በማስታወስ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ምርጫዎች ሁሉ የተፎካካሪዎች ስብጥርና ሰፊ የመራጮች ቁጥር የታየበት መርጫ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply