የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 99ኛ መደበኛ ስብሰባ በሁለት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

  • Post comments:0 Comments
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 99ኛ መደበኛ ስብሰባ በሁለት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር በተደረጉ በአራት የብድር ስምምነቶች ላይ ተወያይቷል፡፡ የመጀመሪያው የብድር ስምምነት የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ለህብረተሰቡ ያለውን ተደራሽነት የማሻሻል እና ለገጠሩ ህብረተሰብ በቤተሰብ ደረጃ፣
ለማህበራዊ ተቋማት እንዲሁም ለኢንተርፕራይዞች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለማሳደግ የሚውል ነው፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውለው ብድር 500 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡ ሁለተኛው የብድር ስምምነት ዓላማ የመሠረታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥ ማሻሻልና የተጠያቂነት ሥርዓትን ማጠናከር ሲሆን፣ በወረዳ ደረጃ የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርና፣ የውሃ እና የገጠር መንገድ አቅርቦት መሠረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግና የአገራችንን ያልተማከለ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ለማጠናከር የሚያግዝ ነው፡፡ የብድር መጠኑም 250 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡ ሶስተኛው የብድር ስምምነት በኢትዮጵያ ልማት ባንክ አማካኝነት የሚተገበር አነስተኛ እና መካከለኛ እንተርፕራይዞችን በፋይናንስ ለማጠናከር ለመደገፍ የሚውል ሲሆን የብድር መጠኑም 180 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡ አራተኛው የብድር ስምምነት የመረጃ ልውውጥ ቴክኖሎጂ በማዘመን ኢኮኖሚውን እና አጠቃላይ የመንግሥት አሰራርን ከተለመደው ባህላዊ የአሰራር ዘዴ ወደ ዲጂታል የመቀየር ስራዎችን ለማስፈጸም የሚውል ሲሆን የብድር መጠኑን 200 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡ በድምሩ የ1 ቢሊየን 130 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የብድር ስምምነቶች በማጽደቂ ረቂቅ አዋጆች ተደግፈው ቀርበዋል፡፡ ሁሉም ብድሮች ምንም አይነት ወለድ የማይታሰብባቸው፤ ባንኩ ብድሮቹን በማስተዳደር ረገድ ለሚሰጠው አገልግሎት 0.75% የአገልግሎት ክፍያ የሚታሰብባቸው ሆነው የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ተከፍለው የሚጠናቀቁ ናቸው፡፡ ምክር ቤቱም ከአገራችን የብድር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ እና ምንም አይነት ተጓዳኝ ጫና የሌላቸው መሆኑን በማረጋገጥ በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ረቂቅ አዋጆቹ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡
2. ምክር ቤቱ በመቀጠል የተወያየው የአፍሪካ የመንገድ ደህንነት ቻርተር እና የተባበሩት መንግስታት የመንገድ ትራፊክ ኮንቬንሽን ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ነው፡፡ የነዚህ ሁለት አለም ዓቀፍ ስምምነቶች መጽደቅ አገራችን በመንገድ ትራንስፖርት ረገድ ከጎረቤት አገራት ጋር የሚኖራትን ግንኙነት የሚያሳልጥ ከመሆኑም በላይ ብሄራዊ፣ አካባቢያዊና አህጉራዊ የመንገድ ደህንነት ፕሮግራሞችን በቅንጅት ለመፈጸም የሚያስችል እንዲሁም በሀገር ደረጃ ሰፊና ሁሉን አቀፍ የሆኑ የመንገድ ደህንነት ፖሊሲዎች እንዲቀረጹ የሚያስችል መሆኑ ታምኖበት ለምክር ቤቱ ይሁንታ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በጥልቀት ከተወያያ በኋላ በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡

ምላሽ ይስጡ