ለዴሞክራሲ የተከፈለ መስዋዕትነት /በሚራክል እውነቱ/

ለዴሞክራሲ የተከፈለ መስዋዕትነት /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments

ታሪካዊው እና ኢትዮጵያ ላይ እየተገነባ ያለውን የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲያብብ መሰረት ሆኖ ያለፈው የሰኔ 14/2013 ብሔራዊ ምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ጨምሮ በብዙ ኢትዮጵያዊያን ውስጥ ሲታወስ የሚኖር ነው፡፡

 
አንዳንዶች ለኢትዮጵያችን ክፉ ተመኝተዋል፤ምርጫው እንደታሰበው ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ሊጠናቀቅ አይችልም፤ከምርጫው በፊት፣በምርጫው ዕለትና ከምርጫ ማግስት ኢትዮጵያዊያን ወደማያባራ ግጭትና ትርምስ ውስጥ ይገባሉ በማለት በኩራት ሲናገሩ በገሃድ ተደምጠዋል፡፡ዳሩ አስተዋዩና ሩቅ አሳቢው የኢትዮጵያ ህዝብ የአገር ሰላም የኔ ሰላም ነው በማለት ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ዘብ ሆኗል፡፡
 
በርካታ ሁነቶችን አስተናግዶ ያለፈው ይህ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ያለ ከልካይ በአግባቡ መጠቀም እንዲችሉ ዕድል የሰጠ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
 
ሊገላገሉ በደቂቃዎች የሚቆጠር ጊዜ የቀራቸው ነፍሰ ጡር እናቶች በምጥ ተይዘው በምርጫ ጣቢያ ላይ እንዳሉ በሰላም ሲገላገሉ፣በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል አንድ ግለሰብ አባታቸውን ከቀበሩ በኋላ ወደ ምርጫ ጣቢያ በመምጣት ድምጽ ሰጥተዋል።
 
የትራፊክ አደጋ ደርሶባቸው ሆስፒታል ውስጥ በኦክስጅን ህክምና ሲከታተሉ የነበሩ ታካሚዎች በምርጫው በመሳተፍ መብቶቻቸውን ስለመጠቀማቸው እንዲሁም በምርጫው ዕለት የነበራቸውን የውጭ አገር በረራ ለሚቀጥለው ቀን በማስተላለፍ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ በካርዳቸው ድምጻቸውን መስጠታቸውንና መምረጥ መቻላቸውን ሰምተናል፡፡ ይህ ሁሉ ለዴሞክራሲ የተከፈለ መስዋዕትነት ነው፡፡
 
በምርጫው ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት፣ህዝቦቿ ለሰላም ያላቸውን የማይናወጥ አቋም በግልጽ ያሳዩበት፣አገራዊ አንድነታችንን አስጠብቀን ዕቅዶቻችንን ያሳካንበት ዕለት ነበር፡፡ምንም እንኳ በርካቶች በምርጫው ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ቢኖራቸውም ኢትዮጵያዊያን ያለምንም ኮሽታ ምርጫውን በሰላም በማጠናቀቅ ሰላም ወዳድ ህዝቦች መሆናቸውን በተግባር አረጋግጠዋል፡፡
 
በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሂደት የታዩ መልካም ክስተቶች ኢትዮጵያውያን ነገን የተሻለ ማድረግ ላይ ያተኮረ ዕይታ እንዳላቸው ያመላከተ ነበር፡፡በምርጫው ሂደት የታየው የሕዝብ ተነሳሽነት፣የምርጫ ቦርድ ጥንካሬና የፖለቲካ ፓርቲዎች ስክነት ኢትዮጵያውያን በብዙ ችግሮች ውስጥም ሆነው ነገን የተሻለ ማድረግ ላይ እንደሚያተኩሩ አሳይቷል።
 
ምርጫው ዲሞክራሲ እና ፍትሕ የነገሰባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ቀድመው የተገነዘቡት ኢትዮጵያዊያን ያለ ማንም ጎታች ሀይል ጸሀዩን፣ብርዱን፣ውርጩንና ዝናቡን ለሰዓታት ተቋቁመው በካርዳቸው ድምጻቸውን መስጠት ችለዋል፡፡

Leave a Reply