You are currently viewing የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር አካሄዱ

የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር አካሄዱ

  • Post comments:0 Comments
የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር አካሄዱ
********************
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰንን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ ከሰዓት በኋላ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር አካሂደዋል፡፡
ርዕሰ-መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ዴምክራሲያዊ ምርጫ ከማካሄድ ጎን ለጎን ሁሉም ዜጎች ለሀገራቸው አረንጓዴ አሻራቸውን ማሳረፍ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመው፣ አመራሩ ያደረገው የችግኝ ተከላም ይህንኑ ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በ6ኛው ሀገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ በክልሉ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት አቶ አሻድሊ፣ ምርጫው ያለምንም የጸጥታ ችግር እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ምርጫው ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት እያረገ መሆኑን ገልጸው፣ በአሶሳ ከተማ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የተፈጠረውን የድምጽ መስጫ ወረቀት እጥረት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
በተያዘው ዓመት እንደክልል 72 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ መያዙን የገለጹት ርዕሰ-መስተዳድሩ፣ በቀጣይም በሁሉም አካባቢዎች የክልሉን ሕዝብ ያሳተፈ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ይካሄዳል ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡም በዛሬው ምርጫ ድምጹን ከመስጠት ጎን ለጎን በችግኝ ተካላው ላይ እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ምላሽ ይስጡ