መጪውን ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ማድረግ ሁላችንንም እንደሀገር አሸናፊ ያደርጋል!

መጪውን ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ማድረግ ሁላችንንም እንደሀገር አሸናፊ ያደርጋል!

  • Post comments:0 Comments

መጪውን ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ማድረግ ሁላችንንም እንደሀገር አሸናፊ ያደርጋል!

በጊዜ መለኪያ በሦስት ዓመታት ቆይታ ውስጥ በርካታ ለውጦችን ማስተዋል የሚቻልባቸው በርካታ ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ቢታመንም ለተወሰኑ ጉዳዮች ግን ሦስት ዓመት በቂ ካለመሆኑም በተጨማሪ በጣም አጭር ጊዜ ሊሆን ይችላል፡፡ በተመሳሳይ በሀገር ደረጃ የአንድን ፓርቲ ስኬታማነት መመዘኛ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ተግባራትን በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወጥኖ ስኬታማ ማድረግ ከባድ ያደርገዋል፡፡

በተለይ በእኛ ሀገር ሁኔታ አጋጥሞ ከነበረው ውስብስብ ፖለቲካዊ ቀውስ አንፃር በባለፉት ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በሀገራችን ላይ አንዣቦ ከነበረው አደጋ ተወጥቶ ወደ ትክክለኛው ጎዳና በመግባት ለኢትዮጵያ ብልፅግና እውን መሆን ተስፋ መሰነቅያ ያስቻሉ በርካታ ስኬቶች መታየታቸው የብልፅግ ፓርቲን ስኬታማ አጀማመር ገና ከማለዳው ያስገነዘበ ነው፡፡

በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በአንድ በኩል በአመታት ሊመዘኑ የሚችሉ በርካታ የለውጥ ተግባራት በስኬት እንዲመዘገቡ ተደርገዋል፡፡ ይህም መላውን ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ስለሚያደርግ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የበርካቶችን ድጋፍ እያገኘ በመቀጠል ላይ የሚገኝ ሀገራዊ እውነታ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከለውጡ በተቃራኒ እየተስተዋሉ ያሉ አሉታዊና ሀገር ጎታች ፀረ-ለውጥ እንቅስቃሴዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው የሚገኝበትን ሁኔታ እናገኛለን፡፡ ስለዚህም አሁን ላይ እንደሀገር በስፋት የተጀማመሩ አዎንታዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማድረግና በአሉታዊ መልኩ የተጋረጡብንን ፈተናዎች በማክሰም የሀገራችንን ብልፅግና እውን ለማድረግ ያለንን እድል ማስፋት ከሁላችንም ዘንድ የሚጠበቅብን ይሆናል፡፡

ሀገራዊ ብልፅግናን እውን በማድረግ አጠቃላይ ሂደት ውስጥ በርካታና እልህ አስጨራሽ እንዲሁም ውስብስብ ፈተናዎች ሊታለፉ እንደሚገባ ከበርካታ ሀገራት ተሞክሮ መረዳት ይቻላል፡፡ ከእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታም ስንነሳ የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማምጣት ምንም እንኳ የራሳችን የሆኑ ልዩ የእድገት ፖሊሲያዊ ባህሪያት ሊኖሩን የሚችሉ ቢሆንም እነዚህን ውስብስብና ፈታኝ ሂደቶች በብቃት ማለፍ ይጠበቅብናል፡፡ ወደ ብልፅግና ከምናደርገው ሀገራዊ ጉዞ በተቃራኒው ከተለያየ መነሻ ሊቃጣ የሚችል አፍራሽ እንቅስቃሴ ሊኖር እንደሚችልም በቅጡ መረዳት ይኖርብናል፡፡ በተለይ እነዚህን አፍራሽ እንቅስቃሴዎች አሳንሶ በማየት ከሚፈጠሩ ከፍተኛ ጉዳቶች መከሰት እንደሀገር መጠንቀቅ ይገባል፡፡

የትኛውንም ጥፋት እንደሀገር አሳንሰን በተመለከትነው ልክ የመበራከትና በአውዳሚነቱም የማደግ እድል እንዲያገኝ እየፈቀድን መሆናችንን ተረድተን ተገቢውን ጥንቃቄ መውሰድ ይኖርብናል፡፡ ኢትዮጵያንና ዜጎቿን ከሁለንተናዊ የእድገት ጉዞ ከሚያደናቅፍ አስተሳሰብና ተግባር እንደሀገር ሁላችንም በኃላፊነትና በጥንቃቄ መከላከል ይገባናል፡፡ በተቃራኒው አሳንሰንና ንቀን ከተውናቸው ከሀገራችን ብልፅግና በተጻራሪ የቆሙ በሀገር ውስጥና በውጪ ያሉ ኃይሎች አጀንዳውን በመግዛት ለሚፈልጉት የጥፋት ተልዕኮ ማስፈፀሚያ መሳሪያ በማድረግ እንዲጠቀሙበት መፍቀድ ይሆንብናል፡፡ በተጨባጭም በሀገራችን ያለው እውነታ ከዚሁ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

እንደሀገር ሁላችንም በመዘናጋት በሚፈጠር ጥቃቅን ስህተቶች መበራከትና ማደግ ምክንያት ሊደርስብን ከሚችል ከፍተኛ ሀገራዊ ኪሳራ በተገቢው መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ በሀገር ደረጃም ይሁን እንደማህበረሰብና ግለሰብ በተራዘመ ጊዜና ከፍተኛ ጥረት እውን ያደረግነውን አዎንታዊ የእድገት ለውጥ በምንፈጥራቸው ያልተገቡ ስህተቶች ምክንያት ከቀናትና ሳህታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንዲፈርስ ማድረጉን ሀገራዊ ተሞክሯችን በሚገባ እያሳየን መጥቷል፡፡ በዚህም ውድ የሆነውን የበርካቶችን ህይወት ከማጣት አንስቶ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት ንብረት እንዲወድም አድርጓል፡፡ አሁን ላይም ቢሆን ሀገራችን መሰል አደጋዎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱባት ሲሆን በቀጣይም ሀገራዊ ምርጫውን እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀም በርካታ አካላት ተመሳሳይ የጥፋት ድግሶችን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ በስጋት መወሰድ ይኖርበታል፡፡

እንደሀገር ለማደግ ካለ የሁሉም ዜጎች የረጅም ጊዜ ከፍተኛ መሻትና በከፍተኛ የአቅም ውስንነቶች በመታጠረ ተግባራዊ ማድረግ የጀመርናቸው በርካታ መልካም የሚባሉ ሀገራዊ የእድገት ፕሮጀክቶችና ጥረቶች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል እነዚህ በፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እድገት ለማምጣት እንደሀገር የተጀመሩ ተግባራት በመጠንና ጥራት ደረጃ በሚፈለገው ልክ ያልደረሱና በቀጣይም መቀረፍ የሚገባቸው በርካታ ውስንነቶችና ችግሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሀገራዊ የእድገት ጅምር ጥረቶች ሊደርስባቸው ከሚችል ማንኛው አይነት ጥፋት ልንጠብቃቸውና በቀጣይም ተሻሽለው ወደፊት እንዲቀጥሉ በማድረግ የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ማድረግ ሀገራዊ ግዴታችን ይሆናል፡፡ ከእዚህ ውጪ የሚኖረው አማራጭ ግን ወደ እድገት ሳይሆን ሀገርን ወደ ቁልቁል የሚነዳ ይሆናል፡፡ መገንባት ሳይሆን ማፍረስ፣ ከፍታ ሳይሆን ገደል በመሆኑ እንደሀገር ከምንገኝበት ችግር ለመላቀቅ ከምናደርገው ጥረት ባነሰ የእስካሁን አዎንታዊ የእድገት ለውጦችን በመናድ ሁላችንንም ለባሰ ኋላቀርነትና ድህነት መዳረግ ይሆንብናል፡፡

በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊያን  መጪውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በማድረግ የሚያገኙት  ጠቀሜታ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን በሚገባ መረዳት ይኖርብናል፡፡ በአንድ በኩል እንደሀገር ለመገንባት የምናልመውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስተማማኝ መሰረት እንዲኖረው ከማድረግ አንፃር ምርጫ ከሚኖረው ጠቀሜታ የሚገኝ መሆኑ ነው፡፡ እንደ ሀገር ስኬታማ ምርጫን ማካሄድ አንዱ የዴሞክራሲ መለማመጃ መሳሪያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በውጤቱ ማሸነፍን ብቻ ሳይሆን መሸነፍንም፣ ያሸነፈ ፓርቲም ስልጣን በኮንትራት የሚሰጥ እንዲሁም ሀገርና ህዝብን ማገልገያ እንጂ መገልገያ እንዳልሆነ፣ በአንድ ምርጫ በድምፁ መርጦ የሾመ ህዝብ በሌላ ምርጫ በሌላ አካል ሊተካ የሚችል ብቸኛ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መሆኑን የምናረጋግጥበት መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ ምርጫውን ስኬታማ ማድረግ ማለት እነዚህን የዴሞክራሲ ግቦች ማሳካት ጭምር በመሆኑ ለምርጫው ስኬታማነት እንደዜጋ የሁላችንም ሀገራዊ ኃላፊነት የሚጠበቅ ያደርገዋል፡፡

በሌላ በኩል የምርጫው ስኬታማነት መለኪያ ተደርጎ የሚወሰደው ከምርጫው ጅማሬ አንስቶ እስከፍፃሜው የሀገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ በኩል የምናሳካው ወሳኝና ቁልፍ ፋይዳው ነው፡፡ በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ላይ በሚገኙ ሀገራት አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል በተሳሳተና ባልተገባ ፖለቲካዊ ቅስቀሳ ሀገርን በሚጎዳ አቅጣጫ ለማነሳሳት ሰፊ እድል ያለ መሆኑና ይህንኑ ማስቆም የሚያስችል ጠንክራ ተቋም ሊገነባ የማይችል በመሆኑ የምርጫ ወቅትን ተከትሎ የሚፈጠር ሀገራዊ ቀውስ በስፋት ይስተዋላል፡፡ በእኛ ሀገር ሁኔታም መሰል ቀውስ የተለመደ ነው፡፡ የዘንድሮውን ሀገራዊ ምርጫም እንደሀገር እያንዳንዱ  ዜጋ የበኩሉን ግዴታ ከመወጣት አንስቶ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ኃላፊነታቸውን በመወጣት ሀገራዊ ሰላማችንን የማስጠበቅ ስራ ከፍተኛ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም የምርጫውን ሰላማዊ ሂደት እስከፍፃሜው የማድረስ ጉዳይ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው እያንዳንዱ ሀገር ወዳድ ዜጋ በሚገባ መገንዘብ ይኖርበታል፡፡

በተመሳሳይ ከጅምሩ አንስቶ ከሞላ ጎደል ጠንካራ መሰረት እየያዘ የመጣው የእስካሁኑ የምርጫው ዴሞክራሲያዊ ሂደት  በቀጣይም እስከምርጫው ፍፃሜ ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፡፡ በተለይም በእያንዳንዱ የምርጫው ሂደት የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ በመላው ሀገራችን ተጠብቆና ውጤቱም ተወዳዳሪ ፓርቲዎችን አሸናፊ ከማድረግ በላይ በመላው ዜጎች ዘንድ እንደሀገር ተጠባቂ የሚሆነውን የዴሞክራሲ ስርዓት በጠንካራ መሰረት እንዲጣል የሚያስችል መሆን ይጠበቅበታል፡፡

በአጠቃላይ ተግባራዊ መደረግ በጀመረው ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ለውጥም ይሁን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ እንደሀገር ለዜጎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ብልፅግና እውን መሆን ወሳኝነት የሚኖራቸው ግቦች እንይሳኩ የሚያደርጉ ተጨባጭ ውስጣዊና ውጫዊ ነባራዊ የኃይል አሰላለፎችና እውነታዎች እንደሀገር አንዣበው የሚገኙ መሆናቸውን ሁላችንም በሚገባ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ለአብነት በሀገራዊ ለውጡ ጥቅማቸው የተነካ የተለያዩ ቡድኖችና አካላት ሀገራዊ ለውጡን ለመቀልበስም ይሁን ምርጫው እንዳይሳካ ለማድረግ እያደረጉ ያለው እውነታ ለዚህ እንደማሳያ ከውስጣዊ ሁኔታችን አንፃር የሚጠቀስ ነው፡፡

በተመሳሳይ ከውስጥ በሀገራዊ ለውጡ ምክንያት ጥቅሙ የተነካበት አካል ጥቅሙን ለማስመለስም ይሁን ሀገር ለማውደም እያደረገ ያለውን የጥፋት እንቅስቃሴ ሀገራችን በምትገኝበት ቀጠና ተመሳሳይ ፍላጎት ካላቸው አካላት ጋር አቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚችሉ በርካታ አብነቶችን በማንሳት መረዳት ይገባል፡፡ በተለይ የአፍሪካ ቀንድና ዙሪያ መለስ ቀጠናው በከፍተኛ የፖለቲካና የፀጥታ አለመረጋጋት የሚገኝ መሆኑ ለእነዚህ አካላት ውጥን መሳካት የሚኖረውን ምቹ ሁኔታ በሚገባ ማጤን ተገቢ ያደርገዋል፡፡ ቀጠናው ባለው ጂኦ ፓለቲካዊ ጠቀሜታ እንዲሁ በርካቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ተፅዕኖ የሚያሳድሩበት አካባቢ ነው፡፡

በተለይም አሁን ላይ ግብጽና ሱዳን የአባይ ግድብ ፕሮጄክታችን ከግብ እንዳይደርስ መጠነ ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ እያደረጉ የሚገኙ ከመሆናቸው ጋር አስተሳስሮ ቀጠናዊ ሁኔታውን በሚገባ የመረዳትና የመመከት ተግባር የሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጎች መሆን ይኖርበታል፡፡ ሀገራቱ ምርጫን አስታኮ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ወኪሎቸቻቸው ጋር በመጣመር ግርግር እንዲነሳ ለማድረግ የሚያስችል ስራ ከመስራት እንደማይቆጠቡ ከነበራቸው ባህርይ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህም በሀገር ውስጥ ጠንካራ መንግስት እንዳይኖር በማድረግ ሀገራችን በአባይ ውሃ የመልማት ተፈጥሯዊ መብቷን እንዳትጠቀም ሙከራ ያደርጋሉ፡፡ የተለያዩ ፅንፍ የወጡ ኃይላትን በመደገፍ የጭቅጭና የብጥብጥ እንዲሁም  የተዳከመች ሀገር ተፈጥራ የተሰነቁ የልማት ግቦች እንዳይሳኩ ያደርጋሉ፡፡

ውስጣዊና ውጫዊ ሀገራዊ አደጋዎችን በሚገባ ተገንዝቦ መከላከል ለአንድ ወገን ወይም ለመንግስት ብቻ የሚተው ተግባር ሳይሆን የሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጎች ድርሻ ጭምር በመሆኑ እያንዳንዳችን ለሀገራችን የሰላም ዘብ በመሆን የተጀመረውን ሀገራዊ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የድርሻችንን እንወጣ፡፡ ብልፅግና ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያ!!

 

 

 

Leave a Reply