ኢትዮጵያ ታሸንፍ!

ኢትዮጵያ ታሸንፍ!

  • Post comments:0 Comments

በቅርቡ የሚካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ “ኢትዮጵያውያን የሚመርጡበት፤ ኢትዮጵያ የምታሸንፈበት” ታላቅ ምርጫ ነው። ወዳጆቻችን ስኬታችንን የሚናፍቁበት፣ የአገራችን ብርሃን የሚፈነጥቅበት፣ የትንሳዔዋ ማሳመሪያ ቀንም ነው።

በሌላ በኩል በየዕለቱ በሚፈጥሩብን ችግር ከአገራዊ ብልጽግና ጉዣችን ተሰናክለን የምንቀር የሚመስላቸው፣ እኛን ቡራኬ ካልሰጠነው ምርጫ ማካሄድ እንደማንችል ለመንገር የሚሞክሩ ሃይላት መጨረሻዋን በሚጠባበቁበት ቅጽበት ኢትዮጵያውያን የሚያካሄዱት ምርጫ ነውና በጉጉት ይጠበቃል።

ብልጽግና ወደ ምርጫ ሲገባ ይህ ታላቅ ቀን እውን እንደሚሆን በኢትዮጵያውያን ተማምኖ፤ ምርጫውን በድል የመወጣት ፍላጎቱ ምንጭም ዕለቱ የኢትዮጵያ ትንሳዔ መጀመሪያ መሆኑን በማመን ነው።
በርግጥ ብልጽግና መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን አስተማማኝ ድምጽ ማግኘት ግቡ አድርጎ ተንቀሳቅሷል። በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ከህዝብ ጋር በመሆን ውጤታማ ስራ በመስራት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻገር እንደሚችል በማስረጃ አስደግፎ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የተከራከረውም ምርጫውን በአሸናፊነት መወጣትን ዒላማ አድርጎ ነው።

አገራዊ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የፍትሃዊ ማህበራዊ አገልግሎትን በፍጥነትና በጥራት ማቅረብን በተመለከተ የተያዙ የፖሊሲ አቅጣጫዎችና ስትራቴጂዎች አገሪቷን ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ ጠንካራ መሰረት እንደሚያስጥል ምንም ጥርጥር የለንም። ፓርቲያችንም የሚያደርገውን ይናገራል፤ ይፈጽማልና።

ፓርቲያችን ወደ ምርጫ ሜዳ ሲገባ ግልጽ ዓላማና ግብ በመያዝ አገርን ለማሻገር እንደሚችል በራሱ በመተማመን ነው። በርግጥ የመጨረሻው ውጤት የሚታየው ህዝቡ “ይበጀኛል፣ ይሆነኛል፣ አገሬን ካለችበት የዘመን አጣብቂኝ አውጥቶ ወደ ብልጽግና ይመራኛል” በማለት በምርጫው ዕለት በነጻነት በሚሰጠው የተከበረ ድምጽ መሆኑን ብልጽግና በጽኑ ያምናል።

ለዚህም ነው ብልጽግና ምርጫውን በድል ለመወጣት ሚዛን የሚደፉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ነድፎ የተንቀሳቀሰው እና ህዝብ ፖሊሲዎቹን፣ ስትራቴጂዎቹንና እቅዶቹን ተመልክቶ ድምጹን እንዲሰጠው የጠየቀው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጹን ለመስጠት የሚያስችለው የመረጃና የማስረጃ ትጥቁን ይዟል፤ ዛሬ ኢትዮጵያን ካጋጠማት ፈተና ለማውጣት ከህዘብ ጋር በመሆን ለመስራት ቁርጠኛ የሆነውን ለይቷል ብሎም ያምናል።

ብልጽግና ባለፉት ሶስት ዓመታት ያከናወናቸውን ተግባራት፣ ከፊቱ ተጋርጠው የነበሩትን መሰናክሎች ያለፈባቸውን ስልቶች፣ በአካባቢው ሰላምን ለመፍጠር የተጠቀመባቸው መንገዶችን በዋቢነት በመጥቀስ ጥልቅ የሆነውን ቁርጠኝነት ማሳየቱ ለምርጫው ትልቅ ጉዳይ ነው። ፓርቲያችን በምርጫው ዕለት የህዝቡን ድምጽ እንደሚያገኝ ይተማመናል። ከሁሉም በላይ ግን ብልጽግና ፓርቲን የኢትዮጵያ አሸናፊነት ይገዛዋል።

ብልጽግና ምርጫውን ከማሸነፍና መንግስት ከመመስረትም በላይ ያስባል። ከህዝብ ተቀባይነት በሚያገኘው ድምጽ አገር የመምራት ሃላፊነትን ከመረከብ በላይ አገር ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂዳ አሸናፊ ሆና ማየትን ይናፍቃል። መንግስት መስርቶ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ ሰላሟ የተረጋገጠ፣ ደህንነቷ አስተማማኝ የሆነ አገር መገንባት ከሚፈልገው በላይ ኢትዮጵያ ጠላቶቿ የሚያፍሩበትን፣ ክፉ የሚመኙ ኃይላት ቅስማቸው የሚሰበርበትን የተመሰከረለት ምርጫ አካሂዶ አሸናፊ መሆናን ይናፍቃል።

ብልጽግና አገራችን በመደመር ፍልስፍና የተቀመመ ዴሞክራሲ ለመገንባት እንዲቻል የኢትዮጵያ ህዝብ “ዕድሉን ይሰጠኛል” ብሎ ከመቀበል ባለፈ ዜጎች ተረጋግተው በነጻነት ለአገራቸው ድምጻቸውን መስጠታቸውን ይናፍቃል። የምርጫው ውጤት ድል እንዲያጎናጽፈው ከመመኘት በላይ ታላቅ የሆነ ድል ይጠብቃል፤ ለዚህም ይሰራል።
ብልጽግና ከፓርቲው ድል የበለጠ የኢትዮጵያ ድል፤ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ይናፍቃል። ብልጽግና በምርጫው ለማሸነፍ የመፈለጉን ያህል ኢትዮጵያ በድል ክብሯን ከፍ እንድታደርግ ይተጋል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ አሸናፊነት ከብልጽግና የምርጫ ድል በላይ ነውና። ለዚህም ነው ፓርቲያችን ምርጫው በተሳካ መልኩ ተካሂዶ ማንም ቢያሸንፍ ድሉ የኢትዮጵያ ነው የሚለው።

ብልጽግና ምርጫውን በማሸነፍ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል አስተማማኝ የሕዝብ ተወካዮች መቀመጫ ማግኘት የሚፈልገውን ያህል፤ በገለልተኝነት ምርጫውን የሚያስፈጽሙና የሚታዘቡ አካላት ነጻነቱንና ፍትሃዊነቱን በተጨባጭ ማስረጃ ለእውነት እንዲመሰክሩለት ይሻል። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫው ኢትዮጵያ ድል ያደረገችበት መሆኑን ሲመሰክሩ፤ ሕዝቡ የፍላጎቱን፣ የምኞቱን፣ ይጠቅመኛል ያለውን በነጻነት መምረጡን በአደባባይ ሲናገር ከድሎች በላይ የሆነ ድል ነው። ለብልጽግና ድሉ የኢትዮጵያን አሸናፊነት የሚያበስር ምስክር ይሆንለታል። ስለዚህ ኢትዮጵያዊያን ይምረጡ ኢትዮጵያም ታሸንፍ ይላል ለብልጽግና። ኢትዮጵያውያን ይመርጣሉ፤ ኢትዮጵያም ታሸንፋለች።

እኛ ብልጽግናዎች ነን!

Leave a Reply