በእውነተኛ ፌዴራሊዝም ልዩነትን አቻችሎ ጠንካራ አገር የመገንባት የብልጽግና ጉዞ!

በእውነተኛ ፌዴራሊዝም ልዩነትን አቻችሎ ጠንካራ አገር የመገንባት የብልጽግና ጉዞ!

  • Post comments:0 Comments

የእውነተኛ ፌዴራሊዝም ሥርዓት መሰረታዊ ጉዳዩ በአንድ አገር የሚኖሩ ብሄሮችና ብሔረሰቦች ልዩነታቸውን አቻችለው በሁሉም መስክ የበለጸገች አገርን በመገንባት ሂደት ውስጥ የሚገለጽ ነው። የራስ እና የጋራ አስተዳደርን እውን ማድረግ ደግሞ ሌላው ነጥብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ከለውጥ በፊት ሲተገበር የነበረው የፌዴራል ስርዓት የሁላችንም የምትሆን አገር ከመገንባት አኳያ ያልተመቸ፤ ይልቁንም ከአንድነት ይልቅ ልዩነት የጎላበትና የተሰበከበት ነበር፡፡

ከዚህም ባሻገር የፌዴራሊዝም ስርዓት መገለጫ የሆነውን የራስ እና የጋራ አስተዳደር ያላከበረ፤ ራስ አስተዳደር በሞግዚት፣ የጋራ አስተዳደሩም በይስሙላ ሲከናወን የቆየ ነበር፡፡ በተለይ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ አጋርና እህት በሚል ዜጎች በራሳቸውም ሆነ በአገራቸው ጉዳይ ተሳትፎም፣ ወሳኝነትም እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡

ለዚህ አብይ ማሳያው ደግሞ፣ የፌዴራል ስርዓቱ ካሉት ዘጠኝ ክልሎች ውስጥ “አምስቱ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ አይመጥኑም” በማለት በአጋርነት ተሰይመው የተሰጣቸውን እና የተባሉትን ከመፈጸም የዘለለ በምንም አገራዊ ጉዳይ ላይ የመሳተፍም ሆነ ውሳኔ የማሳለፍ እድል ተነፍጓቸው መኖራቸው ነው፡፡ በእህትነት አብረው የሚሳተፉትም ቢሆኑ ለይስሙላ ይሳተፉ እንጂ ጥቂት ፈላጭ ቆራጭ ቡድኖች ከሚያራምዱት አቋምና ከሚያሳልፉት ውሳኔ የማፈንገጥ አንዳች መብት አልነበራቸውም፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዝሃ ቋንቋ፣ ባህል፣ ማንነትና እምነት ባለባቸው አገራት ደግሞ የፌዴራል ሥርዓት ምርጫ የሌለው አማራጭ መሆኑን ብልጽግና ፓርቲ ያምናል፡፡ እናም በኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓቱ መቀጠል ካለበት እንዴት ይቀጥል? ምን ጥንካሬዎች ነበሩት? ጉድለቱስ ምን ነበር? ምን የተሻለ ነገርስ ይታከልበት የሚለውን አንጥሮ በመለየት በመደመር እሳቤው ቅኝት ልዩነቶችን አቻችሎ፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን እውን አድርጎ ሁሉንም የመሰለች እና ለሁሉም የምትመች ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚያስችለውን እውነተኛ የፌዴራል ስርዓት እውን ለማድረግ ላለፉት ሶስት ዓመታት መንገዱን ጀምሯል፡፡

እንደ ብልጽግና እምነት፣ በፌዴራል ስርዓት ዜጎች በማንነታቸው ኮርተውና ስለ አገራቸው በልበ ሙሉነት ተባብረው የሚሰሩበት እንጂ፤ በወዳጅና ጠላትነት ላይ ባጠነጠነ ትርክት እርስ በርሳቸው እንዲጋጩ፣ ለማንነት በእጅጉ ከፍ ያለ ግምት በመስጠት አገራዊ ማንነት ላይ የጎላ ጥላቻ እንዲፈጥሩ የማድረጊያ ስርዓት አይደለም፡፡ የፌዴራል ሥርዓት፣ ዜጎች ራሳቸውን በራሳቸው፣ የጋራ አገራቸውንም በጋራ የሚያስተዳድሩበት እንጂ፤ በእኔ አውቅልሃለው የሞግዚት ልጅነት ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ፤ በጋራ አገራቸው ውስጥ ባይተዋር ተደርገው እንዲኖሩ የሚደረግበት ሥርዓት አይደለም፡፡

የፌዴራል ሥርዓት አንዱ ስለ አገሩ የሚያውቅና የሚታመን፣ ሌላው ስለአገሩ ግድ የሌለው ተደርጎ እንደ ጠላት የሚታይበት ሳይሆን፤ ሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች ስለ አገራቸው እኩል ግድ የሚሰጣቸው፣ በአገራቸውም ተመጣጣኝ ውክልና ሊኖራቸው እና በራሳቸውም ሆነ በአገራቸው ጉዳይ በባለቤትነት ወሳኞች የሚሆኑበት ሥርዓት ነው፡፡ ብልጽግናም እውነተኛ ፌዴራሊዝምን እውን ለማድረግ ላለፉት ሶስት ኣመታት የሰራው እነዚህን መሰል ህጸጾች ለማስወገድ ነው፡፡ ከዚህ መሰረታዊ እውነታ በመነሳት በለውጡ ማግስት ሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል የታቀፉበት፣ ሁሉም እኩል የሚበለጽጉበት የፌዴራል ስርዓት መገንባት የጀመረ ሲሆን፤ በዚህም የህዝብ ጥያቄዎችን መመለስ ችሏል፡፡

በፌዴራል ሥርዓቱ የክልሎች ቁጥር አስር መድረስም የዚህ ስራው አንድ ማሳያ ሲሆን፤ ሌሎች ለመመለስ በሂደት ላይ ያሉም በርካታ የህዝብ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ይህ ደግሞ ብልጽግና በዴሞክራሲ ልምምድ ውስጥ እውነተኛ ፌዴራሊዝንም ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበትና ተግባራዊ ምላሽም ያረጋገጠበት ሲሆን፤ ይሄንኑ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ይሄን መሰል ስራ ስኬታማ ለማድረግ ደግሞ የዴሞክራሲ ሥርዓትንና የተቋማት ግንባታን እውን ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ብልጽግናም ይሄን ተገንዝቦ የዴሞክራሲ ስርዓቱንም ሆነ ዘመን ተሻጋሪ እና ከፓርቲ ይልቅ ኢትዮጵያን የሚመስሉ ተቋማትን መገንባት ጀምሯል፡፡ በዚህ ረገድ በመከላከያ፣ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ በፍትህ ተቋማት፣ በምርጫ ቦርድና ሌሎችም የሲቪክና ዴሞክራሲ ተቋማት ላይ የተደረጉ ሪፎርሞች እንዲሁም የሕግ ማሻሻያዎች ዓበይት ማሳያዎች ናቸው፡፡

ይህ ተቋማትን ነጻ፣ የመፈጸም አቅም ያላቸው፣ በሁሉም ዘንድ የሚታመኑና ከፓርቲ ባሻገር ያለችን ኢትዮጵያን የሚመስሉ እንዲሆኑ ማስቻሉን ለማረጋገጥ ደግሞ፤ አሸባሪው የህወሓት ጁንታ ቡድንን በአጭር ጊዜ ልክ ያስገባውን መከላከያ ሰራዊት፤ ከመንግስት ልሳንነት ወጥቶ መንግስትን መተቸት የጀመረውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፤ ብዙዎች እምነት አጥተውበት ዘመናትን ያሳለፉትና የምርጫ ጣዕሙን እንዳናጣጥም አድርጎን የቆየውን ምርጫ ቦርድ አሁናዊ አቋምና ተግባር መፈተሽ ከብዙ በጥቂቱ ስራውን እንድንረዳ የሚያስችሉ ናቸው፡፡
እነዚህና መሰል እርምጃዎች ደግሞ ብልጽግና በኢትዮጵያ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ከዴሞክራሲ አጣምሮ ለመሄድ እያደረገ ያለውን ጅማሮ አመላካች ሲሆኑ፤ ይህ ጉዞውም ለዘመናት ታፍኖ የቆየውን የህዝቦችን ጥያቄ በመመለስ ጭምር የተረጋገጠ ነው፡፡ ብልጽግና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ፌዴራሊዝንም በመተግበር ሂደቱ የራስም ሆነ የጋራ አስተዳደርን በላቀ ሁኔታ እየተገበረም፤ በቀጣይም ለመተግበር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው፡፡

ብልጽግና እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ከዴሞክራሲ ጋር አጣምሮ እውን ለማድረግ ሲሰራም ሆነ ሊሰራ ሲያስብ ሂደቱ አልጋ በአልጋ ነው ወይም ይሆናል ብሎ አይደለም፡፡ እንደማይሆንም ታይቷል፡፡ ይሁን እንጂ እውነተኛ ፌዴራሊዝንም እውን ማድረግ የምርጫ ጉዳይ ያለመሆኑን ስለሚገነዘብ፤ ኢትዮጵያን መስሎ እውነተኛዋን ኢትዮጵያ የሚመስል ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ስለሚያምንና የሚገጥሙትን መሰናክሎች የሚሻገርባቸውን አቅጣጫዎች ነድፎ መስራቱ አዋጪ መሆኑን በማመን በዚሁ አግባብም ስለሚሰራ ነው፡፡ ብልጽግና በፈተና ውስጥ ተጸንሶ፣ በፈተና ውስጥ የተወለደ እና በፈተና ውስጥ ጎልብቶ በፈታኝ ችግሮች መከበቡ ሳያግደው በውጤት ታጅቦ ለዛሬ የደረሰ የኢትዮጵያን ትንሳኤ አብሳሪ ፓርቲ ነው፡፡

በቀጣይም ኢትዮጵያን የሚመጥን የፌዴራሊዝም ስርዓት በመገንባት ሂደት ውስጥ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በማሳተፍ፤ ነጻ፣ ገለልተኛና የመፈጸም አቅም ያላቸው የሲቪክና ዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባት፤ በመደመር እሳቤ የተቃኙና ህዝብን ባሳተፈ መልኩ የሕግና ፖሊሲ ዎቹን እየቃኘ ይጓዛል፡፡ ብልጽግና ኢትዮጵያን የመሰለ፣ ብዝሃነትን የተላበሰ፣ ጠንካራ አደረጃጀትና ፖሊሲ ያለው እና ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማዋ ሊያሻግር የሚችል አቅም ያለው ፓርቲ ነው፡፡ በመሆኑም የራስም ሆነ የጋራ አስተዳደርን፣ እንዲሁም በጠንካራ የተቋማት ግንባታ ዴሞክራሲን እውን እንዲሆን እና የሁሉም የሆነች ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ያለዎትን ህልም በተግባር ለማረጋገጥ ብልጽግናን ይምረጡ!!!

እኛ ብልጽግና ነን!

Leave a Reply