ኢትዮጵያውያን በዘመናት ውስጥ እርስ በርስ ተሳስረዋል፤ በጠበቀ ማንነት ተጋምደዋል። በዓለም ዘንድ ታላቅ በሚያደርጋቸው ፍቅርና ትስስርም ተሰናስነዋል። የእነርሱ ጥብቅ መተሳሰር የመጣው በዘመናት ነው። ለዚህ በዘመናት ውስጥ ደማቸውን ቀለም፣ አጥንታቸውን ብዕር አድርገው የጻፉትን መልካም ታሪክ ዋቢ ማድረግ እንደሚቻል ብልጽግና ያምናል።
በረጅም ዘመን ታሪክ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ችግሮች ዜጎች ባደረጓቸው እንቅስቃሴዎች በተፈጠሩ ግንኙነቶች የተከሰቱ የእርስ በርስ መጋመዶች መፈጠራቸው እውነት ነው። አነድነትን አንደ ሸማ ለብሰው ዜጎች አንዳቸው ከሌሎች ተጋምደዋል ተዋልደዋልም። ኢትዮጵያዊ አንድነት በእውነት፣ በእምነትና በሃይማኖት እንደድርና ማግ ተሸምኗል።
በብልጽግና አተያይ ኢትዮጵያውያን ከውጭ የመጣን ጠላት ለመከላከል፣ ለማጥቃትና የጋራ ክብራቸውን እንዳይገሰስ ለማድረግ አኩሪ መስዋዕትነት ከፍለው ተፋልመዋል። ጠላትን ድል ነስተው ሉዓላዊነቷ የተከበረ አገር አስረክበውናል። ኢትዮጰያዊ ሆነው ኖረው ኢትዮጵያን ሰርተዋታል። በሌላ በኩል ተጋብተው ወልደው ተዛምደዋል። ከቦታ ቦታ በተንቀሳቀሱበት አጋጣሚ እንኳን ራሳቸውን አስተሳስረዋል።
በአንድ አካባቢ ድርቅ ሲነሳ ለምለም ወደ ሆነው አካባቢ ተጉዘዋል፤ ጎርፍ ሲያጠቃቸው ወደ ወንድማቸው ሰፈር አቅንተው ቤት ሰርተዋል፤ ትዳር መስርተው ወልደው ከብደዋል። መኖሪያቸውን በቀየሱበት አካባቢ ከማህበረሰቡ ጋር ጥብቅ ትስስር ፈጥረዋል። እነዚህ ለዓመታት የተካሄዱ የዜጎች እንቅስቃሴዎች አንዱ ብሄር ከሌላው ብሄር፣ አንዱ ጎሳ ከሌላው ጎሳ፣ የአንዱ እምነት ከሌላው እምነት ጋር ያለውን አኩሪ እሴት እንዲለዋወጥ፣ አንዱ የሌላውን እንዲያዳብር፣ እንዲያከብርና እንዲያበለጽግ እድል ፈጥሯል። በዘመናት ውስጥ በገነቡት ማህበራዊ ትስስር አዳዲስ ነገሮችን እንዲፈጥሩም አድርጓቸዋል። አንድ የማህበረሰብ አባል ችግር ሲደርስበት በፍጥነት የሚታገዝበት መንገድ፣ የኢኮኖሚ አቅም ክፍተት ሲያመጣ በጋራ የሚፈቱበት ስልት ቀይሰው እየተጋገዙና አንተ ትብስ እኔ እየተባባሉ ዘመናትን አስቆጥረዋል። ይህ ትልቅ እሴት አብሮነትን ለማጠናከርና በልዩነት ትርክት እየተሸረሸረ የመጣውን አንድነትን ለመመለስ መሰረታዊ እሴት መሆኑን ብልጽግና በሚገባ ይረዳል።
በየትኛውም አገር ጠንካራ አገረ መንግስት በሚፈጠርባቸው መንገዶች ህዝቦችን ሊያስከፉ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ። በዚህ ሂደት ዜጎች ሊጎዱ፣ ቀድሞ የነበራቸውን ሊያጡ ይችላሉ። እነዚህ ነገሮች የሚፈጥሯቸው አሉታዊ ስሜቶች መኖራቸውን ብልጽግና ፓርቲ ያምናል። አምኖ ግን እነርሱ ላይ አይቸከልም።
ፓርቲው እነዚህ አሉታዊ ስሜቶች ዘላቂ ሆነው የዛሬን ሰላምና አብሮነት፣ የነገን ተስፋና እድገት ማናጋት አለባቸው ብሎ አያምንም፤ በፍጹምም አይቀበልም። ዘመኑ የዚህ ዓይነቱን ድርጊትም ሆነ አስተሳሰብ የመሸከም አቅም የለውም። በሃያ አንደኛው ክፍለዘመን ውስጥ ሆነን ከዓመታት በፊት በተደረጉ ጉዳዮች መቆዘ ከችገር ውጪ ጠብ የሚያደርገው አንዳችም ቁም ነገር እንደሌለ ብልጽግና በጽኑ ያምናል። ይሄኛው ክፍለዘመን የሚጠይቀውን ፈጣን ሩጫ ያለማቅማማት እየሮጥን ሌሎች የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ እንተጋለን እንጂ በትናንት የታሪክ አሻራ በእግረ ሙቅ መታሰርንም ብልጽግና አይቀበልም።
ይልቁኑ በመካከላችን የገነባናቸው መልካም እሴቶችን በመጠቀም ህብረ ብሄራዊ አንድነታችንን ማጠናከር አለብን ብሎ የሚያምነው ብልጽግና ለዚህ እውን መሆን በጽት እየሰራ ይገኛል። በዚህም ከጅምሩ አንድነታችን በተግባር ተአምራትን ሲሰራ አስተውለናል። አንድነታችን ጠላቶቻችን ሲያስበረግግ፤ መለያየታችን ደግሞ ሲያስፈነድቅ በራሳችን ዘመን በተጨባጭ አይተናል። ጠላት እንዳይፈነድቅና ዒላማውን እንዳይመታ እንተጋለን እንጂ በታሪክ አጋጣሚ በተከሰቱ ትናንሽ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተን አሁናችንን አንገድልም። አንድነታችን የሚፈጥረውን ተአምር ለማየት እንጓዛለን እንጂ በመለያየታችን ውድቀታችንን ለመጋበዝ የሚጥሩትን ለመስማት ጊዜያችንን ለማንም አንሰጥም።
ትናንት ጣሊያን ለዓመታት ተዘጋጅቶ በወቅቱ የዘመነ መሳሪያ ይዞ በድፍረት በቅኝ ግዛት ሊያስተዳድረን ባህር ተሻግሮ ሲመጣ አባቶቻችን በጋራ ሆነው በአልበገርም ባይነት በጦር በጎራዴ በጥቂት ሰዓታት ድል ነስተውታል። በዚህም ህብረ ብሄራዊ አንድነታችን ተአምር ሲሰራ በተጨባጭ ታይቷል። እናት አባቶቻችን የፈሰሰ ደማቸውን አዋህደው፣ የተከሰከሰ አጥንታቸውን አጥር አድርገው ጠላት እንዳይገባ ድንበሩን የዘጉት ለአገር ባለቸው ቀናኢነትና በህብረ ብሄራዊ የአንድነት መንፈስ እንጂ ቂምና ጥላቻን በመቁጠር አይደለም። እንደዚህ ዓይነቱ ክስተት ከአካባቢያዊ ግጭት ያለፈ ለእኔ ብቻ ከሚል ስሜት የዘለቀ አንድነት መፈጠሩን ያበስራል።
በየትኛውም አካባቢ ግጭቶችም ሆኑ አለመግባባቶች ይፈጠራሉ። በማንኛውም አገረ መንግስት ግንባታ አለመግባባቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። እነዚህ የውስጥ ችግሮች በሽማግሌ ተይዘው በእርቅ ይፈታሉ። በየአካባቢው ባህልና ወግ መሰረት መፍትሄ ያገኛሉ። ከግጭትና አደጋ ከመፍጠር ይልቅ በሽማግሌዎች ምክርና ሀሳብ ነገሩ በመፍታት ለዘላቂ ጉዳይ ትኩረት ይሰጣል። ቂም በቀል ሳይሆን ቀጣዩን ዘመን በማስተዋል ትልቁ ጉዳይ ላይ ለመስራት ትኩረት ይደረጋል። በራስ ባህልና ወግ የሚፈታ ችግር፣ በዘመናዊ አስተሳሰብ ተቃኝቶ በሀሳብ ልዕልና የሚገታ ስሜት ዘላቂ መፍትሄ እንደሚፈጥር ብልጽግና ፓርቲ ያምናል።
ለዚህም ነው ብልጽግና ፓርቲ በአገራችን የቂምና የጥላቻ ታሪክ ምዕራፍ እንዲዘጋ ባህላዊና ዘመናዊ የእርቀ ሰላም ግንባታ አማራጮችን በመጠቀም እርቀ ሰላም ለማውረድ የወሰነውና በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ቂምና ቁርሾ እንዳይወራረስ ተግቶ ለመስራት ቁርጠኛ አቋም የያዘው። ብልጽግና ወንድማማችነትን በማስቀደም ህብረ ብሄራዊነትን ያከበረ አንድነትንና እኩልነትን ለመፍጠር የሚያስችለውን ሰላም ለማረጋገጥ ተግቶ የሚሰራው ለአገረ መንግስት ግንባታ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን በማመን ነው።
ብልጽግና በትናንት የሚቆዝምና እርሱን እየተረከ ለመሄድ የሚፈልግ ፓርቲ አይደለም። ብልጽግና በዜጎች የጥላቻና ቁርሾ ትርክቶች የራሱን ቦታ ለማግኘት የሚሻ ፓርቲም አይደለም፤ አይሆንምም። አሁን ላይ ለዛሬ፣ ዛሬ ላይ ለነገ ጠንካራ ወንድማማችነትን መሰረት ያደረገ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለመገንባት የሚተጋ ፓርቲ ነው እንጂ። ብልጽግና ጥላቻንና ቂምን በነባር መልካም እሴቶች እያከመ፣ ለዘመናት የገነባናቸውን ሀብቶቻችንን እያበለጸገ የኢትዮጵያን ህዳሴ እውን ለማድረግ የሚሰራ ፓርቲ ነው። ይህንንም ባለፉት ሶስት ዓመታት የመጣበት መንገድ አረጋግጧል። በቀጣይም ለመከተል የወሰናቸው የወንድማማችና የእኩልነት ትርክቶቹ ምስክር ይሆኑታል።
ፓርቲያችን ሰላምን ለመገንባት በሚከናወኑ ተግባራት ለእያንዳንዱ ግለሰብ ጥረት እውቅና ይሰጣል። የእያንዳንዳችን መልካም ጥረትም ሆነ ነባር እሴቶችን ማበልጸግ እንደ አንድ አምፖል ብርሃን ያየዋል። የብዙ አምፖሎች ብርሃን ጨለማን በሃይሉ እንደሚገፍ ሁሉ የእያንዳንዳችን በመደመር እሳቤ ብልጽግናን መምረጥ የኢትዮጵያን የብልጽግና ብርሃን እውን እንደሚያደርገው በጽኑ ያምናል። ብርሃን ብርሃንን እንደሚመርጥና ጨለማን እንደሚገፍ አምነው ብርሃን የረጨውን አምፖልን ይምረጡ ይልዎታል!
እኛ ብልጽግናዎች ነን!