You are currently viewing ህዝባችን ንቃ፤ይሄ የፖለቲካ ዲስኩር አይደለም፤

ህዝባችን ንቃ፤ይሄ የፖለቲካ ዲስኩር አይደለም፤

  • Post comments:0 Comments

የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢ/ር ስለሺ በቀለ በግጥምን በጃዝ መድረክ ላይ ተገኝተው ለታዳሚው ካስተላለፉት መልዕክት የተወሰደ

*********************************************************************************************

2013 ዓ/ም ምርጫችን በዴሞክራሲ መንገድ ለዴሞክራሲ መሰረት ለመጣል በሰላም መከወንና ጠንካራ ስርዓት ለመመስረት እንዲሁም የህዳሴ ግድባችንን ግንባታ ከ560 ሜትር ወደ 595 ሜትር አድርሰን ወሃችንን ሂደቱ ውልፍት ሳይል በሐምሌ ሞልተን በአዲስ ዓመት መባቻ ሁለት ተርባይን ሃይል ስናመነጭ ያኔ ነው አዲሲቷ ጠንካራዋ ኢትዮጵያ የምትኖረው፡፡

እነኚህ ሁለት ጉዳዮችን በማሳካት ነው ለህልውናችን፣ ለዕድገታችን፣ ለአገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግና መሰረት በመጣል ኢትዮጵያዊነታችንን አንድነታችንን የምናስከብረው፡፡የማይበገሩት ጀግኖች አባቶቻችንን እናቶቻችንና አያቶቻችን ያቆዩትን አሸናፊነት ለልጆቻችን የምናረጋግጠው፡፡ያኔ ነው አፍሪካም ጭምር የምታሽነፈው፡፡

ለሁለቱም ጉዳዮች የሁላችንንም ትኩረታችንን፣ አይናችንን፣ጆሯችንን ሃሳባችንን በዋነኝነት ተግባራችንን ማሰባሰብ ያስፈልጋል፡፡በእነኚህ ጉዳዮች ላይ ላብና ደም እየፈሰሰ ነውና ቀልድ የለም፡፡

ኢትዮጵያ የዓባይወይም ናይል ዋናዋ ምንጭ አገር ነች፡፡ 86% የሚሆነው የናይል ፍሰት አስዋን ላይ ሲለካ ከኢትዮጵያ የሚፈስ ነው፡፡ ይህም በዋነኛነት ከዓባይ 59%፣ባሮ 14%፣ተከዜ መረብ 13% ሌሎቹ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች 14% የሚሆነውን ብቻ በነጭ ዓባይ በኩል ወደ ዋናው ናይል ይገብራሉ፡፡

በአጠቃላይ የናይል ፍሰት መጠን ግምት 84.5 ቢሊዬን ተብሎ ቢገመትም ብዙ ጥናቶቻችን ይህንን አሃዝ ከፍ ያደርጉታል፡፡አንዱም ማሳያ ለምሳሌ ይህንን ስንደምረው የኢትዮጵያ አማካይ 77 ቢሊዬን የሚሆነው ፍሰት ወደ ናይል ይፈሳል፡፡

ግብጽ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የናይልን ውሃ በሞኖፖል ማልማትና መቆጣጠር ዋነኛ ዓላማዋ ነው፡፡በመሆኑም ከ19ኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ ዘመናዊ የመስኖ እርሻን በከፍተኛ ደረጃ ያስፋፋች ሲሆን ተጨማሪ ልማት ለማካሄድና የውሃ ፍላጎቷን ለመጠበቅ ከተፋሰሱ የራስጌ አገሮች የሚመነጨውን የናይል የውሃ አቅርቦት ከተፋሰሱ ውጭ በማውጣትም ጭምር ለመጠቀምና በዚሁ መንገድ ማስቀጠል የምንጊዜም ፍላጎቷ ነው፡፡

ይህ ዓለም አቀፍ ህግ ብለው ሁልጊዜም የሚናገሩት ትክክለኛ ያልሆነ ኢትዮጵያን ለዘላለማዊ ጉዳት ያቆዬ አይነት ኢ-ፍትሃዊ አሰራር ነው፡፡ለዚህ የግብጽ ፍላጎት መሳካት ቀኝ ገዢዋ እንግሊዝ ልማቱን በማስፋፋትና ኢ-ፍትሃዊ ስምምነቶችን በማድረግ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች፡፡

የእንግሊዝ መንግስት ከግብጽ ጋር በሌሎች የራስጌ አገሮች ኬንያ፣ሱዳን፣ ታንዛንያ እና ኡጋንዳ የኛይል የውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ በ1929 ዓ/ም ያደረገችውና የግብጽን ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቀው ኢ-ፍትሃዊ ስምምነት ለዚህ አብነት ነው፡፡ስምምነቱ ከፍተኛውን የውሃ ድርሻ ለግብጽ የደለደለ ሲሆን አገሮቹ ከግብጽ ቅድመ ሁኔታ ሳያገኙ የናይልን ውሃ የግብጽን ጥቅም በሚጎዳ መንገድ ለመስኖ፣እርሻም ሆነ ለሃይል ማመንጫ ማንኛውም ስራ እንዳይሰሩ ይከለክላል፡፡በአንጻሩ ስምምነቱ ግብጽ በሱዳንና በራስጌ አገሮች ግዛት ውስጥ ውሃ ለማጠራቀም ወይም ለመጨመር የሚያስችል የግንባታ ስራ እንድትሰራ ይፈቅድላታል፡፡ ከዚህም ውስጥ  Veto Power የመሳሰሉትን ሰጧታል፡፡

የራስጌ አገሮች ነጻ ሲወጡ እኛን አይመለከትም፣ሱዳንን ጨምሮ የ1929 ስምምነቱን ቀኝ ገዢ በሆነችው እንግሊዝ የተፈጸመ በመሆኑ ተቀባይነት እንደማይኖረውና በናይል ውሃ የመጠቀም መብታቸው የተጠበቀ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡ሲዳን ያንን የሚተካ ወይም የሚያሻሽል ስምምነት በ1959 ከግብጽ ጋር ተፈራርማለች፡፡በዚህ ስምምነት መሰረት 84 ቢሊዬን ኩዪቢክ ሜትሩን ግብጽ 55.5 ቢሊዬን ኩዪቢክ ሜትር ሱዳን 18.5 ኩዪቢክ ሜትር ቀሪው 10 ቢሊዬን ኩዪቢክ ሜትር ውሃ ደግሞ በትነት አስዋን ግድብ እንደሚጠፋ ወይም እንደ ሜዲትራሊያን ተቆጥሮ ተቀንሷል፡፡ሌሎቻችን እንደሌለን አድርጎ የቆጠረ አስተሳሰብ ነው፡፡

ግብጽና ሱዳን ይህንን ስምምነት ሲያደርጉ ሌሎች የናይል የራስጌ አገሮች ተካፋይ አልነበሩም፡፡ኢትዮጵያ ስምምነቱን እንደማትቀበለው በጊዜው በ1929 እና በ1959 ዓ/ም አሳውቃለች፡፡ዳሩ ግን ሁለቱ የግርጌ አገሮች በመካከላቸው የተደረገ ስምምነት የተካፈሉት የናይል ውሃ Historical Right ብለው በመውሰድ የራስጌ አገሮቹ መጠየቅ እንደሌለባቸው ይናገራሉ፡፡እኛ ደግሞ አመንጪዎቹ Natural Right ነን፡፡

ይህ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ኋላ ቀር እሳቤ ሲሆን የኢትዮጵያ ቀጣይ ልማት እና ህዳሴ ግድባችን ላይ የተረባረበ ቅናት ነው፡፡ከዚህ ውጭ ምንም ሊባል አይቻልም፡፡እነኚህ አገራት የአንዷ እንኳ ድሮም እንደዛ ነው፤ሁለተኛዋን ጨምሮ ህዳሴያችንን ለማደናቀፍ የውክልና ጦርነት፣ማበጣበጥ፣ዘረኝነትን መሰረት አድርጎ እገዛ እያደረጉ ማጣላት፣ወረራና የመሳሰሉትን ተጠቅሞ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማቲክ ጫና እረ ስንቱ እረ ስንቱን ይሞክራሉ፡፡

ህዝባችን ንቃ፤ይሄ የፖለቲካ ዲስኩር አይደለም፤

 

ምላሽ ይስጡ