You are currently viewing ግድቡ ኢትዮጵያ ሃብቷን በራሷ አቅም አልምታ ችግሮቿን መፍታት እንደምትችል የምታሳይበት ነው … ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ

ግድቡ ኢትዮጵያ ሃብቷን በራሷ አቅም አልምታ ችግሮቿን መፍታት እንደምትችል የምታሳይበት ነው … ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ

  • Post comments:0 Comments
የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ሃብቷን በራሷ አቅም አልምታ ችግሮቿን መፍታት እንደምትችል የምታሳይበት ፕሮጀክት ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ።
ዶክተር ቢቂላ በኢትዮጵያ እየተገነቡ በሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ዜጎች ንቁ ተሳትፎ እንድያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ የታላቁን የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ ለማከናወን ዝግጁ መሆኗንም ለኢዜአ ተናግረዋል።
የአገረ መንግስት ግንባታ ረዥምና ጊዜ የሚጠይቅ ሂደት መሆኑን ያነሱት ዶክተር ቢቂላ፤ ሂደቱ የዜጎችን አብሮነትና ትስስር በእጅጉ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
የዜጎችን ትብብር ከሚጠይቁ አገራዊ ፕሮጀክቶች አንዱ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ መሆኑን ገልጸዋል።
ግድቡ እያንዳንዱ ዜጋ ዋጋ የከፈለበት መሆኑን በማንሳት ለዚህም “በዓለም ሠማይ ስር ያለ ኢትዮጵያዊ በሙሉ ፕሮጀክቱን አንደ ዓይኑ ብሌን ሊጠብቀው ይገባል” ብለዋል።
ግድቡ ኢትዮጵያ የማንንም ፈቃድ ሳትጠይቅ የራሷን ሀብት በራሷ አቅም አልምታ ችግሮቿን መቅረፍ እንደምትችል የምታስመሰክርበት መሆኑን ገልጸው፤ የግድቡን ግንባታ ከዳር ለማድርስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲተባበር ዶክተር ቢቂላ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታራምደውን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት እሳቤ ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በማስገንዘብ ረገድ በሚጠበቀው ልክ እንዳልተሰራም ተናግረዋል።
በአንጻሩ በወንዙ ላይ የተሳሳተ ትርክት የሚያራምዱ አገራት “ከእኛ በተሻለ አቋማቸውን ለማስረጽ ስራዎችን እየሰሩ ነው” ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን የዘርፉ ምሁራን በኢትዮጵያ እጅ ያለውን እውነታ በማሳወቅ ረገድ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሀገሪቱ የተፈጥሮ ሃብቷን በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የመፍታት መብት እንዳላት ትኩረት ማድረግ አንዳለበትም እንዲሁ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሁናዊ የግንባታ አፈጻጸም 80 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ የግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትም በመጪው ክረምት እንደሚከናወን ተገልጿል።

ምላሽ ይስጡ