You are currently viewing ብልጽግናና መልካም እሴቶች አይነጣጠሉም!!

ብልጽግናና መልካም እሴቶች አይነጣጠሉም!!

  • Post comments:0 Comments

ኢትዮጵያውያን በዘመናት ውስጥ እርስ በርስ ተሳስረዋል፤ በጠበቀ ማንነት ተጋምደዋል። በዓለም ዘንድ ታላቅ በሚያደርጋቸው እነርሱነታቸው ተሰናስነዋልም። የእነርሱ ጥብቅ መተሳሰር የመጣው በዘመናት ሂደት ነው። ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። በዘመናት ውስጥ ደማቸውን ቀለም፣ አጥንታቸውን ብዕር አድርገው የጻፉትን መልካም ታሪክ ዋቢ ማድረግ እንደሚቻል ብልጽግና ፓርቲ ያምናል።

በብልጽግና አተያይ ኢትዮጵያውያን ከውጭ የመጣን ጠላት ለመከላከል፣ ለማጥቃትና የጋራ ክብራቸው እንዳይገሰስ ለማድረግ ተፋልመዋል። ጠላታቸውን ድል ነስተው ሀሴታቸውን ተጋርተዋል። ኢትዮጵያዊ ሆነው ኖረው ኢትዮጵያን ሰርተዋታል። በሌላ በኩል ተጋብተው ወልደው ተዛምደዋል። ከቦታ ቦታ በተንቀሳቀሱበት አጋጣሚ እንኳን ራሳቸውን አስተሳስረዋል።

በአንድ አካባቢ ድርቅ ሲነሳ ለምለም ወደ ሆነው አካባቢ ተጉዘዋል፤ ጎርፍ ሲያጠቃቸው ወደ ወንድማቸው ሰፈር አቅንተው ቤት ሰርተዋል፤ ትዳር መስርተው ወልደው ከብደዋል። መኖሪያቸውን በቀየሱበት አካባቢ ከማህበረሰቡ ጋር ጥብቅ ትስስር ፈጥረዋል። እነዚህ ለዓመታት የተካሄዱ የዜጎች እንቅስቃሴዎች አንዱ ብሄር ከሌላው ብሄር፣ አንዱ ጎሳ ከሌላው ጎሳ፣ የአንዱ እምነት ከሌላው እምነት ጋር ያለውን ባህላዊ እሴት እንዲለዋወጥ፣ አንዱ የሌላውን እንዲያዳብርና እንዲያበለጽግ እድል ፈጥሯል። በዘመናት ውስጥ በገነቡት ማህበራዊ ትስስር አዳዲስ ነገሮችን እንዲፈጥሩም አድርጓቸዋል።

አንድ የማህበረሰብ አባል ችግር ሲደርስበት በፍጥነት የሚታገዝበት መንገድ፣ የኢኮኖሚ አቅም ክፍተት ሲያመጣ በጋራ የሚፈቱበት ስልት ቀይሰው እየተጋገዙና አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ እየተባባሉ ዘመናትን አስቆጥረዋል። ይህን ትልቅ አብሮነት ለማጠናከር፣ በልዩነትና ከፋፋይ ትርክት እየተሸረሸረ የመጣውን አንድነት ለመመለስ ብልጽግና ፓርቲ በትኩረት ይሰራል፤ መሰረታዊ እሴት መሆኑንም ብልጽግና በአጽንኦት ይቀበላል። ይህም በማንኛውም ወቅት በየትኛውም አገር ጠንካራ አገረ መንግስት ከሚፈጠርባቸው መንገዶች አንዱ ነው።

ብልጽግና ፓርቲ አሉታዊ ስሜቶችና አጋጣሚዎች የዛሬን ሰላምና አብሮነት፣ የነገን ተስፋና እድገት ማናጋት አለባቸው ብሎ አያምንም፤ በፍጹም አይቀበልምም። ዘመኑ የዚህ ዓይነቱን ድርጊትም ሆነ አስተሳሰብ የመሸከም አቅም የለውም። በሃያ አንደኛው ክፍለዘመን ውስጥ ሆነን ከረጅም ዓመታት በፊት በተደረጉ ጉዳዮች አንቆዝምም። ይልቁንም ያለፉትን ምርጥ ተሞክሮዎች እሴት አድርገን እንደ ወረት የምንጠቀምባቸውን ያህል ካለፉ ጉድለቶችና ተግዳሮቶች ትምህርት በመውሰድ እንዳይደገሙ እንማርባቸዋለን።

ያለንበት ክፍለዘመን የሚጠይቀውን ፈጣን ሩጫ ያለማቅማማት እየሮጥን ሌሎች የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ እንተጋለን እንጂ በትናንት በተሰራ ስህተት በታተመ የታሪክ አሻራ በእግረ ሙቅ መታሰርን ብልጽግና አይቀበልም። በመካከላችን የገነባናቸው መልካም እሴቶችን በመጠቀም ህብረ ብሄራዊ አንድነታችንን እናጠናክራለን።

አንድነታችን ጠላቶቻችን ሲያስበረግግ፤ መለያየታችን ደግሞ ሲያስፈነድቅ በራሳችን ዘመን በተጨባጭ አይተናል። ጠላት እንዳይፈነድቅና ዒላማውን እንዳይመታ እንተጋለን እንጂ በታሪክ አጋጣሚ በተከሰቱ ትናንሽ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተን አሁናችንን አንገድልም። አንድነታችን የሚፈጥረውን ተዓምር ለማየት እንጓጓለን እንጂ በመለያየታችን ውድቀታችንን ለማወጅ የሚጥሩትን ለመስማት ጊዜያችንን ለማንም አንሰጥም።

ትናንት ጣሊያን ለዓመታት ተዘጋጅቶ በወቅቱ የዘመነ መሳሪያ ይዞ በድፍረት በቅኝ ግዛት ሊያስተዳድረን ባህር ተሻግሮ ሲመጣ አባቶቻችን በጋራ ሆነው በአልበገርም ባይነት በጦር በጎራዴ በጥቂት ሰዓታት ድል ነስተውታል። ህብረ ብሄራዊ አንድነታቸው ተአምር ሰርቷል። የፈሰሰ ደማቸውን አዋህደው፣ የተከሰከሰ አጥንታቸውን አጥር አድርገው ጠላት እንዳይገባ ድንበሩን የዘጉት ለአገር ባላቸው ቀናኢነትና በህብረ ብሄራዊ የአንድነት መንፈስ እንጂ ቂምና ጥላቻን በመቁጠር አይደለም። እንደዚህ ዓይነቱ ክስተት ከአካባቢያዊ ግጭት ያለፈ “ለእኔ ብቻ” ከሚል ስሜት ከተላቀቀ የዘለቀ አንድነት መፈጠሩን ያበስራል።

በየትኛውም አካባቢ ግጭቶችም ሆኑ አለመግባባቶች ይፈጠራሉ። እነዚህ የውስጥ ችግሮች በሽማግሌ ተይዘው በእርቅ ይፈታሉ። በየአካባቢው ባህልና ወግ መሰረት መፍትሄ ያገኛሉ። ብልፅግና የረጅም ዘመኑ ትርክትና የመለያየት ስሪት በውይይትና ንግግር እንዲፈታ በማድረግ ለዘላቂ ጉዳይ ትኩረት ይሰጣል። ቂም በቀል ሳይሆን ቀጣዩን ዘመን በማስተዋል ትልቁ ጉዳይ ላይ ለመስራት ትኩረት ያደርጋል። በራስ ባህልና ወግ የሚፈታ ችግር፣ በዘመናዊ አስተሳሰብ ተቃኝቶ በሀሳብ ልዕልና የሚገታ ስሜት ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያመጣም ያምናል።

ለዚህም ነው ብልጽግና ፓርቲ በአገራችን የቂምና የጥላቻ ታሪክ ምዕራፍ እንዲዘጋ ባህላዊና ዘመናዊ የእርቀ ሰላም ግንባታ አማራጮችን በመጠቀም እርቀ ሰላም ለማውረድ የወሰነው። በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ቂምና ቁርሾ እንዳይወራረስ ተግቶ ለመስራት ቁርጠኛ አቋም በመያዝ እንዲሁም ወንድማማችነትን በማስቀደም ህብረ ብሄራዊነትን ያከበረ አንድነትና እኩልነትን ለመፍጠር የሚያስችለውን ሰላም ለማረጋገጥ ተግቶ የሚሰራው ለአገረ መንግስት ግንባታ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን በማመንም ነው።

ብልጽግና በትናንት እየቆዘመና እርሱኑ እየተረከ ለመሄድ የሚፈልግ ፓርቲ አይደለም። ብልጽግና በዜጎች የጥላቻና ቁርሾ ትርክቶች የራሱን ቦታ ለማግኘት የሚሻ ፓርቲ አይደለም፤ አይሆንምም። አሁን ላይ ለዛሬ፣ ዛሬ ላይ ለነገ ጠንካራ ወንድማማችነትን መሰረት ያደረገ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለመገንባት የሚተጋ ፓርቲ ነው። ጥላቻንና ቂምን በነባር መልካም እሴቶች እያከመ፣ ለዘመናት የገነባናቸውን ሀብቶቻችንን እያበለጸገ የኢትዮጵያን ህዳሴ እውን ለማድረግ የሚሰራ ፓርቲ ነው። ይህንንም ባለፉት ሶስት ዓመታት የመጣበት መንገድ በጉልህ ያመላክታል።

ፓርቲያችን ሰላምን ለመገንባት በሚከናወኑ ተግባራት ለእያንዳንዳችንን ጥረት እውቅና ይሰጣል። የእያንዳንዳችን መልካም ጥረትም ሆነ ነባር እሴቶችን ማበልጸግ እንደ አንድ አምፖል ብርሃን ያየዋል። የብዙ አምፖሎች ወገግታና የመደመር ኡደት ጨለማን በሃይሉ ገፍፎ ብርሃን እንደሚያጎናፅፈን ሁሉ እያንዳንዳችን በመደመር እሳቤ ብልጽግናን መምረጣችን ለኢትዮጵያውን አዲስ የብልፅግና ጉዞን እንድንጎናፀፍ ያደርጋል። ለዚህም ብርሃን ጨለማን እንደሚገፍ አምነው የብርሃን ተምሳሌት የሆነውን አምፖል ይምረጡ።

እኛ ብልፅግናዎች ነን!! ብልጽግናን ይምረጡ!!

ምላሽ ይስጡ