You are currently viewing የውጭ ምንዛሬ ተመን፣ የወጪ ንግድ ገቢ እና የዋጋ ንረት

የውጭ ምንዛሬ ተመን፣ የወጪ ንግድ ገቢ እና የዋጋ ንረት

  • Post comments:0 Comments

በአንድ ወቅት የሚኖር የውጭ ምንዛሬ ተመን ምጣኔ ወይም የብር ከአሜሪካን ዶላር አንጻር ያለው ዋጋ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ላይ ቀጥተኛና ጠንካራ የሆነ ተፅዕኖ አለው፡፡
የአንድ አገር የውጭ ምንዛሬ ግኝት በዋነኝነት ከአራት ዋና ዋና ሁነቶች ይመነጫል፡፡ እነዚህም ሀገሪቱ ወደ ውጭ ሀገር ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን በመላክ የሚታገኘው ገቢ፣ በዕርዳታና ብድር አማካኝነት የሚገኝ፣ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያን ወደ ሀገር ከሚልኩት እና ከውጭ ቀጥተኝ ኢንቨስትመንት መልኩ ከሚመጣ የሚገኝ ናቸው፡፡

ያደጉና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ልምድና ተሞክሮ አንድ ሀገር ሸቀጦችና አገልግሎቶች ወደ ውጪ ሀገራት በመላክ በአለምአቀፍ ገበያ ተወዳዳራ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ግኝት ዘላቂ እና አስተማማኝ መሆኑን ያሳያል፡፡ በአለምአቀፍ ደረጃ አንድ አገር ከምትወዳደርባቸው መስፈርቶች አንዱ ይዛ የምትቀርበው የሸቀጦችና አግልግሎቶች ዋጋ ነው፡፡ ይህም በውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ ይወሰናል፡፡ የብር ዋጋ ከአሜሪካን ዶላር አንጻር ዉድ ሆኖ እንዲቆይ ማድረግ የወጪ ንግድ ሸቀጦችንና አገልግሎቶች ዋጋ እንዲወደድ በማድረግ የሀገሪቱን አለምአቀፍ ተወዳዳሪነት በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳል፡፡

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ዙሪያ ያላት አፈጻጸም እጅግ ደካማ የሚባል ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የሀገራችን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ምንጭ በዋነኛነት በውጭ ዕርዳታና ብድር ላይ እንዲጠለጠል በማድረግ አጠቃላይ ኢኮኖሚው ወደ የማይወጣበት አዙሪት ወይም ቅርቃር ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡

በመሆኑም ዘላቂና አስተማማኝ ወደ ሆነው የውጭ ምንዛሬ ግኝት ምንጭ ማተኮር አማራጭ የሌለው ዘላቂ መፍትሔ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ገቢ የበለጠ ለማሻሻል ሁሉን አቀፍ የፖሊሲና አስተዳደራዊ እርምጃዎችና እርምቶች እንደሚያስፈልጉ በማመን ብልጽግና ከፖሊሲ፣የህግ ማዕቀፍ ጀምሮ እስከ አሰራር ያሉትን ማነቆዎችን በመፍታት የኢኮኖሚዉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የርፎርም ስራዎች እያከናወነ ይገኛል፡፡

ከዚህ አንጻር የውጭ ምንዛሬ ተመንን ከጥቁር ገበያ ተመን አንጻርም ይሁን የኢትዮጵያ የወጪ ንግድን በማነቃቃት ምርታማና ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያስችል ተመን እንዲኖር ማድረግ ወሳኝምና ግዴታም ነው፡፡ አለበለዚያ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን አሳድጎ ኢኮኖሚውን ከቅርቃር ለማስወጣት ሌላ ዘላቂና አስተማማኝ መንገድ ይኖራታል ብሎ ብልፅግና አያምንም፡፡

የወጪ ንግድን የበለጠ ለማበረታታት ደግሞ የውጭ ምንዛሬ ተመንን በማስተካከል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እውነትም የወጪ ንግድ መር ኢኮኖሚ ማድረግ ብልጽግና የሚከተለው መንገድ ነው፡፡ በዚህም ምርታማና ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚን በመገንባት በመጠንና በአይነት በቂ የሆነ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ያስችላል፡፡ ይህም ከምርት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚከሰትን የዋጋ ንረት በመከላከል ዜጎች በተሻለ ዋጋ በቂ ምርት እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡

ይህንን በቅጡ ባለመረዳትም ይሁን የዜጎችን አሁናዊ ችግር አንደመቀስቀሻ ለመጠቀም የሚፈልጉ እንደሚያደናግሩት ሳይሆን ይልቁንም የኢትዮጵያ ብር ከአሜሪካን ዶላር አንጻር ያለው ዋጋ እንዲወደድ ማድረግ ውጤቱ ኢትዮጵያ የውጭ ሀገራት ሸቀጦችና አገልግሎቶች ማከማቻና ማራጋፊያ እንድትሆን በማድረግ ምርታማነቱና ተወዳዳሪነቱ ዝቅተኛ የሆነ ጥገኛ ኢኮኖሚን መገንባት ነው፡፡ ይህም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በውጭ ዕርዳታና ብድር ላይ ጥገኛ እንዲሆን በማድረግ ኢኮኖሚውን ከማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ወደለየለት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ ብሎም የፖለቲካ ቀውስ የሚያሸጋግር ይሆናል፡፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት ብልጽግና በወጪ ንግድ ዙሪያ በወሰደው የፖሊሲና አስተዳደራዊ እርምጃዎች አበረታችና ተስፋ ሰጪ የሆኑ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ከ2003 በጀት ዓመት ጀምሮ የሀገሪቱ የወጪ ንግድ የኋሊት ጉዞ በማስቆም ለመጀመሪያ ጊዜ በ2012 በጀት ዓመት የወጪ ንግድ ገቢ በ12 በመቶ እንዲያድግ ማድረግ ችሏል፡፡ ይህም አፈጻጸም በ2013 በጀት ዓመትም የበለጠ የተሻሻለ እንደሆነ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ያሳያል፡፡ ይህም ብልጽግና እየተከተለ ያለው የፖሊሲ አቅጣጫ ትክክለኛና አዋጭ መንገድ መሆኑን ያመለክታል፡፡

የወጭ ምንዛሬ ተመን ማስተካከል ከወጪ ንግድ ማሻሻል ባሻገር ሌሎች ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ ለአብነት ያህል በሀገሪቱ በኢ መደበኛ ኢኮኖሚ እና ሕገ ወጥ በሆነ አግባብ የሚንቀሳቀስን የአሜሪካን ዶላር ስርጭት በመገደብ ወደ መደበኛ ኢኮኖሚ እንዲፈስ በማድረግ የኢኮኖሚው የማምረት አቅምና ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም የሀገሪቱን ሀብት አዋጭና ምርታማ በሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ እንዲፈስ በማድረግ የኢኮኖሚውን የዕድገት ጉዞ ፈጣንና ዘላቂ እንዲሆን ያደርጋል፡፡

የዉጭ ቀጥተኛም ሆነ የሀገር ዉስጥ ኢንቨስትመንት በማሳደግ ለዜጎች የተሻለ የስራ ዕድል እና ክፍያ ብሎም አጠቃላይ ገቢ እንዲሻሻል የራሱን ሚና ይጫወታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከጥቁር ገበያ ጋር ተያይዞ ያሉ ሀገራዊ የደህንነት ስጋቶችንም ለመከላከል አይነተኛ መንገድም ነው፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ተመን መጣኔ እና የዋጋ ንረት መጣኔ ቀጥተኛና ግልጽ የሆነ ግንኙነት አላችው ብሎ ማስቀመጥ ትክክል አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል ከ1996 – 2010 ባሉት አስራ አምስት ዓመታት የውጭ ምንዛሬ ተመን የተረጋጋ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሆኖም በእነዚህ ዓመታት የዋጋ ንረት በአማካይ ከ15 በመቶ በላይ ነበር፡፡ ይህም የዋጋ ንረትን በቀጥታ ከውጭ ምንዛሬ ተመን መጣኔ ጋር ብቻ ማገናኘት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በአግባቡ ያለመረዳትና በቂ ጥናቶች በጉዳዩ ዙሪያ ካለማድረግ የሚመነጭ ነው፡፡

ብልፅግና የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት የራሱ የሆነ መገለጫ ያለውና ባደጉና በሰለጠኑ ሀገራት የሚስተዋሉ መገለጫዎችና እሳቤዎች በቀጥታ በኢትዮጵያ ይሰራሉና በዛው መልኩ ሊተነተኑ ይገባል ብሎ አያምንም፡፡ ከዚህ አኳያ ብልፅግና የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት በዋነኝነት ከመዋቅራዊ ችግሮችና ከምርት አቅርቦት ጋር የተገናኙ መሆናቸውን ያምናል፡፡ በተለይም ከመዋቅራዊ ችግሮች ጋር ተያይዞ በሰፊው የሚስተዋሉ የንግድ ስርዓት ያለመዘመን እና በግብይት ሰንሰለት ውስጥ የተተበተቡ በርካታ ችግሮች ለዋጋ ንረቱ መባባስ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡

በመሆኑም በቀጣይ ብልጽግና እነዚህን ችግሮች በመፍታት የዋጋ ንረት ዜጎችን እንዳይፈታተን የመግዛት አቅማቸዉን ማሳደግን ጨምሮ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚረዱ ምሉዕ እይታ ያላቸዉ ማሻሻያዎች ማድረጉን ይቀጥላል፡፡ የዉጭ ምንዛሬ ፖሊሲንም በተመለከተ በሂደት ከሌሎች ፖሊሲዎች ጋር እተናበበ የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ለማስተካከል በልዩ ትኩረት የሚሰራ ይሆናል፡፡

ምላሽ ይስጡ