የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወሉ አብዲ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ብልጽግና አገር አቀፍ ፓርቲ በመሆኑ ከትግራይ ክልል ጋር በሚኖረው ሕገ መንግሥታዊ ግንኙነት መሠረት አደረጃጀቱን በማስፋት በቅርቡ በክልሉ በሁሉም ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ጽሕፈት ቤቶችን ይከፍታል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ በትግራይ ክልል ነባራዊ ሁኔታ እስካሁን ትርጉም ባለው መልኩ እንቅስቃሴ እንዳልተደረገ የገለጹት አቶ አወሉ፤ ነገር ግን አሁን በአዲስ መልክ የትግራይ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ተቋቁሞ ሥራውን እየሰራ ስለሆነ በቅርብ ጊዜ በክልል፣ በዞኖች፣ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ እንቅስቃሴ ይደረጋል ብለዋል።
ፓርቲው በትግራይ ክልል ብዙ ደጋፊዎች እንዳሉት የገለጹት አቶ አወሉ፤ በህወሓት ውስጥ ያሉት ከግማሽ በላይ አመራሮች የብልጽግና ፓርቲ ደጋፊ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የሚከፈቱ ጽሕፈት ቤቶች ላይ የአመራር እጥረት እንደማይገጥም ተናግረዋል።የፓርቲው ሥራም ማሰልጠንና ማደራጀት እንደሆነና የአመራር ክፍተት እንዳይኖር የማብቃት ሥራዎች እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ አወሉ ገለጻ፤ ብልጽግና የሕዝብ ብሶትና ችግር የወለደው የለውጥ ፓርቲ ነው። የአቃፊነትና የአካታችነት ፓርቲ ነው።ሕዝቡን እየከፋፈለ የሚሄድ ሳይሆን ሁሉም ያስፈልገኛል ብሎ የሚያምን ፓርቲ ነው።ከፓርቲው በተቃራኒ የቆሙት ጥቂት ኃይሎች ናቸው።እነዚህ ጥቂት ተቃራኒ ኃይሎች ሕዝቡን በየቤቱ በመሳሪያ የሚያስፈራሩት ቢሆንም ሕዝቡ አይቀበላቸውም።ምክንያቱም በትግራይ ክልል ያለው ሕዝብም የፓርቲውና የለውጡ ደጋፊ ነው።
«ፓርቲው በፊት የነበሩ ግንባር ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን አክስመው ተቀላቅለዋል።ነገር ግን ህወሓት ከውህደቱ ራሴን አግልያለሁ ብሎ ክልላዊ ፓርቲ ሆኖ ቀጥሏል።ህወሓት ራሱን ማግለሉ መብቱ ነው።ይሄ በጣም ልንኮራበት የሚገባ ነው።ያመኑበትንና የራሳቸውን አቋም የገለጹበት ሁኔታ ስለሆነ እንደ ችግር የሚታይ አይደለም።
ነገር ግን ብልጽግና ባለው አገራዊና ክልላዊ አደረጃጀት የትግራይ ክልል ብልጽግና ፓርቲ እንዲቋቋም ተደርጓል። ጽሕፈት ቤቱ አዲስ አበባ ላይ ተከፍቷል በቅርቡም በትግራይ ክልል በሁሉም ወረዳዎች እንከፍታለን ብለን አቅደናል።ይህ አገራዊ ፓርቲ በሁሉም ክልሎች ላይ ተንቀሳቅሶ የራሱን ዓላማ ለሕዝቡ የሚሸጥበት ሁኔታ ይኖራል» ሲሉም አቶ አወሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋሙ አንድ ላይ ተቀናጅተው ግንባር የፈጠሩበትና ኢህአዴግ በሚል ስሙ ለ27ዓመታት አገር ሲያተራምስ እንደነበር አውስተው አሁን ግን እነዚያን ችግሮች በማስተካከል እውነተኛ ፌዴራሊዝምን በተግባር በማሳየት የሕዝብ የማንነት (በተለይ የቋንቋ፣ የባህል፣ ራስን የማስተዳደር) መብቶችና ጥያቄዎች በአግባቡ መልስ እንዲያገኙ ብልጽግና ፓርቲ እየሰራ መሆኑን፤ በተለይም የኢህአዴግ ዋና ዋና ተግዳሮቶች የሚባሉትን ሙሉ በሙሉ አርሞ ወደ ፊት ለመጓዝ የተደራጀ መሆኑን አቶ አወሉ አስታውቀዋል።