ስለ አገር…. ከዜማ ያሬድ

ስለ አገር…. ከዜማ ያሬድ

  • Post comments:0 Comments

ብዙዎቻችን ስለዛሬ ለመናገር ስናስብ ትናንት የመጣንበትን መንገድ በሚዛን ከመመልከት ይልቅ ወደየራሳችን ፍላጎት በማስጠጋት የፖለቲካ ቀመራችንን እንዳያዛባው አድርገን እንጠቀምበታለን፡፡ ትናንትን እንደየሁኔታው በመቀበል ለዛሬ መማሪያነት ያለፈ ዋጋ እንደሌለው ከማሰብ ይልቅ ዛሬያችንን እንዲያበላሽብን ነጋችንንም እንዲያጨልምብን እናደርጋለን፡፡


በአገራችን ባለፉት ዓመታት የተዘራው የሃሰት ትርክት ፍሬ አፍርቶ እርስ በእርስ መጠራጠር ውስጥ እንደከተተን፤ አንዳችን ለሌላችን እድል ከመሆን ይልቅ ስጋት እንደሆንን አድርገን እንድንቀበል የተቀበረብንን ፈንጅ ማምከን ተስኖን እርስ በእርስ የጥላቻ አዙሪት ውስጥ እንሽከረከራለን፡፡ ዛሬን ማሸነፍ ሲገባን እዛው አዘቅት ውስጥ ስንዳክር ለልጆቻችን ተስፋ ሳይሆን ስጋትን ስንጭር እንውላለን፡፡


የመጣንበት የሃሰት ትርክት አደጋው የከፋ መሆኑን ከእኛ የበለጠ ምስክር ማንም የለም፡፡ ስር የሰደደ ጥላቻ የፈጠረው ጭካኔ ዛሬ ብዙ ንጹሃንን ሰለባ አድርጓል፡፡ ይህ የሆነ ቦታ መቆም አለበት የሚል መቆርቆር ውስጥ መግባት ካልተቻለ ሁላችንም የሚጸጽተን ሌላ የባሰ ሁኔታ ውስጥ መግባታችን አይቀሬ ነው፡፡ ማንም ሰው ቀድሞ ራሱን ከተጠያቂነት ለማዳን በሚመቸው መልኩ ጣቱን ወደሌላው ለመቀሰር ከመሞከሩ በፊት እኔስ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ቦታዬ የቱ ጋር ነበር ብሎ መጠየቅ ይገባዋል፡፡ ስህተትን በስህተት ማረም፤ ቁስልን ሌላ ቁስል በመፍጠር መሻር አይቻልም፡፡ ይልቁንስ ከድጡ ወደማጡ ወደሆነ ሁኔታ ውስጥ ከመግባት ባሻገር፡፡


ውድ አንባብያን አገራችን አሁን ዙሪያ መለስ ፈተና ውስጥ ትገኛለች፡፡ በአንድ ጎን ከትናንት መጥፎ ታሪካችን መፋታት ያላቻለና ስህተትን ሌላ ስህተት በመስራት ማረም በሚፈልግ ትውልድ ተወጥራለች፡፡ በሌላ ጎኑ በአገሪቱ የፖለቲካ ሂደቱ ውስጥ ዘዋሪ የነበረው ሃይል ቦታውን እንዲለቅ በመደረጉ ዛሬም እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አይነት አካሄድ ውስጥ በመግባት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ አገሪቷን እያመሳት የሚገኘው ጽንፈኛ ኃይልም ሌላው ነው፡፡ በተጨማሪም ሁሌም ቢሆን የውስጥ ሰላማችን በተናጋ ቁጥር ተጋላጭነታችንን እንደ መነሻ በመውሰድ አገር ለመድፈር ሙከራ የሚያደርጉት ግብጽና ሱዳን ጨምሮ አንዳንድ የውጭ ኃይሎች አገራችን ላይ የሚያሳድሩት ጫና ነው፡፡


አገሬው መገንዘብ ያለበት ይሄን ዙሪያ መለስ ፈታኝ ሁኔታ ነው፡፡ አገር ያለ ሰው ምንም ናት፡፡ አገር እኛ ነን፡፡ እኔ፣ አንተ አንቺ፡፡ እኛ ስንበረታ አገር ትበረታለች፡፡ እኛ ስንተባበር፤ በአንድነትም ስንቆም አገር ጸንታ ትቆማለች፡፡ እኛ በተዳከምን ቁጥር አገር ትዳከማለች፤ ለአደጋም ትጋለጣለች፡፡ በመሆኑም ቆም ብሎ ከራስ ፍላጎት በላይ ስለአገር….ስለ ነጋችን ማሰብ ግድ ይላል፡፡ ሰላም በሌለበት ሁሉ የመኖር ህልውና አደጋ ውስጥ ነው፡፡ ሰላም መንግስት ብቻ በሃይል የሚያስጠብቀው አይደለም፡፡ የሰላም ባለቤት ህዝብ ነው፡፡ ስለ አገር ሲባል ሁሉም ከራስ ፍላጎት እልፍ ብሎ መጨነቅ ይገባዋል፡፡ መንግስት በአገራችን ያለውን ሁኔታ ለማሻሻል ግንባር ቀደም ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ከማመላከት ባሻገር በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የራስ ሚናን ማየት ግድ ይላል፡፡


መንግስትን ከዚህም ከዚያም ወጥሮ አቅም ለማሳጣት የሚደረገው ጥረት ዞሮ ጉዳቱ ለራስ ነው የሚል እይታ አለኝ፡፡ አገር ብትታመስ ቀድሞ የሚጎዳው ሁሉም ነው፡፡ ዘር፣ ሃይማኖት ሰላም በሌለበት ሁሉ ማምለጫ መንገድ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የውጭ ሃይሎች አገራችን ውስጥ ጣልቃ ቢገቡ ምናልባትም ከሶሪያ፣ ከየመንና ሌሎች አገራት በባሰ ሁኔታ ውስጥ ነው የምንገባው፡፡ ይህ ደግሞ ሁሉንም የአገሪቱን ህዝብ አደጋ ውስጥ የሚከት እንጂ ከዚህ የሚያተርፍ ማንም የለም፡፡ ትርፍ አገኛለሁ ብሎ ከውጭ ሃይሎች ጋር በራሱ አገር ጉዳይ ያበረውም ጭምር ያኔ መግቢያ አይኖረውም፡፡

ህልውናው አደጋ ውስጥ ነው የሚሆነው፡፡ ለዛም ነው ብልጽግና የውስጥ ሰላማችን እንዲጠበቅ፤ ተጋላጭነታችንም እንዲቀንስ በሚቻለው ሁሉ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ በመሪዎቹ አማካኝነት በተደጋጋሚ ሲገልጽ የሚደመጠው፡፡ ይህን አደጋ በሁሉም አቅጣጫ ማመዛዘን ያስፈልጋል፡፡ ምን ይመጣል፤ ካልደፈረሰ አይጠራም ብሂል አይሰራም፡፡

የደፈረሰውን ማጥራት ያቃጣቸው ዛሬም አገራቸው የትርምስ ማዕከል ሆና ህዝባቸውን ወደቀደመ ሰላማቸው ለመመለስ የተቸገሩ አገራትን ማየት በቂ ነው፡፡
በእኔ ምልከታ ብልጽግና በተደራራቢ ፈተና ውስጥም ሆኖ ወደፊት መጓዝን፤ በጨለማ ውስጥ ብርሃን መዝራት እንደሚቻል በእምነት ይዞ እየሰራ ያለ ጠንካራ ድርጅት ነው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ልማቶችን ለማሳለጥ እየተጋ ነው፡፡ ዛሬም አርሶ አደሩ ከአድማስ ባሻገር ያለውን ተስፋ አይቶ በትጋት እንዲሰራ ምርታማነቱን እንዲጨምር አዳዲስ ቴክኖሎጂን ከማስተዋወቅ ጨምሮ በትጋት እንዲሰራ የማበረታት ስራ እየተሰራ ያለው፡፡ ብልጽግና በፈተና ውስጥም ሆኖ አገር ማስቀጠል የሚችል ቁመና ያለው ፓርቲ መሆኑን በተለያየ አጋጣሚ ማሳየት የቻለ ፓርቲ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡


ብልጽግና ነገን በብሩህ ማየት የምንችልበት የብርሃን ጮራ የሚፈንጥቅ እሳቤ ይዞ የመጣ ድርጅት ነው፡፡ የትኛውም አካባቢ ከስህተት የጸዳ የለም፡፡ ሁሉም ስህተት ሰርቷል፡፡ አሁን የሚስፈልገው እርምትና መደመር ነው፡፡ ዛሬን፣ ነገንና ወደፊትን በወንድማማችነት ስሜት ሆኖ አገር ማስቀጠል ላይ መረባረብ ያስፈልጋል በሚል አዲስ አገር ቀያሪ እሳቤ የሚያራምደው፡፡ ትርክቶቻችንን ዛሬያችንን እንዲያጨልሙ የነገ መዳረሻችን እንቅፋት እንደሆኑ እድል መስጠት አያሻም፡፡ ስለአገር ሲባል በወንድማማችነት ስሜት ነጋችንን ማቃናት ያስፈልገናል፡፡ በመሆኑም ዙሪያ ገባውን ማየት ያስፈልጋል እላለሁ፡፡


አገር አገር ናት፡፡ በድካማችንም በብርታታችንም ልክ የምትመዘን ናትና አገራችንን ማቆም ላይ እንረባረብ፡፡ እናስተውል፡፡ ምናልባትም መመለስ የማንችለው ችግር ውስጥ ከመግባተችን በፊት ከመንግስት ጎን በመቆም አለኝታነታችንና ለአገራችን ያለንን ቀናኢነት ማሳየት ይገባል፡፡ የሃሳብ ብዝሃነት በአገር ጉዳይ ላይ በጋራ ከመቆም አያግድም ስለሆነም አገራችን እኛ የምትሻበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለንና ልብ ልንል ይገባል እላለሁ፡፡ ስለ አገር ሲባል ችግሮቻችንን ከእኛ በላይ አግዘፍን ከማየት ተላቀን ከችግሮቻችን በላይ ያለንን እምቅ አቅም በማሰብ መፍትሄ ላይ እንረባረብ ለዚህ ደግሞ ሁላችንም ከራሳችን እንጀምር እላለሁ ሰላም፡፡

Leave a Reply