You are currently viewing እይታችን ለመዳረሻችን መሰረት ነው! ከዜማ ያሬድ

እይታችን ለመዳረሻችን መሰረት ነው! ከዜማ ያሬድ

  • Post comments:0 Comments

ጽንፈኝነት የሃሳቡን ተሸካሚም ሆነ በዙሪያው ያለውን አካል ገዝግዞ የሚጥል አስተሳሰብ ነው፡፡ በእኔ ስኬት ውስጥ አንተ ወይም አንቺ አለሽ፤ በእኛ ስኬት ውስጥ እናንተ፤ በእናንተ ውስጥ ደግሞ እኛ አለን የሚል የመደጋገፍና የአብሮነት እሳቤ ግለሰብን፣ ማህበረሰብን ብሎም አገርን ማሻገር የሚችል ተራማጅ አስተሳሰብ ነው፡፡

እኔ ብቻ የሚል ከብዙሃኑ የተነጠለና ጽንፍ የያዘ አስተሳሰብ መጨረሻው ውድቀት መሆኑን በዓይናችን ያየነው እውነታ መሆኑ አይካድም፡፡ ጽንፈኝነት አልያም መስመር የወጣ ግለኝነት የአስተሳሰብ ወይም ነገሮችን የመረዳትና በምሉዕ እይታ የመመዘን ግድፈት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ማናቸውንም ጉዳዮች በተነጣጠለ እና ትርጉም በማይሰጥ መንገድ መመልከት ተገቢ ላልሆነ ውሳኔ የሚዳርግ ነው።

የተበጣጠሰ ወይም ሙሉዕ ያልሆነ እይታ የነገሮችን መጨረሻ እና ድምር ተፅዕኖ ለመረዳት እድል የሚሰጥ አይደለም። ዕይታችን ምሉዕ ካልሆን ምን እየሰራን እንደሆነ እና መንገዳችን ወዴት እንደሚያደርሰን ለመገንዘብ መቸገራችን አይቀሬ ነው፡፡

ዛሬን ከትናንት እና ከነገ ጋር በድክመትም ይሁን በጥንካሬ በመመዘን አሁን እየሰራን ያለው ስራ ቀደም ብሎ ከሰራነው እና ወደፊት ከምንሰራው ስራ ጋር በምን እና እንዴት እንደሚገናኝ ማወቅ ካልታቻለ ህልማችንን ማሳካት፤ ራዕያችንንም መኖር አይቻለንም፡፡ ስለሆነም በድርጊቶቻችን መካከል የምክንያትና የውጤት ትስስር መኖሩን ማወቅ ብርሁ ነገን ለማየት ወሳኝ ነው።ፕራግማቲዝምም ሆነ የመደመር እሳቤ ይህ ነው፡፡

ከተበጣጠሰ እይታ ይልቅ በነገሮች ውስጥ ያለውን መወራረስ፣ መተሳሰር የሚያጎላ አመለካከት መያዝ ማለት ነው። ነገሮችን በማይታረቁ ጉዳዮች ጎራ ከፍሎ መመልከት ሳይሆን በነገሮች መካከል ያለውን ቀጣይነትና ትስስር በማመን ያለውን የእርስ በእርስ በጎ መሳሳቦችን በምሉዕ እይታ መመልከትን የሚያስቀድም ነው። ይህ እሳቤ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ወደፊት የሚያራምድ እሳቤ ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ታሪካችን፣ ባህላችን፣ ልማዳችን፣ እምነታችን እና ሌሎች ጉዳዮቻችን የሚያስተሳስሩን እንጂ የሚለያዩን እንዳልሆነ በጥልቅ መረዳት ግድ ይላል፡፡ በተሸራረፈ መንገድ በማየት እርስ በእርስ የሚያለያየንና የሚያራርቀን ጉዳይ ላይ በማተኮር አንድታችን ላይ ሳንካ ለመሆን የሚራወጠውን ኃይልም መስመር ማስያዝ የሚቻለው እሴቶቻችን ያላቸውን መተሳሰርና መወራረስ በጥልቀት ማየት ስንችል ነው፡፡

ነገሮችን በተነጣጠለ መልኩ መመልከት ችግር እንጂ መፍትሄ የማይወልድ በመሆኑ እይታችን ምሉዕ መሆን ይገባዋል፡፡ አሁን ባለው የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሁላችንም እንደምንገነዘበው አገራችን በየአቅጣጫው በሁለት ጽንፍ ተወጥራለች፡፡ አንድነትን በሚሹ፤ ለኢትዮጵያውያን አንድነት ሌት ተቀን በሚሰሩና ግላዊነትን በሚያንፀባርቁ፤ መከፋፈልን በሚሰብኩ ተዋናዮች።

የእነዚህ ተዋናዮች መሰረታዊ ልዩነት በጉዳዮች ላይ ያለ የተበጣጠሰ እይታና እና በምሉዕ የመመልከት ነው፡፡ ዘመናዊ ሚዲያ ደግሞ በዚህ ውስጥ እየተጫወተ ያለውን ሚና ደግሞ መገመት አያዳግትም፡፡ መጻፍና መናገር የፈለገ ሁሉ መልዕከቱ እና ውጤቱን ከሚዛን ሳያስገባ የተረዳውን ብቻ በተበጣጠሰ እይታ ለአድማጩ ይዘረግፈዋል፡፡

ለመናገር የፈለገ ሁሉ ማይክ አየጨበጥ ያሻውን ማለቱ፤ ለመፃፍ የፈለገ ሁሉ እንዲሁ ቢያሻው በዘመናዊ ሚዲያ አልያም ደግሞ በተለምዶ ሚዲያው ብዕሩን አንስቶ ከወረቀቱ በማገናኘት የመሰለውን መጻፉ ሄዶ አገርና ህዝብ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሰረፉ አልቀረም፡፡

ጽንፈኝነትን እየኮነኑ ጽንፈኝነትን የሚያባብሱ መጣጥፎችን መለጠፍ፤ ግለኝነትን እየተቃወሙ፤ አንድነትን በአፍ እየሰበኩ በተግባር ደግሞ ለአንድነት ሳንካ ለወንድማማችነታችን እንቅፋት የሆኑ ሃሳቦችን ቀምረው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲሰነዝሩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ነጻነት ከኃላፊነት ጋር መሳ ለመሳ መሄድ ሲችል ለአገር ትልቅ አበርክቶት ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ።

የተለምዶ ሚዲያዎችንም ሆነ ዲጂታል ሚዲያውን የሚጠቀሙ አካላት የመጫወቻ ሜዳውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወንድማማችነትን የማይሰብኩበት፤ ለአንድነት የማይሰሩበት ከሆነ፤ ግለሰቦች ጊዜያቸውን በዘመናዊ ሚዲያ ላይ እያጠፉ ነገር ግን ለአገርና ህዝብ ጠብ የሚል ነገር የማያበረክቱበት ከሆነ ኪሳራው የሁሉም መሆን ግልጽ ነው፡፡

በመሆኑም ሁሉም ሰው በአስተሳሰብ ደረጃ የሚኮንነውን ከራሱ ማራቅና ወደፊቱን ማስተካከል ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት፡፡ ጽንፈኝነትን በአንደበት መኮነን ብቻ ሳይሆን በተግባር የኮነኑትን ከራስ መነጠል ግድ ይላል፡፡ ግለኝነትን መንቀፍ ብቻ ሳይሆን በተግባር አስወግዶ ህብረትን ወንድማማችነትን አጠንክሮ መያዝ ያስፈልጋል፡፡

የተለወጠ አስተሳሰብ መያዝና ነገሮችን በምሉዕ እይታ መመልከት አገርና ህዝብ ይለውጣል፤ ብልጽግናንም ያረጋግጣል፡፡ በመሆኑም አንድነታችንን የሚሸረሽሩ እሳቤዎችን በማሰወገድ ተራማጅ እና አገር በሚለውጡ ጉዳዮች ላይ ርብርብ ማድረግ ይገባል፡፡ እይታችን ነጋችንን የሚወስን ነውና ሁሌም ቢሆን ምሉዕ እይታ መያዝ ግድ ይላል እላለሁ፡፡ ሰላም፡፡

ምላሽ ይስጡ